በሃሚድ አወል
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) “ኢትዮጵያ የጎበዝ አለቆች ሀገር” እንዳትሆን ከፍተኛ ስጋት እንዳለው ገለጸ። የሀገርን ሰላም እና አንድነት ማስከበር በዋነኝነት የፌደራል መንግስት ኃላፊነት ነው ያለው ኢዜማ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚወሰደው እርምጃ በአንድ ወጥ የዕዝ ሰንሰለት በፌደራል መንግስት እና በመከላከያ ሰራዊት አመራር ሰጪነት ብቻ መሆን እንደሚገባውም አሳስቧል።
ኢዜማ ይህን ያለው ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 10፤ 2013 አዲስ አበባ በሚገኘው ጽህፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው። የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ “በሰከነ መንገድ አስበን ያወጣነው” ያሉት መግለጫ፤ ዋነኛ ትኩረቱ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ውጊያ ነው።
ፓርቲው በሰኔ ወር መጨረሻ ይፋ አድርጎት በነበረው የቢሆንስ ትንተና (scenario) ላይ ፤ ህወሓት ከሌሎች አክራሪ ብሔርተኞች ጋር ጥምረት መመስረት የሚችልበት ሁኔታ የሚፈጠር ከሆነ፤ በአገሪቱ እና በቀጠናው ላይ ከፍተኛ አደጋ ሊደቅን እንደሚችል መግለጹን አስታውሷል። “ሕወሓት አሁን ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለው እና አደጋ የደቀነው በአማራ እና በአፋር ክልሎች ቢሆንም ይህን ጉዳት እና አደጋ በአስቸኳይ ማቆም ካልቻልን ሳያውል ሳያድር በሁሉም የሀገራችን አካባቢ መከሰቱ የማይቀር ነው” ሲል ፓርቲው በዛሬው መግለጫው ተንብዩአል።
ኢዜማ “በሁሉም ላይ የተጋረጠ” ያለውን “አደጋ” በብቃት ለመመከት እና ለማስቀረት፤ ኢትዮጵያውያንን በአንድነት አሰብሳቦ ማሰለፍ የሚችለው የፌደራል መንግስት መሆኑን አመልክቷል። ሆኖም የፌደራል መንግስቱ በሀገሪቱ ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመቀልበስ የሚወሰደው እርምጃ “የዛሬውንም ሆነ የወደፊቱን ወቀሳም ሆነ የድል ሽሚያ ማስቀረት በሚያስችል መልኩ” እንዲደረግ ጠይቋል።
እርምጃው በ“አንድ ወጥ የእዝ ሰንሰለት” መፈጸም ይገባዋል የሚል እምነቱን በመግለጫው ያንጸባረቀው ኢዜማ፤ የአመራር ሰጪነቱም በፌደራል መንግስት እና በኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት ብቻ መከናወን እንደሚገባው አበክሮ አሳስቧል። በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተገኙት የፓርቲው የስራ አስፈጻሚ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ፤ “በእርግጠኝነት የምነግራችሁ TPLF [ህወሓት] ይሸነፋል። ነገር ግን ከተሸነፈ በኋላ [ኢትዮጵያ] የጎበዝ አለቆች ሀገር ከሆነች፤ የትህነግ [ህወሓት] ሽንፈት ምንም ትርጉም አይኖረውም” ሲሉ የመጪውን ጊዜ ስጋታቸውን አጋርተዋል።
የፌደራል መንግስት በአመራር ሰጪነት ከሚጫወተው ዋነኛ ሚና ባሻገር፤ ግዴታውን በከፍተኛ ውጤታማነት መወጣት የሚያስችለውን “ብሔራዊ የአገር ሉዓላዊነት እና የህዝብ ደህንነት ማስከበር ዘመቻ ግብረ ኃይል” “በአስቸኳይ” እንዲያቋቋም ኢዜማ ጥሪ አቅርቧል። ግብረ ኃይሉ የወታደራዊ፣ የዓለም አቀፍ ግንኙነት፣ የፕሮፖጋንዳ ስራዎችን በተመለከተ ስትራቴጂዎችን የሚነድፍ እንደሚሆን በፓርቲው ምክረ ሃሳብ ተመላክቷል።
የዘመቻ ግብረ ኃይሉ ከዚህ በተጨማሪም ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉና እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች ማገዝ እንዲሁም ከሀብት ማሰባሰብ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ መሰራት ያለባቸው ስራዎች ላይ ስትራቴጂዎች የሚቀርጽ እንደሚሆንም ኢዜማ ጠቁሟል። የሚቋቋመው ግብረ ኃይል እነዚህ ስትራቴጂዎች እንዲፈጸሙ ውሳኔዎች የማስተላለፍ ስልጣን እንደሚኖረውም በምክረ ሃሳቡ ተዘርዝሯል።
ኢዜማ በመግለጫው የግብረ ኃይሉ አወቃቀር ምን መምሰል እንዳለበትም ጥቆማ ሰጥቷል። በዋነኛነት በፌደራል መንግስት የሚመራ መሆን አለበት የተባለው የዘመቻ ግብረ ኃይል፤ በሁሉም የመንግስት እርከኖች በተዋረድ የሚደራጅ ሆኖ መዋቀር እንዳለበት ሀሳብ ቀርቧል። ግብረ ኃይሉ ከመንግስት መዋቅር ውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ጭምር ማሳተፍ እንደሚገባውም ኢዜማ አሳስቧል። የጥሪው ዓላማ ሁሉም በየሙያ መስኩ ለሀገሩ እንዲያዋጣ ነው ብለዋል የኢዜማ ስራ አስፈጻሚ አባሉ አቶ ግርማ ሰይፉ።
ተቃዋሚ ፓርቲው በዛሬው መግለጫው “ችግሮች በኃይል አማራጭ ብቻ ይፈታሉ የሚል እምነት እንደሌለው” በድጋሚ አስታውቋል። ሆኖም “ህወሓት እና አጋሮቹ ወደ ሰላማዊ መስመር እስኪመጡ ድረስ፤ የሀገርን ሉዓላዊነት እና የህዝብን ደህንነት ማስጠበቅ የመንግስት ኃላፊነት ነው” ሲል ይህን በተመለከተ የፌደራል መንግስቱ ሚና ላቅ ያለ መሆኑን አስታውሷል። የመከላከያ ሰራዊት እና የሌሎች የጸጥታ አካላት በዚህ ረገድ የሚያደርጉት ተልዕኮ እንዲሳካም ኢዜማ “የሚችለውን ሁሉ ተሳትፎ የሚያደርግ መሆኑን” በመግለጫው አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)