በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ከምትገኘው ኮምቦልቻ ከተማ ወደ አዲስ አበባ ለመጓዝ የተሽከርካሪዎች አጥረት በመፈጠሩ፤ መንገደኞች ከመደበኛ የትራንስፖርት ታሪፍ አምስት እጥፍ ለመክፈል መገደዳቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ። ሌላኛው የትራንስፖርት አማራጭ የነበረው የአውሮፕላን በረራም ካለፈው ሰኞ ወዲህ መቋረጡንም የከተማይቱ ነዋሪዎች ተናግረዋል።፡
“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው አራት መንገደኞች፤ ነገ አርብ ጥቅምት 12፤ 2014 ወደ አዲስ አበባ ለሚደረግ ጉዞ አንድ ሺህ ብር ከፍለው ለመሄድ መስማማታቸውን አስረድተዋል። በሚኒባስ ተሽከርካሪዎች ለሚደረገው እና እስከ 1,200 ብር ለሚጠየቅባቸው በእነዚህ ጉዞዎች ለመሄድ፤ መንገደኞች ከደሴ ከተማ ጭምር የመጡ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በሀገር አቋራጭ አውቶብሶች ከሁለት መቶ ብር ባነሰ ታሪፍ ይጓጓዙ የነበሩ መንገደኞች የመደበኛ ዋጋውን አምስት እጥፍ ያህል እንዲከፍሉ የተገደዱት፤ በአካባቢው የተሽከርካሪ እጥረት በመከሰቱ መሆኑን ደላሎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር’” ገልጸዋል። የተሽከርካሪዎች እጥረቱ የተከሰተው ሀገር አቋራጭ አውቶብሶች “ለግዳጅ በመሰማራታቸው ነው” ብለዋል።
ከኮምቦልቻ ወደ አዲስ አበባ ከሚደረገው ጉዞ በተጨማሪ ወደ አጎራባች ከተሞች እና ወረዳዎች የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች፤ መንገደኞችን እጥፍ እያስከፈሉ መሆኑን የከተማይቱ ነዋሪዎች ተናግረዋል። ወደ አዲስ አበባ ለመጓዝ ሌላኛው የትራንስፖርት አማራጭ የነበረው የአውሮፕላን በረራ ላለፉት ሶስት ቀናት መቋረጡ፤ ከፍተኛ የመጓጓዣ ዋጋ ለሚጠይቁ አሽከርካሪዎች እድል እንደፈጠረላቸውም አመልክተዋል።
በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሰራተኛ የሆኑ አንድ ግለሰብ ትላንት ረቡዕ ጥቅምት 10 በአውሮፕላን ወደ አዲስ አበባ ሊጓዙ የነበረ ቢሆንም “በረራ የለም” ስለተባሉ መቅረታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ሶስት የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዎችም ከሰኞ ጀምሮ ወደ ከተማይቱ በረራ እንዳልነበር ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ ኮምቦልቻ የሚያደርገውን የመንገደኞች በረራ ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ማቋረጡን በኮምቦልቻ አየር ማረፊያ የሚሰሩ አንድ ግለሰብ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። ዛሬ ሐሙስ ጥቅምት ረፋድ ላይ በነበረ ስብሰባ “በረራው በወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ ታግዷል” መባሉንም የአየር ማረፊያው ሰራተኛ ተናግረዋል። ጉዳዩን በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው “[በረራ] መቋረጡን አላውቅም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)