ለስኳር ልማት ታስበው የተገነቡ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ስንዴ ለማምረት ሊውሉ ነው

በሃሚድ አወል

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት በጸደቀው ተጨማሪ በጀት የሚጠገኑ አራት የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች፤ ለስንዴ ማምረቻነት እንደሚውሉ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር አስታወቀ። ለስኳር ልማት ታስበው የተገነቡት አራቱ የመስኖ ፕሮጀክቶች ለምግብ ፍጆታ እንዲውሉ የተደረጉት፤ በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ምክንያት ሊከሰት የሚችለውን የምግብ እጥረት ለመቅረፍ ነው ተብሏል። 

በአቅራቢያቸው ለተገነቡ የስኳር ፋብሪካዎች ግብዓት የሚሆነውን የሸንኮራ አገዳ በስፋት ለማምረት ታስበው የተገነቡት  የኦሞ ኩራዝ፣ ጣና በለስ እና ተንዳሆ የመስኖ አውታሮች ናቸው። ግድብ እና የመስኖ አውታርን በአንድ ላይ ያቀፈው የከሰም ፕሮጀክትም ለተመሳሳይ ዓላማ እንዲውል የተገነባ ነበር። 

ባለፈው ሳምንት አርብ ጥር 20 በፓርላማ በጸደቀው የፌደራል መንግስት ተጨማሪ በጀት ውስጥ፤ ለእነዚህ አራት የመስኖ ፕሮጀክቶች ጥገና የሚውል የ2.2 ቢሊዮን ብር ገንዘብ መመደቡ ይፋ ተደርጓል። ለመስኖ ፕሮጀክቶቹ ጥገና በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የተመደበው “አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ እና ከመንግስት የትኩረት አቅጣጫ አንጻር” በመስኖ ልማት ረገድ ያለውን “ክፍተት ለማጥበብ” በሚል እንደሆነ ተጨማሪ በጀቱን ለማብራራት በቀረበ ሰነድ ላይ ተገልጾ ነበር።

በመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ብርሃኑ ሌንጂሶ፤ “ከዚህ ከጦርነቱ [ጋር] ተያይዞ የምግብ እጥረት ሊኖር ይችላል ተብሎ ይታሰባል። ለዚያ ግብዓት የሚሆን ነገር ለማምረት ነው ይኼን ተጨማሪ በጀት የጠየቅነው” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

“ለማምረት የታቀደው ለሚመረትበት አካባቢ ተገቢ የሆኑ ለምግብ ፍጆታ የሚውሉ ሰብሎችን ነው” የሚሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በተቻለ መጠን በስንዴ ምርት ላይ “ትኩረት ይደረጋል” ሲሉ በመንግስት ቅድሚያ የሚሰጠውን የሰብል አይነት አስረድተዋል። የመስኖ ፕሮጀክቶችን በመጠቀም በዓመት ሶስት ጊዜ ማምረት እንደሚቻል የጠቆሙት ዶ/ር ብርሃኑ፤ በአራቱም ፕሮጀክቶች ከሶስቱ የምርት ወቅቶች በአንዱ ስንዴ የመመረት እድሉ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

ለምግብ ፍጆታ የሚውሉ ሰብሎችን ያመርታሉ የተባሉት የመስኖ ፕሮጀክቶች የተመረጡት በፕሮጀክቶቹ የማልማት አቅም መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ዶ/ር ብርሃኑ የመስኖ ፕሮጀክቶቹ ለስኳር ፋብሪካዎች ግብዓት የሚሆነውን የሸንኮራ አገዳ ለማልማት በሙሉ አቅማቸው ጥቅም ላይ አልዋሉም ይላሉ። ለዚህም የኦሞ ኩራዝ ፕሮጀክትን በአስረጂነት ይጠቅሳሉ። 

“ኦሞ ኩራዝ ትልቅ መሬት ነው ያለበት። ስኳር ነው እየለማበት ያለው። እዚያ ትልልቅ ስኳር ፋብሪካዎች አሉ። ግን ስኳር ኮርፖሬሽን ሙሉ በሙሉ እየተጠቀመበት አይደለም” ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል።

በኦሞ ኩራዝ ሊለማ የሚችለው መሬት ስፋት 175 ሺህ ሄክታር እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከዚህ ውስጥ 7,800 ሄክታር የሚሆነው መሬት እንዲለማ ለማስቻል ለሚደረገው እድሳት ብቻ 1.5 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ሚኒስቴር ዴኤታው ይገልጻሉ። ይህ የገንዘብ መጠን ማለት፤ ባለፈው ሳምንት አርብ በጸደቀው ተጨማሪ በጀት ለመስኖ ፕሮጀክቶች ከተመደበው 75 በመቶ የሚሆነውን የሚይዝ ነው። 

ዶ/ር ብርሃኑም፤ ለመስኖ ፕሮጀክቶቹ ጥገና በተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው የ2.2 ቢሊዮን ብር በጀት “በቂ ነው” የሚል እምነት የላቸውም። የእርሳቸው መስሪያ ቤት በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን በኩል ባሰራው ጥናት፤ የኦሞ ኩራዝን የመስኖ ፕሮጀክት ጥገና አከናውኖ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ለማስገባት ብቻ 30 ቢሊዮን ብር እንደሚስፈልግ መገመቱን ለዚህ በማሳያነት ጠቅሰዋል። 

ኦሞ ኩራዝን ጨምሮ የሚጠገኑት አራት የመስኖ ፕሮጀክቶች ያመርቱታል ተብሎ የሚገመተው የሰብል ምርት መጠን የሚታወቀው፤ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ጋር እያካሄደው ካለው ጥናት መጠናቀቅ በኋላ ነው ተብሏል። ኢትዮጵያ በ2013 ያመረተችው የስንዴ ምርት መጠን 5.1 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የሚገመት እንደሆነ፤ የአሜሪካ መንግስት የግብርና ሚኒስቴር ባለፈው ዓመት መጋቢት ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል።  

በተመሳሳይ ወቅት በኢትዮጵያ የነበረው የስንዴ ፍጆታ 6.7 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን መሆኑ በሪፖርቱ ተጠቅሷል። በሪፖርቱ መሰረት ኢትዮጵያ 25 በመቶ የሚሆነውን የሀገር ውስጥ የስንዴ ፍላጎት የምታሟላው ከውጭ በግዢ በማስመጣት ነው። በ2012 በጀት ዓመት ወደ ኢትዮጵያ ከገባው 1.4 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ውስጥ፤ 256 ሺህ ሜትሪክ ቶን የሚሆነው የመጣው ከአሜሪካ መሆኑን በሪፖርቱ ተመላክቷል።  

ከዩናይትድ ስቴትስ ከሚመጣው ስንዴ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለውን ድርሻ የሚይዘው፤ አሜሪካ ለኢትዮጵያ በእርዳታ የምትልከው ነው። ኢትዮጵያ ከአሜሪካ የስንዴ እርዳታን በቀዳሚነት ከሚቀበሉ የአፍሪካ ሀገራት አንዷ ነች። 

“2014፣ 2015 በደንብ ሰርተን ስንዴ ሚባል ነገር ኢትዮጵያ እንዳይገባ ካደረግን 70 ፐርሰንት የኢትዮጵያ ችግር ይቀረፋል። የኢትዮጵያ ችግር የእርዳታ ስንዴ ነው”

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባለፈው ጥቅምት ወር የመኸር እርሻ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት የተናገሩት

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከሶስት ወራት በፊት ከክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ጋር በኦሮሚያ ክልል የመኸር እርሻ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት፤ ከኢትዮጵያ ዋነኛ ችግሮች አንዱ “ከውጭ የሚገባ የእርዳታ ስንዴ” መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል።  “2014፣ 2015 በደንብ ሰርተን ስንዴ ሚባል ነገር ኢትዮጵያ እንዳይገባ ካደረግን 70 ፐርሰንት የኢትዮጵያ ችግር ይቀረፋል። የኢትዮጵያ ችግር የእርዳታ ስንዴ ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ተናግረው ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)