የፖለቲካ ፓርቲዎች በፖለቲካዊ እና ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የሚያደርጉት ውይይት የሚመራበት መመሪያ ጸደቀ

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ ህጋዊ ዕውቅና ያገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች በፖለቲካዊ እና ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የሚያደርጉት ውይይት የሚመራበትን መመሪያ አሻሽሎ አጸደቀ። መመሪያው ከተከታታይ ውይይቶች በኋላ የጸደቀው ዛሬ ጥር 25፤ 2014 ቦርዱ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረገው ስብሰባ ላይ ነው።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይትን ለመምራት የመጀመሪያው መመሪያ የወጣው ከሶስት ዓመታት በፊት በ2011 ነበር። ዛሬ የጸደቀው የተሻሻለው መመሪያ፤ በፓርቲዎች መካከል የሚደረገው ውይይት የሚካሄድበትን ስርዓት፣ የሚመራበትን መርህ እና ከተወያዮች የሚጠበቀውን ኃላፊነት በሶስት ምዕራፎች እና ሃያ አንድ አንቀጾች ዘርዝሮ አቅርቧል። 

የተሻሻለው መመሪያ ፓርቲዎች ውይይት የሚያካሂዱበት መድረክ እንዲቋቋም ያደርጋል። ከውይይቱ አላማዎች መካከል አንዱ፤ የፓርላማ እና የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች በአብዛኛው በአንድ ፓርቲ የተያዙ መሆናቸው በሁሉም ፓርቲዎች መካከል ሊኖር የሚገባውን ውይይት በቀጣይነት ማስተናገድ ነው።

ከውይይት ሂደቱ አላማዎች ውስጥ አንደኛው፤ በዛሬው የምርጫ ቦርድ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብሰባ ላይ ከፍተኛ ክርክር አስንስቷል። ፓርቲዎችን ያከራከረው የውይይቱ ዓላማ “በአገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሚመራው ሁሉን አቀፍ ምክክር መድረኮች ግብዓት የሚሆኑ የስምምነት ሀሳቦችን ማቅረብ” በሚል በመመሪያው መግቢያ ላይ የተቀመጠ ነው።

አቶ ጀቤሳ ጋቢሳ “በሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በኩል ስምምነት የለም። engage እናደርጋለን፤ አናደርግም የሚለውን ያልወሰኑ ፓርቲዎች አሉ” ሲሉ በዛሬው ስብሰባ ላይ ተናግረዋል [ፎቶ፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ]

ይህ የውይይት ዓላማ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና ከኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ተቃውሞ ገጥሞታል። በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግን ወክለው በስብሰባው የተሳተፉት አቶ ጀቤሳ ጋቢሳ “በሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በኩል ስምምነት የለም። engage እናደርጋለን፤ አናደርግም የሚለውን ያልወሰኑ ፓርቲዎች አሉ። እኛ engage እያደረግን አይደለም” ሲሉ የፓርቲዎቹ ውይይት ለሀገራዊ ምክክክሩ ግብዓት ይሆናል መባሉን ተቃውመዋል።

የኦፌኮ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ጥሩነህ ገምታ፤ አገራዊ ምክክሩ “ሁሉን አቀፍ ስለመሆኑ ምን ያህል እርግጠኛ ናችሁ?” ሲሉ በመመሪያው በሰፈረው ገለጻ ላይ ጥያቄ አንስተዋል። የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ተወካይ የሆኑት አቶ ዛዲግ አብርሃ በበኩላቸው የሁለቱን የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀሳብ የሚቃረን አስተያየት ሰጥተዋል። 

በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል የዘርፍ አስተባባሪ አቶ ዛዲግ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ውይይት ለሀገራዊ ምክክሩ ግብዓት ይሆናል መባሉን እንደ “ዕድል” ወስደውታል። “ስለ ምክክሩ የተቀመጠው እኔ እንደውም ዕድል (opportunity) ነው የሚመስለኝ። ምክክሩ ሁሉን አቀፍ ይሆናል ወይ? ሁሉን አቀፍ ብሎ ህግ ላይ ተቀምጧል” ሲሉ ተናግረዋል።

የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ተወካይ የሆኑት አቶ ዛዲግ አብርሃ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ውይይት ለሀገራዊ ምክክሩ ግብዓት ይሆናል መባሉን እንደ “ዕድል” ወስደውታል [ፎቶ፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ]

የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ “[አገራዊ ምክክሩ] ሁሉን አቀፍ መሆን አለበት። መሆን ያለበትን ነው የምናስቀምጠው እንጂ እንዳይሆን የምንፈልገውን አይደለም። ይህን [ምክክር] የሚመራው ኮሚሽንም ሆነ የሚያግዘውም ማንም አካል ወይም በሌላ መልኩ involve የሚያደርገው መንግስት፤ ነገሩን ከሁሉን አቀፍ በታች ሊያደርገው አይገባም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ከዚህ በፊት በነበሩ ተመሳሳይ ውይይቶችም፤ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚደረገው ውይይት እና የአገራዊ ምክክሩ ጉዳይ ተነስቶ ነበር። “የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ውይይት ከአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ጋር አይጋጭም ወይ?” የሚል ጥያቄ  ላነሱ ተሳታፊዎች የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ “አይጋጭም” የሚል ምላሽ ሰጥተው ነበር። “ይኼኛው የፖለቲካ ልሂቃን የሚያደርጉት ውይይት ነው። ምክክሩ ግን የፖለቲካ ልሂቃንን ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡን በአጠቃላይ የሚያካትት ነው” ብለዋል። 

የፖለቲካ ፓርቲዎች ከዚህ ቀደም ከቦርዱ ጋር በነበራቸው ተከታታይ ውይይቶች መመሪያው ላይ ቢካተተቱ እና ቢቀነሱ ያሏቸውን ሌሎች ጉዳዮችን አንስተው ነበር። ከፖለቲካ ፓርቲዎቹ የተነሱት ዋና ዋና ጉዳዮች በመመሪያው ላይ ስለተነሱ ስያሜዎች እና ከአወያዮች ጋር የተያያዙ ናቸው።

በተሻሻለው መመሪያ መሰረት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የሚያደርጓቸው ውይይቶች የሚመሩት፤ በአብዛኛዎቹ ፓርቲዎች ተቀባይነት ባላቸው እና ገለልተኝነታቸው በተረጋገጠ ግለሰቦች ነው

በተሻሻለው መመሪያ መሰረት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የሚያደርጓቸው ውይይቶች የሚመሩት፤ በአብዛኛዎቹ ፓርቲዎች ተቀባይነት ባላቸው እና ገለልተኝነታቸው በተረጋገጠ ግለሰቦች ነው። “አወያይ” ተብለው በሚመረጡት ግለሰቦች ላይ የገለልተኝነት ጥያቄ ሊነሳ እንደሚችል የጠቆሙት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ፤ “ምርጫ ቦርድ ለምን አወያይ አይሆንም?” የሚል ጥያቄ ሰንዝረው ነበር። 

ዛሬ የጸደቀው መመሪያ ምርጫ ቦርድ፤ የአወያዩን ማንነት ውይይቱ ከመካሄዱ ሰባት ቀናት አስቀድሞ ለፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚያስታውቅ ይገልጻል። ቦርዱ ከዚህ በተጨማሪም ውይይት የሚካሄድበትን ቦታ፣ ሰዓት እና ቀን ከሳምንት በፊት ለፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚያስታውቅ ደንግጓል። ውይይቱ የሚካሄድበትን ስርዓት በሚዘረዝረው የመመሪያው ክፍል ላይ፤ ምርጫ ቦርድ ከሚያቋቁመው የባለሙያዎች ኮሚቴ ጋር በመሆን በፖለቲካ ፓርቲዎች በጽሁፍ የሚቀርቡትን የውይይት አጀንዳዎች ቅደም ተከተል እንደሚያወጣ ያስቀምጣል።  

የፖለቲካ ፓርቲዎች በውይይቱ ተሳታፊ በሚሆኑበት ጊዜ 12 መርሆዎችን ማክበር እንደሚጠበቅባቸው በመመሪያው ላይ ተጠቅሷል። በውይይቱ ሂደት ለሀገራዊ ጥቅም ቅድሚያ መስጠት፣ መደማመጥ፣ መከባበር እና የሌላውን ሀሳብ መረዳት እና ማክበር ከመርሆዎቹ መካከል ናቸው። ውይይቶቹ የሚካሄዱት በፌደራሉ የስራ ቋንቋ አማርኛ እንደሚሆን እና ቋንቋውን ለማይናገሩ ተወያዮች ምርጫ ቦርድ አስተርጓሚ እንደሚያቀርብ በመመሪያው ላይ ሰፍሯል። ቦርዱ እንደ አስፈላጊነቱ የምልክት ቋንቋ ባለሙያ እንደሚመድብም መመሪያው ይገልጻል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)