በሃሚድ አወል
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተፈጸመውን ሰውን አቃጥሎ የመግደል ድርጊት የሚመረምር የወንጀል ምርመራ ቡድን ድርጊቱ ወደተፈጸመበት መተከል ዞን አቀና። ከፍትህ ሚኒስቴር እና ፌደራል ፖሊስ በተውጣጡ መርማሪዎች የተዋቀረው የምርመራ ቡድን ወደ መተከል ዞን የተጓዘው ከትላንት በስቲያ ረቡዕ መጋቢት 7፤ 2014 ነው።
አምስት አባላት ባሉት በዚህ የምርመራ ቡድን ውስጥ ከፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ ሶስት ባለሙያዎች መካተታቸውን የሚኒስቴሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ አወል ሱልጣን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ቀሪ ሁለቱ አባላት ደግሞ ከፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ የተወከሉ ናቸው።
የወንጀል ምርመራው በሁለቱ የፌደራል ተቋማት የሚከናወን መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የገለጹት የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙሊሳ አብዲሳ፤ የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት የአጋዥነት ሚና እንደሚኖረው አስረድተዋል። “የኮማንድ ፖስቱ ስራ የአካባቢውን ጸጥታ ማስጠበቅ እና ተጠርጣሪዎች መያዝ ነው” ሲሉም ምክትል ኃላፊው የኮማንድ ፖስቱን ኃላፊነት አብራርተዋል።
ከመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት አባላት ጋር ትላንት ሐሙስ መጋቢት 8፤ 2014 ውይይት ያደረገው የምርመራ ቡድኑ፤ “ያለውን ነገር አቅዶ ወደ ምርመራ ለመግባት” ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አቶ ሙሊሳ ተናግረዋል። “ምርመራውን ለመጀመር የሚያስችል በቂ ኃይል አለን። ትንሽ የሚያስቸግረን በአካባቢው ያለው የጸጥታ ችግር ነው። [ጸጥታው] አስተማማኝ አይደለም” ሲሉም በመተከል ዞን የሚስተዋለው የጸጥታ ችግር ለምርመራ ቡድኑ ስራ እንቅፋት ሊፈጥር እንደሚችል ጠቁመዋል።
በመተከል ዞን፣ ጉባ ወረዳ፣ አይሲድ ቀበሌ ከሁለት ሳምንት በፊት የተፈጸመው በህይወት ያለን ሰው አቃጥሎ የመግደል ድርጊት በመንግስት የጸጥታ አባላት ተሳትፎ ጭምር መከናወኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባለፈው እሁድ አስታውቆ ነበር። የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ የሕግ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ በተጠርጣሪዎች ላይ ተገቢውን የወንጀል ምርመራ በአፋጣኝ እንዲደረግ አሳስበው እንደነበርም ይታወሳል።
ድርጊቱ ወደተፈጸመበት አካባቢ የወንጀል ምርመራ ቡድን መጓዙን ኢሰመኮ እንደሚያውቅ የኮሚሽኑ የሰብዓዊ መብቶች ክትትልና የምርመራ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ይበቃል ግዛው ገልጸዋል። “መሄዳቸውን እናውቃለን። የተወሰነ ጊዜ እንስጣቸው ብለን ነው። ከዚያ በኋላ ግን በቂ እርምጃ አልተወሰደም ብለን ካሰብን መግለጫ እናወጣለን” ሲሉ ኮሚሽኑ የምርመራ ቡድኑን ስራ በቅርበት እንደሚከታተል አቶ ይበቃል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
ኢሰመኮ ከአምስት ቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ፤ በመተከል ዞን፣ ጉባ ወረዳ፣ አይሲድ ቀበሌ አሰቃቂው ድርጊት በተፈጸመበት ዕለት፤ የመንግስት የጸጥታ ኃይል አባላት አስር ሰዎችን ተኩሰው መግደላቸውን እና አስክሬናቸውን ማቃጠላቸውን ገልጾ ነበር። የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ “ከዳኝነት ውጪ የተፈጸመ ግድያ” (extra-judicial killing) ሲል በጠራው በዚሁ ድርጊት፤ የመከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ክልል ልዩ ፖሊስ እንዲሁም የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ልዩ ፖሊስ አባላት መሳተፋቸውን በመግለጫው ይፋ አድርጓል።
ድርጊቱን በተመለከተ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ መጋቢት 3፤ 2014 መግለጫ ያወጣው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች አገልግሎት፤ “መንግስት ይህን አይነት ፍፁም ከሰብአዊነት የራቀና ጭካኔ የተሞላበትን ድርጊት የፈጸሙ አካላትን አጣርቶ ህጋዊ እርምጃ ይወስዳል” ማለቱ ይታወሳል። ድርጊቱን “እጅግ አሰቃቂ እና ከሰብአዊነት ያፈነገጠ” ሲል የጠራው መስሪያ ቤቱ፤ የንጹሃን ዜጎችን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ አካላትን መንግስት ከዚህ በኋላ እንደማይታገስ አስጠንቅቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)