በናኦል ጌታቸው
በደቡብ ክልል፣ ኮንሶ ዞን ሰገን ከተማ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ የታሰሩ እስረኞችን ትላንት አርብ መጋቢት 23 ለሊት ለማስመለጥ የተደረገ ሙከራ መክሸፉን የአካባቢው ባለስልጣናት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። በሰገን ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ላይ ጥቃቱን የሰነዘሩት “የተደራጁ ጽንፈኛ ኃይሎች” ሲሉም ባለስልጣናቱ ከስሰዋል።
በኮንሶ ዞን የሰገን ዙሪያ ወረዳ አስተዳዳሪ አስተዳዳሪ አቶ በርሻ ኦላታ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደገለጹት፤ በከባድ መሳሪያ ጭምር የታገዘው የትላንቱ ጥቃት የተፈጸመው ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ገደማ ነው። የጥቃቱ ፈጻሚዎች ወደ ፖሊስ ጣቢያው ሁለት የእጅ ቦምቦች መወርወራቸውን የገለጹት አስተዳዳሪው፤ በቦምብ ፍንጣሪም በጥበቃ ላይ ተሰማርቶ የነበረ የሚሊሺያ አባል መቁሰሉን አስረድተዋል።
ጥቃቱን የፈጸሙት ኃይሎች በሁለት አቅጣጫዎች ወደ ሰገን ከተማ መግባታቸውን ያስረዱት አቶ በርሻ፤ በከተማይቱ ተሰማርተው የነበሩት የደቡብ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ከለሊቱ ሰባት ሰዓት ገደማ ወደ ካምፓቸው መመለሳቸውን ተከትሎ በፖሊስ ጣቢያው ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ገልጸዋል። ጥቃት አድራሾቹ ብሬን የሚባል ከባድ መሳሪያ መጠቀማቸውን አክለዋል።
የጥቃቱ ዓላማ በአካባቢው በተለያየ ጊዜ በተከሰቱ ሁከቶች ተጠርጥረው በከተማይቱ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው ያሉ ግለሰቦችን ማስፈታት እንደነበር የሰገን ዙሪያ ወረዳ ወረዳ አስተዳዳሪ አመልክተዋል። “ከፖሊስ ጣቢያው ጀርባ መስጊድ አለ። የመስጊዱን ቆርቆሮ ቀድደው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ በመግባት የእስረኞችን ስም በመጥራት ‘ይሄው መጣን፤ ኑ ውጡ። ከዚህ በኋላ እናንተን እናስወጣለን’ ሲሉ ነበር” ብለዋል።
የእስረኞችን የማስመለጥ ሙከራው የከሸፈው የደቡብ ክልል ልዩ ኃይል እና የፌደራል ፖሊስ ወደ አካባቢው ተመልሰው ከመጡ በኋላ መሆኑን አቶ በርሻ አስረድተዋል። የድርጊቱ ፈጻሚዎች ከደራሼ አካባቢ ሐይቤና ቀበሌ የመጡ “ጽንፈኞች ናቸው” ሲሉም ወንጅለዋል። ይህንን የሰገን ዙሪያ ወረዳ አስተዳዳሪ ገለጻ፤ የወረዳው የመንግስት ተጠሪ አቶ ገሜይዳ ጉዳኖም ይጋሩታል።
“መጀመሪያ የጸጥታ ችግር ነበር። ጽንፈኛው እየገባ፤ ህዝብን እየገደለ፣ እያፈናቀለ ነበረ” የሚሉት የወረዳው መንግስት ተጠሪ፤ ለድርጊቶቹ ተጠያቂ የሚያደርጉት ከሐይቤና ቀበሌ የሚነሱ “የተደራጁ እና ጽንፈኛ” ያሏቸውን ኃይሎችን ነው። እነዚህ ኃይሎች ከመጋቢት 9፤ 2014 ጀምሮ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ባሉ የተለያዩ ቀናት ተደጋጋሚ ጥቃቶችን መፈጸማቸውንም ተናግረዋል።
አቶ ገሜይዳ ለዚህም በማሳያነት የጠቀሱት በሰገን ገነት ቀበሌ ሊቀመንበር አቶ ኩሴ ቶኔ ላይ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ መጋቢት 22 የተፈጸመውን ግድያ ነው። “[ሊቀመንበሩ] ከሰገን ገነት ትምህርት ቤት ወደ ሰገን ከተማ በሚሄድበት ወቅት በግምት ከቀኑ 8 ሰዓት ተኩል የያዘውን መሳሪያ ከነጠቁት በኋላ በታጣቂዎች ተገድሏል። ከዚህም ባሻገር ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ቤቶች ተቃጥለዋል” ብለዋል።
ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ መጋቢት 17 በተመሳሳይ ሁኔታ የሰገን ዙሪያ ወረዳ የገቢዎች ጽህፈት ቤት ኃላፊ በሆቴል ውስጥ በመመገብ ላይ ሳሉ በ“ጽንፈኛ ኃይሎች” መገደላቸውን በተጨማሪ ማሳያነት አንስተዋል። ሁለቱ የሰገን ዙሪያ ወረዳ የመንግስት ኃላፊዎች ለእነዚህ ጥቃቶች ከደራሼ ልዩ ወረዳ የሚመጡ ናቸው የሚሏቸውን ኃይሎች ተጠያቂ ቢያደርጉም፤ በልዩ ወረዳው በኩል ይህ ውንጀላ ተቀባይነት አላገኘም።
የደራሼ ልዩ ወረዳ የኮሙኒኬሽን ባለሙያ አቶ ተማሪ ተስፋዬ፤ የሰሞኑ ግጭት በደራሼ ልዩ ወረዳ እና በኮንሶ ዞን መካከል ባለው የወሰን ችግር ምክንያት የተከሰተ እንጂ በጽንፈኞች የተፈጠረ ሁከት አይደለም ሲሉ አስተባብለዋል። በአሌ ልዩ ወረዳ እና በኮንሶ ዞን መካከል ያለው የአስተዳደር መዋቅር ጥያቄም ከሰሞኑ በአካባቢው ለነበሩ ግጭቶች ሌላ መንስኤ ነው ባይ ናቸው።
በደራሼ እና ኮንሶ የወሰን አካባቢዎች ትላንት አርብ መጋቢት 23 ጭምር ግጭቶች እንደነበሩ የጠቆሙት አቶ ተማሪ፤ በዚህም ሳቢያ እስካሁን ቢያንስ ሶስት ሰዎች መገደላቸውን እንደሚያውቁ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። “ጠንከር ያለ ግጭት በአቴያ ቀበሌና በደራሼ ድንበር አካባቢ ባለ የእርሻ ቦታ ላይ የነበረ ሲሆን፤ በክልሉ ልዩ ኃይል አማካይነት [ትላንት] ማምሻውን ተኩስ ቆሟል” ሲሉ በአካባቢው የነበረውን ሁኔታ አስረድተዋል።
የኮንሶ፣ ደራሼ፣ አማሮ፣ ቡርጂ እና አሌ ብሔረሰቦች፤ የሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን በተባለ የአስተዳደር አወቃቀር ስር ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ ለስምንት ዓመታት ያህል በደቡብ ክልል ስር በአንድ ላይ ሆነው እንዲተዳደሩ ተደርገው ነበር። ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በልዩ ወረዳ ደረጃ የነበረው ኮንሶ ራሱን ችሎ በዞን ሲደራጅ፤ ደራሼ፣ አማሮ እና ቡርጂ በልዩ ወረዳነት ቀጥለዋል። በወረዳ ደረጃ የነበረው የአሌ አካባቢም ወደ ልዩ ወረዳነት አድጓል።
የትላንቱን የሰገን ከተማ ጥቃት ተከትሎ፤ የወረዳው የመንግስት ኃላፊዎች ተመሳሳይ ጥቃት እንዳይፈጸም እርምጃዎች መውሰዳቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ባለስልጣናቱ ከጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች ጋር ባደረጉት ምክክር የከተማውን መግቢያ ለመዝጋት እና በከተማው ውስጥ ሆነው ሁከትን የሚያባብሱ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ከውሳኔ ላይ መድረሳቸውን አስታውቀዋል። ይሆም ሆኖ በሕብረተሰቡ ዘንድ አሁንም ከፍተኛ ስጋት በመኖሩ ምክንያት የደቡብ ክልል ለአካባቢው ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ የወረዳው ባለስልጣናት ጠይቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)