የሐሰተኛ መረጃ እና የጥላቻ ንግግር አሰራጭተዋል የተባሉ መገናኛ ብዙኃን በፌደራል ፖሊስ ምርመራ ሊደረግባቸው ነው

በተስፋለም ወልደየስ

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ሐሰተኛ መረጃ እና የጥላቻ ንግግር አሰራጭተዋል ባላቸው ስድስት መገናኛ ብዙኃን ላይ ምርመራ እንዲካሄድባቸው ሰነዶች አደራጅቶ ለፌደራል ፖሊስ መላኩን  አስታወቀ። ባለሥልጣኑ ምዘገባ ሳያከናውኑ በበይነ መረብ አማካኝነት በህገወጥ መልክ የሚዲያ ስርጭት ላይ የተሰማሩ 25 ድርጅቶችን በህግ ተጠያቂ የማድረግ ሂደት መጀመሩንም ገልጿል።

ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ይህን ያስታወቀው ዛሬ አርብ ሚያዝያ 21፤ 2014 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለህግ፣ ፍትህ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበው የዘጠኝ ወር የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ነው። የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እድሪስ ለቋሚ ኮሚቴው ባቀረቡት ሪፖርት ላይ እንዳሉት፤ መስሪያ ቤታቸው ባለፈው ዘጠኝ ወር ባከናወነው የሞኒተሪንግ ስራ በስድስት መገናኛ ብዙሃን በተሰራጩ 10 ፕሮግራሞች ላይ የህግ ጥሰቶችን ተስተውለዋል።  

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

“ከሐሰተኛ [መረጃ] እና ጥላቻ [ንግግር] ጋር ተያይዞ አስር ፕሮግራሞች ላይ የህግ ጥሰት በመስተዋሉ ፋይሉን አደራጅተን ለህግ አስፈጻሚ አካላት፣ ለፌደራል ፖሊስ ጥቆማ አቅርበናል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የህግ አስፈጻሚ አካላት በሚያደርጓቸው ምርመራዎች ላይ የተቋሙን ሙያዊ ድጋፍ በሚፈልጉበት [ጊዜ] ሁሉንም የጠየቁትን ጥያቄ በህጉ እና በህጉ ብቻ መሰረት አድርገን ሙያዊ ድጋፍ ሰጥተናል” ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ለቋሚ ኮሚቴ አባላቱ አስረድተዋል። 

አቶ መሐመድ የመገናኛ ብዙኃኑን ማንነት በስም ከመጥቀስ ቢቆጠቡም፤ በንግድ መገናኛ ብዙኃን ዘርፍ የተሰማሩ እንደሆኑ ግን በሪፖርታቸው ላይ አመልክተዋል። እነዚህ መገናኛ ብዙኃን “ሚዛናዊነት የጎደላቸው እና የአንድ ወገን ሀሳብና ፍላጎትን የሚያንጸባርቁ አድሏዊ ዘገባዎችን በማቅረብ” የህግ ጥሰቶችን መፈጸማቸውንም ጠቁመዋል። 

ከዚህ በተጨማሪም መገናኛ ብዙኃኑ “ከዘመቻ ለህብረ-ብሄራዊ አንድነት ጋር በተያያዘ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ዙሪያ ያልተረጋገጡ ሐሰተኛ መረጃዎችና አሉባልታዎችን ማሰራጨት እና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን የሚተላለፉ መሆናቸውን ለማየት ተችሏል” ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ለፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡት ሪፖርታቸው ላይ አስፍረዋል።

የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት በተመለከተ በተወሰኑ የህዝብ መገናኛ ብዙኃን ዘንድም ተመሳሳይ ችግር ተስተውሎ እንደነበር የገለጹት አቶ መሐመድ፤ መስሪያ ቤታቸው ባከናወነው “የይዘት ሞኒተርንግ” ላይ ተመስርቶ ባደረገው ክትትል “ያማረ ውጤት” ተገኝቷል ብለዋል። ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ በተለይ በጦርነቱ ወቅት ሳምንቱን ሙሉ፣ ለ24 ሰዓት ሳያቋርጥ የመገናኛ ብዙኃን የሞኒተሪንግ ስራ ሲያከናውን እንደነበርም አስረድተዋል።  

“መጀመሪያ አካባቢ በአንዳንድ የህዝብ መገናኛ ብዙኃን conflict sensitive [ግጭት አገናዛቢ] አለመሆን፣ የሽብር ቡድኑን እንቅስቃሴ ሊደግፉ የሚችሉ ወይም promote ሊያደርጉ የሚችሉ ዘገባዎች ላይ ‘ፋክቱን’ አገኘን በማለት፣ ከሃላፊነት በመጉደል የመስራት አይነት ሁኔታዎች ስለነበሩ፤ ቀጥተኛ intervenetion የሚያስፈልጋቸው ሁኔታዎች ላይ ግብዓት የመስጠት፣ የማስጠንቀቅ፣ የጹሁፍ ማስጠንቀቂያ የመስጠት፣ የመደገፍ፣ የመካከር ስራዎች ተሰርተዋል” ሲሉም መስሪያ ቤታቸው ጥሩ ውጤት አግኝቶበታል ያሉትን የስራ አፈጻጸም አብራርተዋል። 

በበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን ረገድ፤ በባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ “ሳይመዘገቡ የሚዲያ ስርጭት በህገ-ወጥ መልኩ ያካሄዳሉ” የተባሉ 25 ድርጅቶች ተለይተው በመገናኛ ብዙሃን አዋጁ መሰረት በህግ ተጠያቂ ለማድረግ በሂደት ላይ መሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል። በበይነ መረብ አማካኝነት በሚደረግ የመገናኛ ብዙኃን ስራ ፍቃድ ሳያገኙ የተሰማሩት “በጣም ብዙ” መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ መሐመድ፤ ለህግ አስፈጻሚ አካላት በማቅረብ ክትትል እየተደረገባቸው ያሉት “የህግ ጥሰት” በፈጸሙት ላይ ብቻ እንደሆነ ለፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ አባላት ተናግረዋል።    

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

“ከፍተኛ ተጽዕኖ የፈጠሩ በተለይ የጥላቻ ንግግራቸው እና የሀሰተኛ መረጃቸው በሀገር ሰላም እና ደህንነት ላይ የሚፈጥረው የተጽዕኖ ደረጃ ከፍተኛ የሆኑትን በመለየት፣ በህግ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ፣ ፋይላቸውን በማደራጀት ለሚመለከተው ህግ አስፈጻሚ አካላት ቀርቧል። አንዳንዶቹም በተለያየ ሁኔታ ላይ የህግ ሂደት እንደተጀመረ እናውቃለን። የእኛ የህግ ክፍልም እየተከታተለ ይገኛል” ብለዋል አቶ መሐመድ እድሪስ።  

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ፍቃድ የተሰጣቸው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን 34 መሆናቸውን ከመስሪያ ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ሶስት ተጨማሪ መገናኛ ብዙኃን ፍቃድ ለማግኘት ጥያቄ አቅርበው በሂደት ላይ መሆናቸው የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ለፓርላማ አባላቱ አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)