በሃሚድ አወል
የገቢዎች ሚኒስቴር ባለፉት አስር ወራት ብቻ አራት ቢሊዮን ብር ገደማ የሚገመቱ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን መያዙን አስታወቀ። በእነዚህ ወራት ውስጥ በኮንትሮባንዲስቶች በደረሰ ጥቃት ከስድስት በላይ ግለሰቦች ህይወታቸው ማለፉን እና “በበርካቶች” ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት መድረሱን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገልጿል።
የገቢዎች ሚኒስቴር ይህን የገለጸው ዛሬ ሐሙስ ግንቦት 11፤ 2014 ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው የአስር ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ነው። በሪፖርቱ በተጠቀሱት ወራት ሚኒስቴሩ በአጠቃላይ 282 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ይፋ አድርጓል።
ከእዚህ ገቢ ውስጥ 39.1 ቢሊዮን ብር ያህሉ የተገኘው፤ የንግድ ማጭበርበር እና ኮንትሮባንድን ለመከላከል በተደረገው ጥረት መሆኑ በሪፖርቱ ተጠቅሷል። የንግድ ማጭበርበርን በመከላከል ረገድ ከፍተኛው ገቢ የተሰበሰበው “ከመደበኛ ፍተሻ እና ሰነድ ምርመራ” መሆኑን የገለጸው ሚኒስቴሩ፤ በዚህም 25.2 ቢሊዮን ብር ገቢ መደረጉን አመልክቷል።
ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ እና ወደ ውጭ ሀገራት እንዲወጡ የሚደረጉ የኮንትሮባንድ ቁሳቁሶችን ለመከላከል በተደረገው የቁጥጥር ስራ፤ “ሀገር እና ህዝብ ሊያጣው የነበረ” ወደ አራት ቢሊዮን ብር ገደማ ሀብት ወደ ገቢ እንዲቀየር መደረጉ በሪፖርቱ ተብራርቷል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በመከላከል ስራው ከያዛቸው ቁሳቁሶች መካከል 3.5 ቢሊዮን ብር ግምት ያላቸው የገቢ ኮንትሮባንድ ዕቃዎች መሆናቸው ተገልጿል።
ከእነዚህ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙት፤ ኮንትሮባንድ ጭነው ወይም በኮንትሮባንድ ገብተው የተወረሱ ተሽከርካሪዎች እንዲሁም ምግብና መጠጥ ነክ ዕቃዎች ናቸው ተብሏል። በሪፖርቱ “እልህ አስጨራሽ” በሚል የተጠቀሰውን የኮንትሮባንድ መከላከል ስራ በዋነኛነት ያከናወነው ለገቢዎች ሚኒስቴር ተጠሪ የሆነው የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን መሆኑ ተጠቅሷል።
ጉምሩክ ኮሚሽን፤ ከአገር መከላከያ ሰራዊት፣ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች አመራሮችና የጸጥታ አካላት፣ ከሌሎች አጋር አካላት እና ከህዝብ ጋር በመተባበር ባከናወነው የኮንትሮባንድ መከላከል ስራ በርካታ ኮንትሮባንዲስቶችን በቁጥጥር ስር መዋል መቻሉ ተገልጿል። በኮንትሮባንድ ንግድ ከተጠረጠሩ 725 ግለሰቦች መካከልም 613 ያህሉ ባለፉት 10 ወራት በቁጥጥር ስር ውለው በምርመራ ሂደት ላይ መሆናቸውን ሪፖርቱ አስታውቋል።
የገቢዎች ሚኒስቴር ሪፖርት፤ ባለፉት 10 ወራት በኮንትሮባንዲስቶች በደረሰ ጥቃት ከስድስት ግለሰቦች በላይ ህይወታቸው ማለፉን እና በበርካቶች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን አጽንኦት ሰጥቶ ቢጠቅስም፤ ዝርዝሩን ከመግለጽ ግን ተቆጥቧል። በገቢ አሰባሰብ ላይ ያተኮረው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሪፖርት በገቢዎች ሚኒስትሩ አቶ ላቀ አያሌው በንባብ ከቀረበ በኋላ፤ የተወካዮች ምክር ቤት ፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያዘጋጃቸውን ጥያቄዎች በተከታታይ ቀርበው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።
ጥያቄዎቹን በንባብ ያሰሙት የቋሚ ኮሚቴ አባሉ አቶ ደበበ አድማሱ፤ ከኮንትሮባንድ ጋር የተያያዙ እና “በመስክ ምልከታ የተረጋገጡ” ያሏቸውን “ችግሮች” ጠቅሰው መስሪያ ቤቱ እነዚህን ለማሻሻል ምን እየሰራ እንደሆነ ጠይቀዋል። አቶ ደበበ ያነሱት የመጀመሪያ ችግር “ለቁጥጥር የሚመደቡ ተሽከርካሪዎች ኮንትሮባንዲስቶቹ ከሚጠቀሙባቸው አንጻር አሮጌ እና በቁጥርም አነስተኛ መሆናቸውን” ነው።
የገቢዎች ሚኒስትሩ አቶ ላቀ አያሌው በምላሻቸው “የእኛ አቅምና የኮንትሮባንዲስቶቹ አቅም የተመጣጠነ አይደለም። ከተሽከርካሪ ይጀምራል። እነሱ የሚይዙት ተሽከርካሪ ጥሶ ለመሄድ ሁሉ የሚያስችል ነው” ሲሉ ችግሩ መኖሩን አምነዋል። የኢትዮጵያ የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቀበታም ይህንኑ የሚደገፍ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
“ኮንትሮባንዲስቶቹ የሚጠቀሙባቸው ተሽከርካሪዎች እና እቃዎች በጣም ዘመናዊ ናቸው። አደረጃጀታቸውም፣ የታጠቁትም ከወትሮ ጥንት ከምናውቀው በላይ ነው። የእኛን ኃይልም ጭምር የሚገዳደር ነው” ሲሉ ኮሚሽነሩ የሚኒስትሩን ሃሳብ ተጋርተዋል። “የሚያስፈልጉን ቴክኖሎጂዎች አሉ፤ የሚያስፈልጉን ተሽከርካሪዎች አሉ። እነዚህን ለይተን ገንዘብ ሚኒስቴር ውሳኔ ሰጥቶ እንዲያሟላልን በቅርበት እየተከታተልን ነው” ሲሉም ችግሩን ለመቅረፍ በመስሪያ ቤታቸው በኩል የተደረገውን ጥረት ገልጸዋል።
የተወካዮች ምክር ቤት ፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባሉ አቶ ደበበ በቀጣይነት ያነሱት ጥያቄ የጉምሩክ ተቆጣጣሪዎችን የተመለከተ ነው። “ከኮንትሮባንዲስቶች ጋር የሚደራደሩ ተቆጣጣሪዎች አሉ” ያሉት የቋሚ ኮሚቴ አባሉ፤ እነዚህን የጉምሩክ ሰራተኞች በተመለከተ መስሪያ ቤቱ ምን እያደረገ እንደሆነ ጥያቄ አቅርበዋል።
ችግሩ መኖሩን የተቀበሉት የጉምሩክ ኮሚሽነሩ አቶ ደበሌ ቀበታ “አንዳንዴ በመንግስት መኪና ጭምር፣ የቀይ መስቀል መኪናዎችም ጭምር የጸጥታ አካላት ተሽከርካሪዎችንም አልፎ አልፎ በመጠቀም እነዚህን የኮንትሮባንድ እቃዎች በማመላለስ በኩል ድርሻ ያላቸው አካላት አሉ” ሲሉ ለፓርላማ አባላት ተናግረዋል። “ትግሉ፤ ወጪ እና ገቢ ኮንትሮባንዱ ላይ የተሰለፉ ኮንትሮባንዲስቶች ላይ ብቻ የሚደረግ ትግል አይደለም፤ በውስጥም ነው” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የገቢዎች ሚኒስቴር ለፓርላማ ባቀረበው የ10 ወራት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ላይም ተመሳሳይ ሀሳብ አንጸባርቋል። “አንዳንድ የንግድ ማጭበርበርና የኮንትሮባንድ ተግባሮች እጅግ በጣም ውስብስብና ፈታኝ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ስውርና ረጃጅም እጆች እንዳሉበት” እንደሚያምን በሪፖርቱ የገለጸው ሚኒስቴሩ፤ ከተቋሙ ውጭ የሆኑ ሌሎች መስሪያ ቤቶችን እና አመራሮችን ድጋፍ እንደሚፈልግ አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ በዚሁ ሪፖርቱ፤ ኮንትሮባንድ “የሽብር ቡድኖችን የገንዘብ ምንጭ በመሆን አገርን የማተራመስ ሚና ይጫወታል” ሲልም ህገ ወጡ የንግድ ሂደት በፖለቲካ ላይ ጭምር ያለውን ተጽዕኖ አጎልቶ አሳይቷል። ኮንትሮባንድ “የህዝቦች የእርስ በእርስ ግጭት እና የፖለቲካዊ አረመረጋጋት” ምክንያት እንደሚሆን ሪፖርቱ ቢጠቀስም፤ በዚህ አኳያ በኢትዮጵያ የተከሰቱ ክስተቶች የትኞቹ እንደሆኑ ግን ሳያብራራ አልፎታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)