በተስፋለም ወልደየስ
አሜሪካ፤ አምባሳደር ማይክ ሐመርን ለአፍሪካ ቀንድ አዲስ ልዩ መልዕክተኛ አድርጋ መሾሟን አስታወቀች። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ዛሬ ረቡዕ እንዳስታወቁት፤ አዲሱ ተሿሚ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛነት ሚናቸውን በቅርቡ የሚያስረክቡትን ዴቪድ ሳተርፊልድን ይተካሉ።
በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና በቺሊ በአሜሪካ አምባሳደርነት ያገለገሉት ማይክ ሐመር፤ አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ለምታከናውናቸው ጥረቶች “ያልተቆጠበ ጉልበት እና ራዕያቸውን” ይለግሳሉ የሚል እምነት እንዳላቸው አንቶኒ ብሊንከን ገልጸዋል። “የአምባሳደር ማይክ ሐመር ሹመት፤ በቀጠናው ለምናደርገው ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ያለንን ዘላቂ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው” ብለዋል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ።
የልዩ መልዕክተኛው መሾም፤ አሜሪካ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ አንገብጋቢ ለምትለውና ድጋፍ ለምትሰጠው “ሁሉን አካታች የፖለቲካ ሂደት” አስተዋጽኦ እንዳለውም ብሊንከን ዛሬ ረቡዕ ግንቦት 24 ባወጡት መግለጫ ጠቁመዋል። “ይህ [የአሜሪካ] አስተዳደር፤ ግጭቶች እንዲቆሙ፣ ያልተገደቡ የሰብዓዊ ድጋፎች ተደራሽ እንዲሆኑ፣ በተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ውስጥ ተሳታፊ በሆኑ ሁሉም አካላት ላይ ግልጽ ምርመራዎች እንዲደረጉ እና በድርድር ለግጭቱ መፍትሔ እንዲመጣ በከፍተኛ ሁኔታ ትኩረት ማድረጉን ይቀጥላል” ሲሉም የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ የሚከተለውን አቋም አስገንዘበዋል።
አሜሪካ በኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ያለውን ጦርነት ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ አሳሳቢ ላለቻቸው ወቅታዊ ችግሮች መፍትሔ የማፈላለግ ኃላፊነት የተጣለባቸው ልዩ መልዕክተኛ ለመጀመሪያ ጊዜ የሾመችው በሚያዝያ 2013 ነበር። ሀገሪቱ ለአፍሪቃ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛነት በወቅቱ የሾመቻቸው፤ በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በከፍተኛ ኃላፊነት የሰሩትን የ62 አመቱ ጄፍሪ ፌልትማንን ነው።
ጄፍሪ ፌልትማን በኢትዮጵያ እና ሱዳን ላሉ ፖለቲካዊ ቀውሶች መፍትሔ ለማበጀት ተደጋጋሚ ጥረቶችን ሲያደርጉ ከቆዩ በኋላ ባለፈው ታህሳስ ወር ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸው ይታወሳል። እርሳቸውን ተክተው የልዩ መልዕክተኛነት ኃላፊነቱን የተረከቡት በቱርክ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ዴቪድ ሳተርፊልድ በቦታው ላይ እምብዛም አልቆዩም።
ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ከተሾሙ በኋላ ከአንድም ሁለት ሶስት ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የተመላለሱት አምባሳደር ሳተርፊልድ፤ ከኃላፊነታቸው እንደሚለቅቁ የተነገረው ባለፈው ሚያዝያ ወር ላይ ነበር። የአምባሳደር ሳተርፊልድ ተተኪ መሆናቸው ዛሬ ይፋ የተደረገው አምባሳደር ማይክ ሃመር በአፍሪካ አህጉር የስራ ልምድ ያላቸው ናቸው።
በላቲን አሜሪካ ያደጉት እና በቺሊ፣ ቦሊቪያ፣ ኖርዌይ፣ አይስላንድ፣ ዴንማርክ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች የሰሩት ማይክ ሐመር፤ በአፍሪካ አህጉር ተመድበው በአምባሳደርነት ለመጀመሪያ ጊዜ ያገለገሉት በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ነው። ወደ ኮንጎ ኪንሻሳ በመስከረም 2011 ያቀኑት አምባሳደር ሐመር፤ እስካለፈው እሁድ ድረስ በስራቸው ላይ እንደነበሩ በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ላይ ካጋሯቸው ምስሎች መመልከት ተችሏል።
አምባሳደሩ በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በነበራቸው ቆይታ “ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ” እንደነበሩ ስለ እርሳቸው የተጻፉ ጽሁፎች ያወሳሉ። በዲፕሎማሲው ዘርፍ እምብዛም ባልተለመደ መልኩ፤ በሀገሪቱ ስላለው ፖለቲካዊ ችግር “በግልጽ አስተያየቶችን የሚሰጡ” እንደነበሩ ባሮንስ በተሰኘ እውቅ የአሜሪካ ሳምንታዊ መጽሔት የታተመ አንድ ጹሁፍ አስነብቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደሩ” ዘላለም ደምሴ ለዚህ ዘገባ አስተዋጽኦ አድርጓል]