የደቡብ ክልል የፓርላማ ተወካዮች ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጋር ሊወያዩ ነው

በሃሚድ አወል

የደቡብ ክልል ተወካይ የሆኑ የፓርላማ አባላት ከክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ እርስቱ ይርዳ ጋር ሊወያዩ ነው። በሚቀጥለው ሳምንት በሐዋሳ ከተማ ይካሄዳል በተባለው በዚህ ውይይት፤ ክልሉን ለሁለት የሚከፍለው የአደረጃጀት ጉዳይ “አበይት አጀንዳ” ሆኖ እንደሚነሳ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች ገልጸዋል።

በ11 ዞኖች እና ስድስት ልዩ ወረዳዎች የተዋቀረው የደቡብ ክልል፤ በፌደራል ፓርላማ 84 ተወካዮች አሉት። ከእነዚህ ውስጥ ሰባቱ የተቃዋሚ ፓርቲ ተመራጮች ሲሆኑ ቀሪ ሰባ ሰባቱ የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ተወካዮች ናቸው። የቀጣይ ሳምንቱ ውይይት የተጠራው፤ ባለፈው ሳምንት መደበኛ ስብሰባውን ባካሄደው በደቡብ ክልል ምክር ቤት በኩል መሆኑን ክልሉን የወከሉ የፓርላማ አባላት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

የክልሉ ምክር ቤት ለፓርላማ አባላቱ ጥሪ ያስተላለፈው፤ ተወካዮቹ ባለፈው የካቲት ወር ወደ ተመረጡባቸው የምርጫ ክልሎች ተጉዘው ከህብረተሰቡ ጋር ባደረጓቸው ውይይቶች ላይ የተነሱ ጥያቄዎችን በተመለከተ ለመወያየት በሚል ነው። የቀጣዩ ሳምንት ውይይት ዋነኛ አጀንዳ ይህ ነው ቢባልም፤ በደቡብ ክልል በተደጋጋሚ የሚቀርቡት በክልል የመደራጀት እንደዚሁም የዞን እና ልዩ ወረዳ መዋቅር ጥያቄዎች ከፍተኛ መነጋገሪያ እንደሚሆኑ የፓርላማ አባላቱ ገልጸዋል።

ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ አንድ የፓርላማ አባል፤ የአደረጃጀት ጥያቄ “በጣም ወሳኝ ስለሆነ፤ በዛ ላይ ህዝቡ የሚያነሳቸው ነገሮች ስላሉ፤ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ለእኛ እንደ ማብራሪያ የሚያቀርበው ነገር ይኖራል። እኛም የምናነሳቸው ጥያቄዎች ይኖራሉ” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። አንድ ሌላ የፓርላማ አባልም፤ በክልሉ የተነሱ የመዋቅር ጥያቄዎች የውይይቱ “ዋና አጀንዳ” ሊሆኑ እንደሚችሉ በተመሳሳይ ግምታቸውን አስቀምጠዋል። 

በደቡብ ክልል ያሉ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ምክር ቤቶች ትላንት ቅዳሜ ሐምሌ 23 እና ዛሬ እሁድ ሐምሌ 24 ባካሄዷቸው ጉባኤዎች፤ በሁለት የተለያዩ ክልሎች ለመደራጀት የቀረበላቸውን የውሳኔ ሃሳብ አጽድቀዋል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የደቡብ ክልል የፓርላማ ተወካይ፤ “ክልል ሲጠይቁ የነበሩ [ዞኖች] አሉ። ‘ይሄ አደረጃጀት እኛ በፈለግነው አቅጣጫ አይደለም’ የሚሉ አሉ እና ብዙ ነገር ይነሳል። የዞን እና ልዩ ወረዳ ምክር ቤቶች ውሳኔ ትልቁ ጉዳይ ነው ብዬ አስባለሁ” ሲሉ ከቀጣዩ ሳምንት ውይይት የሚጠበቀውን አመልክተዋል።

አዲስ ከሚመሰረቱት ክልሎች አንደኛውን ለመቀላቀል፤ ትላንት ቅዳሜ ሐምሌ 23፤ 2014 ባካሄዱት የየምክር ቤቶቻቸው ጉባኤ ውሳኔ ያሳለፉት የወላይታ፣ ጌዲኦ፣ ጋሞ፣ የደቡብ ኦሞ እና ኮንሶ ዞኖች ናቸው። የአማሮ፣ ባስኬቶ፣ ቡርጂ፣ እና አሌ ልዩ ወረዳዎችም ተመሳሳይ ውሳኔ በትላንትናው ዕለት በምክር ቤቶቻቸው አጽድቀዋል። 

ዛሬ እሁድ ሐምሌ 24 ጉባኤውን ያካሄደው የጎፋ ዞን ምክር ቤት፤ በዚሁ አዲስ ክልል ለመካተት መወሰኑን አስታውቋል። ጉባኤውን ነገ ሰኞ ሐምሌ 25 የሚያካሄደው የደራሼ ልዩ ወረዳ አዲሱን የክልል አደረጃጀት የሚያጸድቅ ከሆነ በስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች የሚደራጀውን አዲስ ክልል በመቀላቀል የመጨረሻ ይሆናል። 

ሁለተኛውን ክልል ይመሰረታሉ ከተባሉ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ውስጥም አብዛኞቹ በየምክር ቤቶቻቸው ተመሳሳይ ውሳኔ አሳልፈዋል። የሀድያ፣ ሀላባ እና ከምባታ ጠምባሮ ዞኖች እንዲሁም የየም ልዩ ወረዳ ምክር ቤቶች ትላንት ቅዳሜ ሐምሌ 23 ባካሄዱት ጉባኤ አንድ የጋራ ክልል ለመመስረት ወስነዋል። የስልጤ ዞን ምክር ቤት ዛሬ እሁድ ባካሄደው ጉባኤ የአዲሱ ክልል አካል የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ አጽድቋል። 

በዚህ ክልል ይካተታል ተብሎ የሚጠበቀው የጉራጌ ዞን ዕጣ ፈንታ ግን ገና በግልጽ አልታወቀም። የጉራጌ ዞን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አርሺያ አህመድ የዞኑ ምክር ቤት ጉባኤውን የሚያካሄድበት ቀን እስካሁን አለመወሰኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የደቡብ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ፤ የጉራጌ ዞን ራሱን ችሎ ክልል እንዲሆን ከዚህ ቀደም በዞኑ መክር ቤት የጸደቀው የውሳኔ ሃሳብ ተግባራዊ እንዲደረግ የሚጠይቁ ጠንከር ያሉ ድምጾች ተደምጠዋል። 

በክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ ላይ የቀረቡትን እነዚህን ጥያቄዎች የጉራጌ ዞንን የወከሉ የገዢው ብልጽግና እና የተቃዋሚው ኢዜማ ፓርቲ አባላት ያለ ልዩነት ሲያንጸባርቁ ታይተዋል። ከጉራጌ ዞን የተመረጡት የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳ ለክልሉ ምክር ቤቱ አባላት በወቅቱ በሰጡት ምላሽ፤ የክልልነት እና የመዋቅር ጥያቄ ሊፈታ የሚገባው “በውይይት” እንጂ “ጡዘት ውስጥ በመግባት” እንዳልሆነ ተናግረው ነበር። 

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በዚሁ ጉባኤ ላይ፤ በደቡብ ክልል በተደጋጋሚ እና በየጊዜው የሚነሳውን የክልልነት ጥያቄ “የመጨረሻ ውሳኔ” ለመስጠት የሚያስችል ሰነድ በገዢው የብልጽግና ፓርቲ ተዘጋጅቶ ውይይት እየተደረገበት መሆኑን ማስታወቃቸው አይዘነጋም። የደቡብ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋጤ ስርሞሎም፤ የክልሉ ምክር ቤት ከአደረጃጀት ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ጥያቄዎች የሚጠበቅበትን ተግባር ሁሉ “በህግ አግባብ” እንደሚያከናውን በወቅቱ ተናግረው ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)