በሃሚድ አወል
የ“ፍትሕ” መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በዐቃቤ ህግ የቀረበበትን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸሙን በመግለጽ የእምነት ክህደት ቃሉን ለፍርድ ቤት ሰጠ። ጋዜጠኛው ለተወነጀለባቸው ሶስት ተደራራቢ ክሶች በጠበቃው በኩል ያቀረበው የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ በፍርድ ቤት ውድቅ ተደርጎበታል።
የተመስገን ደሳለኝን ጉዳይ እየተመለከተ የሚገኘው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ችሎት ለዛሬ ማክሰኞ ሐምሌ 26፤ 2014 ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው፤ ለፌደራል ዐቃቤ ህግ ክሶች የተከሳሽ ጠበቃ ያቀረቡትን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ መርምሮ ብይን ለመስጠት ነበር። የጋዜጠኛው ጠበቃ አቶ ሔኖክ አክሊሉ የይርጋ የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያቸውን ለችሎቱ በጽሁፍ ያስገቡት ከሁለት ሳምንት በፊት ሐምሌ 11፤ 2014 ነበር።
ጠበቃ ሔኖክ በዚሁ የክስ መቃወሚያቸው፤ በደንበኛቸው ላይ የቀረቡት ክሶች ተመስገን በ“ፍትሕ” መጽሔት ላይ በጻፋቸው እና ሌሎች ሰዎች በመጽሔቱ ላይ ያሳተሟቸውን ጽሁፎች ላይ የተመሰረቱ መሆናቸውን አንሰተዋል። ስለሆነም ጉዳዩ በመገናኛ ብዙሃን አዋጁ መሰረት ሊታይ ይገባል ብለዋል። የመገናኛ ብዙሃን አዋጁ፤ ደንበኛቸው በተከሰሱባቸው የወንጀል ድርጊቶች ላይ የተጠያቂነት ገደብ እንደሚያስቀምጥ በመጥቀስም የይርጋ መከራከሪያቸውን አቅርበዋል።
ባለፈው ዓመት በፓርላማ የጸደቀው የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ አንቀጽ 87 “በየጊዜው በሚወጣ ህትመት አማካኝነት የሚፈጸም የወንጀል ጥፋት፤ ህትመቱ ከተሰራጨበት ወይም ከተላለፈበት ቀን አንስቶ እስከ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ክሱ ካልቀረበ በይርጋ ቀሪ ይሆናል” ሲል ይደነግጋል። በዚህም መሰረት በጋዜጠኛ ተመስገን ላይ በቀረቡት ክሶች ላይ የተካተቱ እና ከጥር 2011 እስከ የካቲት 2012 ዓ.ም. በተለያዩ የ“ፍትሕ” መጽሔት ቅጾች ላይ ታትመው የወጡ አስር ጽሁፎች ውድቅ እንዲደረጉ የተከሳሹ ጠበቃ ጠይቀዋል።
“እነዚህ ህትመቶች በህጉ በተቀመጠው መሰረት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ክስ ያልቀረበባቸው ስለሆነ፤ አሁን ይህ የህግ ጊዜ ካለፈ በኋላ ሊቀርቡ ስለማይችሉ ከክሱ ውስጥ ውድቅ እንዲደረግልኝ መቃወሚዬን አቀርባለሁ” ሲሉ አቶ ሔኖክ በይርጋ የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያቸው አመልክተው ነበር። በጋዜጠኛ ተመስገን ላይ በተመሰረቱበት ሶስት ክሶች ላይ በ“ፍትሕ” መጽሔት የወጡ እና በዐቃቤ ህግ በማስረጃነት የቀረቡ ጽሁፎች ብዛት 17 ነው።
ጋዜጠኛው “ወታደራዊ ምስጢርን መግለጽ” በተመለከተ የተደነገገውን የወንጀል ህግ ተላልፏል በሚል በቀረበበት የመጀመሪያ ክስ ላይ በማስረጃነት የቀረቡት አራት ጽሁፎች ናቸው። በ“ፍትሕ” መጽሔት ላይ የታተሙ አምስት ጽሁፎች፤ ተመስገን “የሐሰት ወይም የሚያደናግር መረጃ አሰራጭቷል” በሚል ለተመሰረተበት ሁለተኛ ክስ በማስረጃነት ቀርበዋል። በጋዜጠኛው ላይ ለቀረበው “መገፋፋትና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት የወንጀል ተግባር መፈጸም” ለሚለው ሶስተኛ እና የመጨረሻ ክስ በማስረጃነት የቀረቡ የ“ፍትሕ” መጽሔት ጽሁፎች ብዛት ደግሞ ስምንት ነው።
ጽሁፎቹን በተመለከተ በተከሳሽ ጠበቃ በኩል ለቀረበው መቃወሚያ ዐቃቤ ህግ በጽሁፍ ባቀረበው ምላሽ “ክሱ በመደበኛ የወንጀል ህግ የቀረበ እንጂ በመገናኛ ብዙሃን ህግ የቀረበ አይደለም” ሲል ጉዳዩ በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ሊታይ አይገባውም ሲል ተከራክሯል። የግራ ቀኙን መከራከሪያ የመረመረው ችሎቱ፤ ጉዳዩ “በመደበኛ ህጉ ነው መታየት ያለበት” የሚለውን የዐቃቤ ህግ መከራከሪያ ሳይቀበለው ቀርቷል።
ሆኖም ፍርድ ቤቱ “የይርጋ ጊዜው እንዴት ይቆጠራል?” የሚለው ጥያቄ በመገናኛ ብዙሃን አዋጁ አለመቀመጡን በማንሳት፤ የይርጋ ጊዜውን ለማስላት የወንጀል ህጉን ማጣቀስ መርጧል። በወንጀል ህጉ ላይ “ተከታታይ የወንጀል ድርጊት የተፈጸመ እንደሆነ የይርጋ ጊዜው የሚቆጠረው የመጨረሻው ደርጊት ከቆመበት ጊዜ ጀምሮ ስለመሆኑ” መደንጉን ችሎቱ ገልጿል። ጋዜጠኛው ፈጸማቸው የተባሉት የወንጀል ድርጊቶች እስከ ግንቦት 2014 ዓመት ድረስ መፈጸማቸው በዐቃቤ ህግ መጠቀሱን ያስታወሰው ችሎቱ፤ “ድርጊቱ አንድ ዓመት ስላልሞላው” የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያውን አለመቀበሉን አስታውቋል።
በዛሬው የችሎት ውሎው የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጠበቃ ያቀረቡትን የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ ውድቅ ያደረገው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ የተከሳሽን የእምነት ክህደት ቃል ተቀብሏል። ተመስገን በ “ፍትሕ” መጽሔት ላይ የታተሙትን ጽሁፎቹን መጻፉን አምኖ “ወንጀል ግን አልፈጸምኩም” ሲል ለችሎቱ ቃሉን ሰጥቷል።
ጋዜጠኛ ተመስገን “ወንጀሉን አልፈጸምኩም” ማለቱን ተከትሎ ዐቃቤ ህግ ከክሱ ጋር አያይዞ ያቀረባቸው የሰነድ ማስረጃዎች በችሎቱ እንዲመዘኑለት ጥያቄ አቅርቧል። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የፀረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ችሎት፤ የዐቃቤ ህግ ማስረጃዎችን እና ጠበቃው በማስረጃዎቹ ላይ የሚያቀርቡትን አስተያየት መርምሮ ብይን ለመስጠት ለነሐሴ 19፤ 2014 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። የተከሳሽ ጠበቃ በማስረጃዎቹ ላይ አስተያየታቸውን እስከ ነሐሴ 4፤ 2014 በጽህፈት ቤት በኩል እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ በመስጠት ችሎቱ የዛሬ ውሎውን አጠናቅቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)