በሃሚድ አወል
የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተሾሙት የጠበቆች አስተዳደር ቦርድ አባላት ስብጥር ላይ ቅሬታውን አሰማ። ማህበሩ ቅሬታውን የገለጸው፤ የፍትሕ ሚኒስቴር ለጠበቆች አስተዳደር ቦርድ በአባልነት የተሾሙ ግለሰቦችን ዝርዝር ባለፈው ቅዳሜ ሐምሌ 23፤ 2014 ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ነው።
በፍትሕ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ አቅራቢነት የተሾሙት የጠበቆች አስተዳደር ቦርድ አባላት የተውጣጡት ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከጠበቆች ማህበር፣ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው። ከጥብቅና ሙያ እና ከጠበቆች ማህበር ጋር የተያያዙ ውሳኔዎችን የመወሰን ስልጣን በአዋጅ የተሰጠውን ይህንን ቦርድ በሰብሳቢነት እንዲመሩ የተመረጡት በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግስት ህግ እና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት አቶ አለምአንተ አግደው ናቸው።

ለጠበቆች አስተዳደር ቦርድ በአባልነት የተሾሙት ሁሉም ግለሰቦች ወንዶች መሆናቸው፤ ሹመቱ “ሁሉን አካታች አይደለም” የሚል ቅሬታ ቀስቅሷል። የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ዛሬ ማክሰኞ ሐምሌ 26፤ 2014 ባወጣው መግለጫ “የተደረገው ሹመት የሴቶች እና አካል ጉዳተኞችን ባለመካተት የስርዓተ ጾታ ሚዛን፣ አካታችነት እና የእኩልነት መርህን የጣሰ መሆኑን ተረድተናል” ሲል ቅሬታውን አስታውቋል።
የቦርድ አባላቱ የተውጣጡባቸው ተቋማት ተወካዮችን ሲልኩ “አካታችነትን ከግምት ባስገባ መልኩ ይሆን ዘንድ እንጠይቃለን” ያለው ማህበሩ፤ ይህንንም ለማሳካት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጥያቄ አቅርቧል። “የቦርዱ አባላት 50 በመቶ ብቃት ያላቸው ሴቶች እንዲሆኑ፤ በተደረገው ሹመት ላይ ማስተካከያ ተደርጎ የሴቶችን እኩልነት በተጨባጭ ለማረጋገጥ ይቻል ዘንድ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የበኩሉን ጥረት እንዲያደርግ እንጠይቃለን” ሲል የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር በመግለጫው አሳስቧል።
ለፌደራል ጠበቆች አስተዳደር ቦርድ በአባልነት የተመረጡ ግለሰቦች የስራ ዘመን ሶስት ዓመት እንደሚሆን በ2013 ዓ.ም. በጸደቀው የፌደራል ጥብቅና አገልግሎት ፍቃድ አሰጣጥ እና አስተዳደር አዋጅ ላይ ተደንጓል። በአዋጁ መሰረት የተቋቋሙት የጠበቆች ዲስፕሊን ጉባኤ፣ የጥብቅና መግቢያ ፈተና ኮሚቴ እና የጥብቅና ፍቃድ ገምጋሚ ኮሚቴ ተጠሪ የሚሆኑት ለዚሁ ቦርድ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)