የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ወደ ተኩስ አቁም ስምምነት የሚያመራ ሰነድ በፌደራል መንግስት መዘጋጀቱ ተገለጸ

በሃሚድ አወል

ለሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የተኩስ አቁም ስምምነት ሊያመጣ የሚችል የሰላም ምክረ ሀሳብ በፌደራል መንግስት በኩል መዘጋጀቱ ይፋ ተደረገ። የሰላም ምክረ ሃሳቡን የያዘውን ሰነድ ያዘጋጀው፤ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተቋቋመው የሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ መሆኑ ተገልጿል። 

አብይ ኮሚቴው በመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት በኩል ዛሬ ረቡዕ ነሐሴ 11፤ 2014 ባወጣው መግለጫ፤ የሰላም ምክረ ሃሳቡ “በተቻለ ፍጥነት ለአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ ወኪል እንዲቀርብ” ውሳኔ መተላለፉን አስታውቋል። ኮሚቴው አክሎም የሰላም ንግግሩ “በአስቸኳይ ተጀምሮ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስ ይቻል ዘንድ” ከአፍሪካ ህብረት ጋር በቅርበት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አመልክቷል።

እነዚህ ስራዎች “የሰላም ንግግሩ የሚካሄድበትን ቦታ እና ጊዜ በፍጥነት ወስኖ ንግግሩ እንዲጀመር” የሚያስችሉ መሆናቸውን የአብይ ኮሚቴው መግለጫ ጠቅሷል። የአፍሪካ ህብረትን የሰላም ጥረት በሚደግፉ አካላት በመታገዝ በአጭር ጊዜ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ይቻል ዘንድም፤ ጉዳዩ ለዓለም አቀፍ ማህብረሰብ ለማስረዳት በታቀደው መሰረት በዛሬው ዕለት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማብራሪያ ተሰጥቷል ተብሏል። 

ማብራሪያውን የሰጠው የሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ የተቋቋመው ከ50 ቀናት ገደማ በፊት ባለፈው ሰኔ 20፤ 2014 ሲሆን፤ ስራውን በይፋ የጀመረው ደግሞ ከአንድ ወር ገደማ በፊት ነበር። በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በሚመራው እና  ሰባት አባላት ባሉት በዚህ ኮሚቴ ውስጥ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን፣ የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዮስ እንዲሁም የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተሩ አቶ ተመስገን ጥሩነህ ተካትተዋል።  

የሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴው በቅርቡ ባደረገው ውይይት፤ በትግራይ ክልል “መሰረታዊ አገልግሎቶችን በተቻለ ፍጥነት መልሶ ማቅረብ ይቻል ዘንድ አስፈላጊ ቅደም ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን” መገምገሙን አስታውቋል። በክልሉ መሰረታዊ አገልግሎቶቹን ማቅረብ የሚጀመረው፤ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ተከትሎ “በሚፈጠረው አስቻይ ሁኔታ” እንደሆነም በዛሬው የኮሚቴው መግለጫ ላይ ሰፍሯል።  

የፌደራል መንግስት ካለፈው መጋቢት አጋማሽ ጀምሮ “ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት ለማቆም ስለመወሰኑ” ቢያስታውቅም፤ የትግራይ ክልልን ከሚያስተዳድረው ህወሓት ጋር ይፋዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ገና አልደረሰም። ከአምስት ወር በፊት የተላለፈው “የግጭት ማቆም ውሳኔ” በፌደራል መንግስት በኩል “ለሰላም እድል ለመስጠት” ከተደረጉ “ተደጋጋሚ ሙከራዎች” መካከል የሚጠቀስ መሆኑ በዛሬው መግለጫ ላይ ተወስቷል። 

በዚህ ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ታውጆ ለአራት ወራት የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳት እና የእስረኞች ፍቺ፤ የፌደራል መንግስት “ለሰላም ዕድል ለመስጠት” ሲል ከወሰዳቸው እርምጃዎች መካከል የሚመደቡ መሆኑን የሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴው አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)