የዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ዎሕዴግ) በወላይታ ዞን ህዝበ ውሳኔ እንዲደረግ ጠየቀ

የዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ዎሕዴግ)፤ በ“ክላስተር” መደራጀትን በተመለከተ የወላይታ ዞን ምክር ቤት  ያስተላለፈው ውሳኔ ታርሞ “በአስቸኳይ ህዝበ ውሳኔ እንዲደረግ” ጠየቀ። ዎሕዴግ የዞኑ ምክር ቤት ያሳለፈው ውሳኔ “ከህዝብ ፍላጎት ውጪ በድብቅ” የተላለፈ ነው ሲል ተችቶታል። 

ክልላዊ ፓርቲው ዎሕዴግ፤ በወላይታ ዞን ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ የጠየቀው ትላንት ሰኞ ነሐሴ 9፤ 2014 ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በጻፈው ደብዳቤ ነው። ፓርቲው በዚሁ ደብዳቤው፤ ወላይታ ዞንን ከሌሎች ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ጋር በ“ክላስተር” ለማደራጀት በዞኑ ምክር ቤት የተወሰነው ውሳኔ “የህዝብ ፈቃድ እና ስምምነት ሳያገኝ” የተላለፈ መሆኑን ገልጾ፤ በዚህ ምትክ ህዝበ ውሳኔ እንዲደረግ ጠይቋል።  

የደቡብ ክልልን ለሁለት የሚከፍለውን የ“ክላስተር” አደረጃጀት የወላይታ ዞን ምክር ቤት ያጸደቀው ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት ባለፈው ሐምሌ 23፤ 2014 ነበር። የዞኑ ምክር ቤት ባጸደቀው በዚህ ውሳኔ መሰረት፤ የወላይታ ዞን ከጋሞ፣ ጎፋ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ኮንሶ እና ጌዲኦ ዞኖች እንዲሁም ከባስኬቶ፣ ደራሼ፣ አሌ፣ ቡርጂ እና አማሮ ልዩ ወረዳዎች ጋር በመሆን አንድ አዲስ ክልል ይመሰርታል።

ፎቶ፦ የወላይታ ዞን የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ

ተቃዋሚው ዎሕዴግ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በጻፈው ደብዳቤ፤ በገዢው ብልጽግና ፓርቲ የቀረበውን የ“ክላስተር” አደረጃጀት “ኢ-ህገ መንግስታዊ” ሲል ጠርቶታል። የክላስተር አደረጃጀትን “ህዝቡ በድምጽ ያላረጋገጠው ነው” ያለው ግንባሩ፤ የፌደሬሽን ምክር ቤት ይህንኑ ተገንዝቦ “ህዝበ ውሳኔ እንዲያደራጅ” ጥያቄውን አቅርቧል።  

የወላይታ ብሔር ብቻውን ክልል የመመስረት አማራጭን በህዝበ ውሳኔ መለየት “ህገ መንግስታዊ አሠራር” መሆኑን ዎሕዴግ ገልጿል። ህዝበ ውሳኔ የማደራጀት ህገ መንግስታዊ አሠራር ከዚህ ቀደም ለሲዳማ አና ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች መተግበሩን የጠቀሰው ዎሕዴግ፤ ይህ አካሄድ የወላይታ ብሔር ላቀረበው ጥያቄም ተግባራዊ እንዲሆን የፌዴሬሽን ምክር ቤትን በደብዳቤው ጠይቋል። (በሃሚድ አወል- ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)