የፌዴሬሽን ምክር ቤት “ደቡብ ኢትዮጵያ” የተሰኘ አዲስ ክልል የሚመሰርት ህዝብ ውሳኔ እንዲካሄድ ወሰነ

በሃሚድ አወል

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በደቡብ ክልል የሚገኙ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች በጋራ አንድ ክልል ለመመስረት ያቀረቡትን ጥያቄ በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ። ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕዝበ ውሳኔውን በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ እንዲያደራጅም ውሳኔ አሳልፏል።

በደቡብ ክልል ስር ያሉት ቀሪ አምስት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ በነባሩ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አንድ ላይ እንደሚቀጥሉ ምክር ቤቱ አስታውቋል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔውን ያሳለፈው ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ 12፤ 2014 ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ ነው። የዛሬው ውሳኔ የጸደቀው በአምስት የምክር ቤት አባላት ድምጸ ተዐቅቦ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቋል።

አዲሱን “የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን” የሚመሰረቱት የወላይታ፣ የጋሞ፣ የጎፋ፣ የደቡብ ኦሞ፣ የጌዴኦ፣ የኮንሶ ዞኖች እንዲሁም የደራሼ፣ የአማሮ፣ የቡርጂ፣ የአሌ እና የባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች ናቸው። በነባሩ የደቡብ ክልል የሚቀጥሉት ደግሞ የሀድያ፣ ሀላባ፣ ከምባታና ጠምባሮ፣ ስልጤ፣ ጉራጌ ዞኖችና የም ልዩ ወረዳ መሆናቸው ተገልጿል።

በደቡብ ክልል የሚገኙ አስር ዞኖች እና ስድስት ልዩ ወረዳዎች፤ የደቡብ ክልልን ለሁለት የሚከፍለውን የ“ክላስተር” አደረጃጀት በየምክር ቤቶቻቸው ያጸደቁት የዛሬ ሶስት ሳምንት ገደማ ነበር። ምክር ቤቶቹ ውሳኔዎቻቸውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በይፋ ያስገቡ ከሁለት ሳምንት በፊት ሐምሌ 28፤ 2014 ነው። 

በደቡብ ክልል ካሉ መዋቅሮች ውስጥ የ“ክላስተር” አደረጃጀትን ሳይቀበል የቀረው የጉራጌ ዞን ብቻ ነው። የጉራጌ ዞን ምክር ቤት በአብላጫ ድምጽ ውድቅ ያደረገውን ይህን ውሳኔውን፤ ባለፈው ሰኞ ነሐሴ 9፤ 2014 ለፌደሬሽን ምክር ቤት አስገብቷል።  በዞኑ ስር የሚገኙ ስድስት ወረዳዎች እና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች፤ የ“ክላስተር” አደረጃጀትን በመደገፍ በየምክር ቤቶቻቸው ያጸደቋቸውን ውሳኔዎች በተመሳሳይ ቀን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ማስገባታቸው ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)