የጉራጌ ዞን አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ጀማል ከኃላፊነታቸው ተነሱ 

በሃሚድ አወል

የጉራጌ ዞን ምክር ቤት አቶ መሐመድ ጀማልን ከዞን አስተዳዳሪነት አንስቶ በምትካቸው አቶ ላጫ ጋሩማን አስተዳዳሪ አድርጎ ሾመ። የዞኑ ምክር ቤት አስተዳዳሪውን ያነሳው ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 14፤ 2015 ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ ነው።

በዛሬው አስቸኳይ ስብሰባ የአዲሱን አስተዳዳሪ ሹመት ለምክር ቤት ያቀረቡት፤ የጉራጌ ዞን የመንግስት ተጠሪ እና የብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ክፍሌ ለማ መሆናቸውን አንድ የዞኑ ምክር ቤት አባል “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። አቶ መሐመድ ጀማል ከኃላፊነታቸው የተነሱት “ባቀረቡት ጥያቄ እና የዞኑን ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ” መሆኑን አቶ ክፍሌ መናገራቸው እኚሁ  የምክር ቤቱ አባል ገልጸዋል።

አቶ ላጫ ጋሩማ የጉራጌ ዞን እንዲያስተዳድሩ ከመሾማቸው በፊት የደቡብ ክልል የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በመሆን እያገለገሉ ነበር | ፎቶ፦ የጉራጌ ዞን የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ

ተሰናባቹ የጉራጌ ዞን አስተዳዳሪ ወደ ኃላፊነት ቦታቸው የመጡት በ2011 ዓ.ም አጋማሽ ሲሆን ዞኑን ለአራት ዓመታት አስተዳድረዋል። የጉራጌ ዞን ከክልልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ ውጥረት ሰፍኖበት ቆይቷል። በደቡብ ክልል ውስጥ ካሉ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች መካከል በ“ክላስተር” የመደራጀትን ውሳኔ ሃሳብ ውድቅ ያደረገው የጉራጌ ዞን ብቻ ነው። 

የጉራጌ ዞን ምክር ቤት የደቡብ ክልልን ለሁለት የሚከፍለውን የ“ክላስተር” አደረጃጀት ውድቅ ካደረገ ከአንድ ወር በኋላ በዞኑ በቢሮ ኃላፊነት ሲያገለግሉ የቆዩ ስድስት አመራሮች ለእስር ተዳርገዋል። እነዚሁ የቢሮ ኃላፊዎች በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ፤ በአቶ መሐመድ ፊርማ ከስልጣናቸው መሰናበታቸው ይታወሳል። ስድስቱ የቢሮ ኃላፊዎች ከአንድ ወር እስር በኋላ ክስ ሳይመሰረትባቸው ተለቅቀዋል።

ዛሬ በተካሄደው የጉራጌ ዞን ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤ ከኃላፊነታቸው የተነሱት አቶ መሐመድ ጀማል በአካል ተገኝተው ሂደቱን ተከታትለዋል። በአስቸኳይ ጉባኤው ላይ ብቸኛው አስተያየት ሰጪ የነበሩት የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳ፤ ለአዲሱ ተሿሚ ድጋፋቸውን መስጠታቸውን ሶስት የምክር ቤት አባላት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ዛሬ በተካሄደው የጉራጌ ዞን ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤ ከኃላፊነታቸው የተነሱት አቶ መሐመድ ጀማል በአካል ተገኝተው ሂደቱን ተከታትለዋል | ፎቶ፦ የጉራጌ ዞን የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ

አቶ ርስቱ በድጋፍ አስተያየታቸው፤ አቶ ላጫ “ዞኑን በተረጋጋ ሁኔታ ለመምራት እና በልማት ወደፊት ለማስኬድ ትክክለኛ ሰው ናቸው” ማለታቸውን የምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል። ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አስተያያት በኋላ የጉራጌ ዞን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አርሽያ አህመድ “የተለየ አስተያየት የሚያቀርብ” እንዳለ ቢጠይቁም፤ የድጋፍም ሆነ የተቃውሞ አስተያየት አለመደመጡን ጉባኤውን የታደሙት ሶስቱ የምክር ቤት አባላት አስረድተዋል።

አፈ ጉባኤ አርሽያ የዞኑ ምክር ቤት አባላት ሹመቱን እንዲያጸድቁ በጠየቁበት ወቅት ዘጠኝ ድምጸ ተዐቅቦ መዝገቡን ሶስቱ አባላት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል። የጉራጌ ዞን የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ በፌስ ቡክ ባወጣው መረጃ የአዲሱ አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ሹመት በዘጠኝ ድምጸ ተዐቅቦ በአብላጫ ድምጽ መጽደቁን አረጋግጧል። 

አቶ ላጫ የጉራጌ ዞን እንዲያስተዳድሩ ከመሾማቸው በፊት የደቡብ ክልል የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በመሆን እያገለገሉ ነበር። የጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳን ወክለው የዞኑ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ላጫ፤ ከዚህ ቀደም የደቡብ ክልል ትራንስፖርት ቢሮን በኃላፊነት መርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[ይህ ዘገባ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]