በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት መካከል የሚደረገው የሰላም ንግግር ተጀመረ

በደቡብ አፍሪካ አስተናጋጅነት የሚካሄደው የኢትዮጵያ የፌደራል መንግስት እና የህወሓት የሰላም ንግግር ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 15፤ 2015 መጀመሩን የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ ቪንሰንት ማግዌንያ ተናገሩ። የሰላም ንግግሩ እስከ መጪው እሁድ ጥቅምት 20 እንደሚዘልቅ ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።

“ፕሬዝዳንት [ሲሪል] ራማፖሳ የደቡብ አፍሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት እና በትግራይ መካከል የሚካሔደውን በአፍሪካ ኅብረት የሚመራ የሰላም ንግግር እንድታስተናግድ በመመረጧ ክብር ተሰምቷቸዋል” ሲሉ ቃል አቀባዩ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፖሳ ደቡብ አፍሪካ የሰላም ንግግሩን እንድታስተናግድ ስትጋበዝ “ያለ ማቅማማት ተስማምተዋል” ያሉት ቪንሰንት ማግዌንያ፤ እንዲህ አይነት ንግግር አፍሪካ “ደህንነቷ የተረጋገጠ እና ግጭት የሌለበት አህጉር” እንድትሆን ከሚሻው የአገራቸው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ዓላማ ጋር የተስማማ እንደሆነ ገልጸዋል።

ቃል አቀባዩ “አውዳሚ” ላሉት የትግራይ ግጭት “ሰላማዊ እና ዘላቂ መፍትሔ ለማፈላለግ” የተጀመረው የሰላም ንግግር፤ በቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ አመቻችነት የሚካሄድ ነው። በሰላም ንግግሩ የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና የቀድሞዋ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ፑምዚ ለምላምቦ “በደጋፊነት” ይካፈላሉ።

“ደቡብ አፍሪካ ለአመቻቺው ቡድን መልካሙን ትመኛለች” ያሉት የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ቃል አቃባይ፤ የሰላም ንግግሩ “የእህት አገር ኢትዮጵያ ህዝቦችን ሁሉ ወደ ዘላቂ ሰላም የሚመራ ስኬታማ ውጤት” ያመጣል የሚል ተስፋቸውን ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)