በሃሚድ አወል
በትግራይ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ለሰራተኞቻቸው ደመወዝ ለመክፈል በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ አስታወቁ። የገንዘብ ሚኒስቴር ለሰራተኞች ውዝፍ ደመወዝ መክፈያ እና የአንድ ወር የስራ ማስኬጃ በጀት፤ ባለፈው አርብ መጋቢት 1፤ 2015 እንደፈቀደላቸው ዩኒቨርሲቲዎቹ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
ተጠሪነታቸው ለፌደራል ትምህርት ሚኒስቴር የሆኑ አራት ዩኒቨርስቲዎች በትግራይ ክልል ይገኛሉ። በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት የመማር ማስተማር አገልግሎታቸውን አቋርጠው የሚገኙት እነኚህ አራት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፤ የመቐለ፣ አክሱም፣ አዲግራት እና ራያ ዩኒቨርስቲዎች ናቸው።
“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የመቐለ፣ አክሱም እና ራያ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች፤ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት ላለፉት 20 ወራት በዩኒቨርሲቲዎቹ ለሚሰሩ ሰራተኞች ደመወዝ አለመከፈሉን ገልጸዋል። ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራር፤ የሰራተኞችን ውዝፍ ደመወዝ ጉዳይ ከገንዘብ ሚኒስቴር አመራሮች ጋር በነበራቸው ስብሰባ ወቅት ማንሳታቸውን ገልጸዋል።
በዚሁ ስብሰባ ላይ የሚኒስቴሩ ኃላፊዎች፤ “ ‘ሌላውን የሲቪል ሰርቪስ ሰራተኛም ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ መንግስት ውሳኔ የሚሰጥበት ይሆናል’ የሚል ምላሽ መስጠታቸውንም አስታውሰዋል። የዚሁ ስብሰባ ተሳታፊ የነበሩት የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕ/ር ገብረየሱስ ብርሃነ በበኩላቸው፤ “መንግስት በልዩ ሁኔታ የሚወስነው ውሳኔ እንዳለ ነው የተነገረን” ሲሉ የሰራተኞች ውዝፍ ደመወዝን በተመለከተ ጉዳዩ ከሚመለከተው የፌደራል ተቋም የቀረበውን መልስ ጠቅሰዋል።
የገንዘብ ሚኒስቴር ይህ ስብሰባ በተካሄደ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ባሳለፈው ውሳኔ፤ የዩኒቨርስቲዎቹ ሰራተኞች ደመወዝ እንዲከፈል በጀት መልቀቁ ታውቋል። የፌደራል ተቋማት ለሆኑት አራቱ ዩኒቨርስቲዎች ሰራተኞች የደመወዝ ክፍያ የሚሆን ገንዘብ መተላለፉን የገንዘብ ሚኒስቴር ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። “የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ገና ስላልተመሰረተ፤ ለክልሉ የተላከ ገንዘብ የለም” ሲሉም የሚኒስቴሩ ምንጮች አክለዋል።
በትግራይ ክልል የሚገኙት አራት ዩኒቨርሲቲዎች ለሰራተኞቻቸው የሚከፍሉት ውዝፍ ደመወዝ፤ በተያዘው የ2015 በጀት ዓመት ከታህሳስ እስከ የካቲት ያሉትን ሶስት ወራት የሚሸፍን ነው። የገንዘብ ሚኒስቴር ያስተላለፈው ይህ በጀት፤ ባለፈው ሰኞ መጋቢት 4፤ 2015 ወደ መቐለ ዩኒቨርሲቲ የባንክ ሂሳብ መግባቱን የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ገንዘቡ በዩኒቨርስቲው ስር ወዳሉ ኮሌጆች መሰራጨቱን እና በቀጣዩቹ ጥቂት ቀናት ለሰራተኞች ደመወዝ መክፈል እንደሚጀመር አክለዋል።
የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ለአስተዳደር እና የአካዳሚክ ሰራተኞች ከሚቀጥለው ሳምንት ሰኞ መጋቢት 11፤ 2015 ጀምሮ ደመወዝ መከፈል እንደሚጀምር የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕ/ር ገብረየሱስ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። የራያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕ/ር ታደሰ ደጀኔ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ለሰራተኞቹ ደመወዝ ለመክፈል “በዝግጅት ላይ” እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የአክሱም፣ ራያ እና መቐለ ዩኒቨርሲቲ ሰራተኞች፤ ደመወዝ ይከፈላል መባሉን “በጭምጭምታ” መስማታቸውን ተናግረዋል። አንድ የራያ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ሰራተኛ፤ በዩኒቨርሲቲው “ሪፖርት አድርጉ” የሚል ማስታወቂያ ባለፈው ሰኞ መለጠፉን ገልጿል። ይህን ተከትሎም በማግስቱ ወደ ዩኒቨርሲቲው የሰው ሀብት ቢሮ በመሄድ ስሙን በማስመዝገብ እና በመፈረም “ሪፖርት” ማድረጉንም አክሏል።
በትግራይ ክልል ስር ባሉ ዩኒቨርሲቲዎቹ የሚደረገው ውዝፍ ክፍያ፤ የዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች የነበሩ እና በትምህርት ሚኒስቴር ወደ ሌላ ዩኒቨርሲቲዎች የተመደቡ ሰራተኞችን አይጨምርም ተብሏል። የመቐለ ዩኒቨርሲቲው አመራር “ትምህርት ሚኒስቴር ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የመደባቸው ሰራተኞች ዝርዝራቸው ደርሶናል። እነሱን አንከፍለም እነሱን አያካትትም” ሲሉ ይህንኑ አረጋግጠዋል።
የፌደራል መንግስት የ2015 ዓ.ም በጀትን በፓርላማ ሲያጸድቅ፤ በትግራይ ክልል ለሚገኙ አራት ዩኒቨርሲቲዎች 3.5 ቢሊዮን ብር በጀት መመደቡን ይፋ አድርጎ ነበር። ከዩኒቨርሲቲዎቹ ውስጥ ከፍተኛው ገንዘብ የተመደበለት መቐለ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፤ 1.2 ቢሊዮን ብር የመደበኛ እና ካፒታል በጀት ተፈቅዶለታል። በሁለተኛነት የሚከተለው አክሱም ዩኒቨርሲቲ 845 ሚሊዮን ብር፣ ራያ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ 691.8 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦላቸዋል። አዲግራት ዩኒቨርስቲ ለዚህ ዓመት የተመደበለት በጀት 691. 2 ሚሊዮን ብር ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)