በሃሚድ አወል
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤ ከደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ወረዳዎች እና ከተሞች ከተውጣጡ ተወካዮች ጋር ነገ ቅዳሜ መጋቢት 16፤ 2015 በወልቂጤ ከተማ ውይይት ሊያደርጉ ነው። የጉራጌ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ወልቂጤ ከተማ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመቀበል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ነዋሪዎች እና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የዞኑ አመራር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
ነገ በጉራጌ ባህል አዳራሽ በሚደረገው ውይይት፤ በጉራጌ ዞን የሚገኙ የወረዳ አመራሮች እንዲሁም በአዲስ አበባ የሚገኙ የዞኑ ተወላጆች ጥሪ ተደርጎላቸዋል። በጉራጌ ዞን ከሚገኙ በ16 ወረዳዎች ውስጥ የአንዱ አስተዳዳሪ የሆኑ አመራር ለነገው ውይይት ጥሪ እንደተደረገላቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። የውይይቱ ዋና አጀንዳ የ“ክልል አደረጃጃት” እንደሚሆን ተናግረዋል።
ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ሌላ የጉራጌ ዞን አመራር በበኩላቸው፤ የውይይቱ አጀንዳ “በዞኑ ከነበረው ተቃውሞ” ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከነገው ውይይት አስቀድመው ከጉራጌ ተወላጅ ባለሃብቶች እና ምሁራን ጋር በትላንትናው ዕለት ባደረጉት ውይይት ዋነኛ አጀንዳ የነበረው፤ የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ መሆኑን የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች ገልጸዋል።
በዚሁ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የጉራጌ ህዝብ ከልዩነት ይልቅ አንድ መሆን እንደሚገባው መናገራቸውን ምንጮች አክለዋል። በወልቂጤ ከተማ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቀባበል ከተሰቀሉ ባነሮች ውስጥ የተወሰኑት፤ ይህንኑ “የጉራጌ ህዝብን አብሮ የመኖር እሴት የሚሰብኩ” እንደሆኑ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የከተማይቱ ነዋሪዎች ገልጸዋል። በከተማዋ አደባባዮች እና አውራ ጎዳናዎች ላይ ከተሰቀሉት ባነሮች አብዛኞቹ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስል የታተሙባቸው ለእርሳቸው “የእንኳን ደህና መጡ” መልዕክት የሚያስተላልፉ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
የጉራጌ ዞን ነባሩን የደቡብ ክልል ለሁለት የሚከፍለውን የ“ክላስተር” አደረጃጃት ምክረ ሃሳብ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ውድቅ ማድረጉን ተከትሎ፤ በተለይ በወልቂጤ ከተማ ውጥረት ነግሶ ቆይቷል። የጉራጌ የክልልነት ጥያቄን በመደገፍ በወልቂጤ ከተማ ተደጋጋሚ የስራ ማቆም እና በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማዎች ተካሄደዋል።
ካለፈው ህዳር ወር አጋማሽ ጀምሮ በኮማንድ ፖስት እየተመራ በሚገኘው የጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ፤ ባለፈው የካቲት ወር በተካሄደ ሰላማዊ ሰልፍ ሁለት ሰዎች ሲገደሉ ሰባት ሰዎች መቁሰላቸው ይታወሳል። ሰልፈኞቹ አደባባይ ወጥተው የነበረው፤ በወልቂጤ ከተማ ያለውን የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር አስመልክቶ ቅሬታቸውን ለማቅረብ ነበር።
በጉራጌ ዞን በነዋሪዎች ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲቀርበብት የቆየው የክልልነት ጥያቄ እስካሁን መፍትሔ ባያገኝም፤ ጥያቄውን “በአጭር ጊዜ” እውን የማድረግ ዕቅድ ያለው ሀገር አቀፍ ፓርቲ ከሁለት ሳምንት በፊት ምስረታውን አከናውኗል። ጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትህ ፓርቲ (ጎጎት) የተሰኘው ይኸው ፓርቲ ዛሬ አርብ መጋቢት 15 2015 በሰጠው የመጀመሪያው ጋዜጣዊ መግለጫው፤ የክልልነት ጥያቄን በተመለከተ የክልልነት ምስረታን በተመለከተ “የህዝቡ ሕገ መንግስታዊ መብት ሳይሸራረፍ እንዲከበር እንጠይቃለን” ብሏል። ብሏል። የደቡብ ክልል እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች እንዲሁም ሌሎች የመንግስት ተቋማት፤ “ከጉራጌ ዞን ምክር ቤት ውሳኔ ውጭ ህዝቡን በክላስተር ለመጨፍለቅ እያደረጉ ካሉት የተቀናጀ ህገ መንግስታዊ ጥሰት እንዲታቀቡ” በመግለጫው ጠይቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)