ራስ ገዝ ዩኒቨርስቲዎችን የሚመሩ ፕሬዝዳንቶች፤ የፖለቲካ ፓርቲ አባል እንዳይሆኑ የሚያስገድድ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ 

በሃሚድ አወል

የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ ሲሆኑ የሚሾሙላቸው ፕሬዝዳንቶች፤ የፖለቲካ ፓርቲ አባል እንዳይሆኑ የሚያስገድድ የአዋጅ ረቂቅ ለፓርላማ ቀረበ። በአዋጅ ረቂቁ መሰረት ለፕሬዝዳንትነት ተወዳድሮ ያሸነፈ ግለሰብ፤ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ከሆነ ከፓርቲ አባልነት ለመልቀቅ መስማማት ይኖርበታል። 

ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 21፤ 2015 ለተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ስለ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመደንገግ የተዘጋጀው የአዋጅ ረቂቅ፤ የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳቶች አሿሿም እና የስራ ዘመን ላይ ለውጦችን አድርጓል። ከሶስት ዓመት ከመንፈቅ በፊት በ2011 ዓ.ም የወጣው የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ፤ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች ምርጫን በበላይነት የመምራት ስልጣን የሰጠው ለዩኒቨርሲቲ ቦርድ ነበር። አዲሱ የአዋጅ ረቂቅ በበኩሉ፤ የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዝዳንት ሹመት የሚከናወነው “በዩኒቨርሲቲው ቻንስለር ይሆናል” ይላል።

የዩኒቨርስቲዎች ፕሬዝዳንት የሚሾመው “በዓለም አቀፍ ደረጃ ግልጽ በሆነ ውድድር” መሆኑን የሚያትተው የአዋጅ ረቂቁ፤ “የምልመላ እና የምርጫ ስርዓቱም” ተመሳሳይ ሂደትን እንደሚከተል አስፍሯል። በዚህ አይነቱ ውድድር በራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲው ቦርድ አቅራቢነት ከሚቀርቡ ሶስት ዕጩዎች መካከል፤ የዩኒቨርሲቲው “ቻንስለር” ፕሬዝዳንቱን እንደሚሾሙ በረቂቁ ላይ ሰፍሯል። የፕሬዝዳንቱን ሹመት በተመለከተ የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲው ቦርድ፤ መመሪያ የማውጣት ስልጣንም ተሰጥቶታል።

የአዋጅ ረቂቁ ለራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንትነት ካስቀመጣቸው መስፈርቶች መካከል አንደኛው፤ ፕሬዝዳንቱ “በውድድር ካሸነፈ እና የፖለቲካ ፓርቲ አባል ከሆነ ከፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ለመልቀቅ የተስማማ መሆን አለበት” የሚል ነው። አዲሱ አዋጅ “ከፖለቲካ ፓርቲ አባልነት መልቀቅን” በመስፈርትነት ቢያስቀምጥም፤ ራስ ገዝ በመሆን ቀዳሚ እንደሚሆን የሚጠበቀው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕ/ር ጣሰው ወልደሃና ግን በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ብልጽግና ፓርቲን ወክለው አባል ናቸው። 

ገዢውን ፓርቲ ወክለው በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ተወዳድረው ያሸነፉት ግን ፕ/ር ጣሰው ብቻ አይደሉም። የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፋሪስ ደሊልም በተመሳሳይ በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ብልጽግና ፓርቲን ወክለው የፓርላማ አባል ሆነዋል። በተጨማሪም ተጠሪነቱ ለአዲስ አበባ ከተማ የሆነው ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብርሃነመስቀል ጠናም በተመሳሳይ ብልጽግናን ወክለው ፓርላማ ገብተዋል። አሁን በስራ ላይ ያለው የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ፤ ለዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንትነት ለሚደረግ ውድድር “የፖለቲካ ፓርቲ አባል አለመሆን” በመስፈርትነት አልተቀመጠም። 

የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲን በተመለከተ የተዘጋጀው አዋጅ ያስተዋወቀው ሌላኛው አዲስ ነገር፤ “የዩኒቨርሲቲ ቻንስለር” የተባለውን የኃላፊነት ቦታ ነው። በአዲሱ አዋጅ መሰረት የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ አደረጃጀት የሚጀምረው ከ“ቻንስለር” ነው። ቻንስለሩ በእነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች በውስጥ አስተዳደራቸው ውስጥ ሳይገባ “እንደ ከፍተኛ አምባሳደር የሚያገለግል፣ ሀብት የሚያፈላልግ እና ሌሎች በጎ ተግባራትን የሚያከናውን” እንደሚሆን በረቂቁ ተቀምጧል። 

“የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲውን ስራ እና መልካም ስም የሚያጎሉ ተግባራትን፤ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ማከናወን” ሌላው ለ“ቻንስለሩ” የሚሰጠው ኃላፊነት ነው። በዚህ አዋጅ መሰረት ራስ ገዝ ለሚሆኑ የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች “ቻንስለር” የሚሾመው፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሆንም በረቂቁ ሰፍሯል። በዚህ መልኩ የሚሾሙ የዩኒቨርሲቲ “ቻንስለሮች” ለአምስት አመት የሚያገለግሉ ይሆናል። 

በስድስት ክፍሎች እና 45 አንቀጾች የተዘጋጀው አዲሱ አዋጅ፤ የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ማቋቋሚያ መስፈርቶችን ዘርዝሯል። ጠንካራ የፋይናንስ አቅም እና አካዳሚያዊ ተወዳዳሪነት፤ ራስ ገዝ ለመሆን ከሚያስፈልጉ መስፈርቶች መካከል ተጠቅሰዋል። ትምህርት ሚኒስቴር የባህርዳር፣ ጎንደር፣ ጅማ፣ ሀዋሳ፣ አርባ ምንጭ እና መቐለ ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ 10 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ለማድረግ እቅድ መያዙን የአዋጅ ረቂቁ ለፓርላማ ከመቅረቡ ወራት በፊት ገልጾ ነበር።

ከሰባ ሁለት ዓመታት በፊት በቀዳማዊ ኃይለስላሴ የተቋቋመው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ በተያዘው በጀት ዓመት የ“ራስ ገዝ” አስተዳደርን ተግባራዊ በማድረግ የመጀመሪያው ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች በመንግስት ከሚሰጣቸው የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ፤ በስጦታ፣ በኑዛዜ፣ ከትምህርት ከፍያ እና ከፈጠራ ገቢያቸውን ሊያገኙ እንደሚችሉ በአዲሱ አዋጅ ተመላክቷል። 

የመንግስት የገንዘብ ድጋፍ ለራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጠው፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋሙ “በፋይናንስ ራሱን እስኪችል ድረስ” እንደሆነ በአዋጅ ረቂቁ ላይ ተገልጿል። ሆኖም ይህ ከመንግስት የሚመደብ የገንዘብ ድጋፍ “በሂደት እየቀነሰ የሚሄድ” መሆኑ በአዋጁ ተጠቁሟል። ከእነዚህ የገንዘብ ማግኚያ መንገዶች በተጨማሪ ማንኛውም ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ በቦርዱ ውሳኔ የንግድ ድርጅቶች ሊያቋቁም እንደሚችል በረቂቁ ላይ ተቀምጧል። 

ይህን የአዋጅ ድንጋጌ የተወሰኑ የፓርላማ አባላት በስጋት እንደሚመለከቱት ገልጸዋል። አቶ አዳነ ማንዴ የተባሉ የፓርላማ አባል፤ በዚህ አንቀጽ ምክንያት የራስ ገዝ ዩኒቨርስቲዎቹ “የትምህርት ጥራቱን፣ ሌሎች ሌሎች ነገሮችን ትተው ገንዘብ ማግኘት ላይ ብቻ ሊያተኩሩ ይችላል” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ አቶ አዳነ አክለውም ረቂቅ አዋጁ የሚመራለት ቋሚ ኮሚቴ “በዚህ ረገድ ሰፋ ያለ ስራ እንዲሰራ” አሳስበዋል። 

ዶ/ር ተውፊቅ አብዱላሂ የተባሉ ሌላ የምክር ቤት አባልም በተመሳሳይ፤ “በዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት አመታዊ ሪፖርት ላይ ብዙ ችግር ካለባቸው ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀሱት ዩኒቨርሲቲዎቻችን ናቸው። ስለዚህ ራስ ገዝ ሲሆኑ የበለጠ ጥንቃቄ ቢደረግበት” ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል። ምክር ቤቱ የአባላቱን አስተያየት ካዳመጠ በኋላ፤ ረቂቅ አዋጁ በፓርላማው የሰው ሀብት፣ የስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዝርዝር እንዲታይ በሙሉ ድምጽ መርቶታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)