በፓለቲካ ፓርቲዎች ላይ የሚደረጉ “ወከባ፣ ክልከላ እና እገዳዎች” ሰብዓዊ መብቶችን የሚጥሱ መሆናቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ

በአማኑኤል ይልቃል

የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤዎቻቸውን እና ስብሰባዎችን እንዳያደርጉ “በመንግስትም ሆነ በሌሎች አካላት” የሚደረጉ “ወከባ፣ ክልከላ እና እገዳዎች”፤ የመሰብሰብ፣ የመደራጀት እና የመሳተፍ መብቶች ጥሰቶች መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አሳሰበ። መንግስት የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርጓቸውን ስብሰባዎች በተመለከተ “ድንገተኛ እና ከታሰበላቸው ዓላማ በላይ የሆኑ እርምጃዎችን” ከመውሰድ የመቆጠብ ግዴታውን እንዲወጣም ኮሚሽኑ ጠይቋል። 

ኢሰመኮ ይህንን ማሳሰቢያ የሰጠው በፖለቲካ ፓርቲዎች የመሰብሰብ መብት ላይ የሚደረጉ ገደቦች እና በአባላቶቻቸው ላይ የሚደርሱ እንግልቶችን አስመልክቶ ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 21፤ 2015 ባወጣው መግለጫ ነው። ከሰሞኑ የእናት ፓርቲ እና የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤዎች “መስተጓጎሉን” ኮሚሽኑ በመግለጫው ጠቅሷል። የጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ ፓርቲ ምስረታ አስተባባሪዎች ላይ “እስራት እና እንግልት” መፈጸሙንም አስታውሷል። 

መንግስታዊው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋም፤ ከዚህ ቀደም ባደረጋቸው ክትትሎች የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲዎች የአመራር አባሎች ላይ “ገደብ፣ ማዋከብ እና እስራት” መደረጉን በመጠቀስም ችግሩ አሁን የተጀመረ አመሆኑን አስረድቷል። ዜጎች በመረጡት የፖለቲካ አመለካከት እንዲደራጁ፣ የፖለቲካ ፓርቲ እንዲመሰርቱ እና በህዝብ ጉዳዮች ውስጥ እንዲሳተፉ የመሰብሰብ እና የመደራጀት መብቶች አስፈላጊ መሆናቸውን የጠቀሰው ኮሚሽኑ፤ “በተለይ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ህልውና አስፈላጊ ነው” ሲል አጽንኦት ሰጥቷል።

የኢሰመኮ መግለጫ እንደሚያስረዳው በዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች መሰረት እነዚህ መብቶች ሊገደቡ የሚችሉት፤ “ለብሔራዊ ደህንነት፣ የህዝብ ደህንነት፣ የህዝብ ጤና ወይም ሞራል እንዲሁም የሌሎችን መብት ለመጠበቅ” ሲባል ነው። ይህም ቢሆን “የገደቦቹ አስፈላጊነት በአንድ ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ ተቀባይነት” ሊኖረው እና “ተመጣጣኝ” ሊሆን እንደሚገባ አብራርቷል። መንግስት የ“አስፈላጊነት እና ተመጣጣኝነት” ቅድመ ሁኔታዎችን ያላሟሉ እንዲሁም “ድንገተኛ እና ከታሰበላቸው ዓላማ በላይ” የሆኑ እርምጃዎችን ከመውሰድ የመቆጠብ ግዴታ እንዳለበትም ኮሚሽኑ አሳስቧል።

የዜጎች የመሰብሰብ መብት ተግባራዊ እንዲሆን “የማመቻቸት እና ለተሳታፊዎች ጥበቃ እና ከለላ” የማድረግ ግዴታ፤ መንግስት ላይ የተጣለ መሆኑንም ብሔራዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም አስታውሷል። መንግስት ከራሱም ሆነ ከሌላ ሶስተኛ ወገን የሚመጡ “ማስፈራራቶች፣ ዛቻዎች እና ማጉላላቶችን” በመከላከል፣ ጣልቃ ገብነቶችን በአግባቡ በማጣራት እና ምርመራ በማድረግ፤ ተጠያቂነትን የማስፈን ግዴታ እንዳለበት ኮሚሽኑ ጨምሮ ገልጿል። በእነዚህ ክልከላዎች ሳቢያ ዜጎች “የመሰብሰብ መብታቸውን ከመጠቀም እንዲያፈገፍጉ” ከማድረግ መንግስት መቆጠብ እንዳለበትም ኢሰመኮ አሳስቧል። 

ከሰሞኑ ጠቅላላ ጉባኤዎችን ሊያደርጉ በተንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ የተደረገው እግድ፤ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም በተመሳሳይ ትችት ቀርቦበት ነበር። ባርዱ ከሶስት ሳምንት በፊት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ይህ አይነቱ እግድ “በመድብለ ፓርቲ ስርዓት የማሳደግ የሙከራ ሂደት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ጫና የሚያስከትል ይሆናል” ሲል ተቃውሞውን አሰምቶ ነበር። የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤን ያሰናከሉ የህግ አስፈጻሚ አካላት ላይም ፍትሕ ሚኒስቴር ክስ እንዲመሰርት ቦርዱ በዚሁ መግለጫው መጠየቁ ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)