ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው እና ቴዎድሮስ አስፋው፤ “ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ” በመንቀሳቀስ መጠርጠራቸውን ፖሊስ ለፍርድ ቤት ገለጸ

በሃሚድ አወል

የ“አራት ኪሎ ሚዲያ” የዩ ቲዩብ መገናኛ ብዙሃን መስራች ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው እና “ኢትዮ ሰላም” የተሰኘው የዩ ቲዩብ መገናኛ ብዙሃን መስራች ቴዎድሮስ አስፋው፤ “በህዝብ የተመረጠን መንግስት እና ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ” በመንቀሳቀስ መጠርጠራቸውን ፖሊስ ለፍርድ ቤት አስታወቀ። ሁለቱ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች፤ 10 የምርመራ ቀናት በፍርድ ቤት ተፈቅዶባቸዋል። 

ባለፈው ረቡዕ እና ሐሙስ በቁጥጥር ስር የዋሉት ቴዎድሮስ እና ዳዊት፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረቡት ዛሬ ቅዳሜ ሚያዚያ 7፤ 2015 ነው። የፌደራል ፖሊስ ሁለቱን የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ባቀረበበት ወቅት፤ የተጠረጠሩበትን የወንጀል ዝርዝር በንባብ አሰምቷል። 

ሁለቱ ተጠርጣሪዎች በከፈቷቸው የዩ ቲዩብ መገናኛ ብዙሃኖች፤ “ምንም አይነት የህዝብ ውክልና ሳይኖራቸው፤ የአማራ ህዝብ ግፍ ደርሶበታል በማለት ያልተገባ ወሬ አሰራጭተዋል” ሲል ወንጅሏቸዋል። በመገናኛ ብዙሃኖቻቸው “ግላዊ ፍላጎታቸውን” ሲያንጸባርቁ ነበር የተባሉት ዳዊት እና ቴዎድሮስ፤ “ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ” እንዲሁም “የአማራን ህዝብ ለአመጽ እና ለትግል ለማነሳሳት” በሚዲያ ሲቀስቅሱ ነበር ሲል ፖሊስ ለችሎት ባቀረበው እና ለተጠርጣሪዎቹም በሰጠው መማልከቻ ላይ አስፍሯል።  

ሁለቱ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ፈጽመውታል በተባለ ቅስቀሳ “ሁከት እና ብጥብጥ እንዲፈጸም፣ መንገዶች ተዝግተው ዜጎች የመንቀሳቀስ መብታቸው እንዲታገድ እና የኢኮኖሚ ጉዳት እንዲደርስባቸው” ማድረጋቸውን ፖሊስ ለችሎት አስረድቷል። ተጠርጣሪዎቹ “በብሔር ብሔረሰቦች መካከል ጥላቻን በማሰራጨት፣ በሀገሪቷ ዕልቂት እንዲፈጸም የሃይማኖት ጉዳይን ምክንያት በማድረግ፣ በህዝብ የተመረጠን መንግስት እና ሕገ መንግስታዊ ስርዓት በኃይል ለመናድ የማህበራዊ ሚዲያ በመጠቀም ሁከት እና ብጥብጥ እንዲፈጸም ሲያደርጉ የቆዩ መሆናቸውን” ፖሊስ በማመልከቻው አትቷል።

የፌደራል ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ ቅሰቀሳ ያደርጉባቸዋል ያላቸው ማህበራዊ ሚዲያዎች፤ “ኢትዮ ሰላም” እና “አራት ኪሎ ሚዲያ” የተባሉ የዩ ቲዩብ መገናኛ ብዙሃንን ነው። እነዚህ “የዩ ቲዩብ ማህበራዊ ሚዲያዎች”፤ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ተመዝግበው “ህጋዊነታቸው ያልተረጋገጠ” እና “ፍቃድ የሌላቸው” መሆኑን ፖሊስ በማመልከቻቸው ጠቁሟል። ቴዎድሮስ እና ዳዊት “ሌሎች ጠያቂ ግለሰቦችን በማዘጋጀት”፣  እነርሱ ራሳቸው “መግለጫ ሰጪ በመሆን” “ግጭት ቀስቃሽ ሀሳቦችን በመልቀቅ” ሲቀሰቅሱ ነበር ሲል ፖሊስ ወንጅሏል። 

“የተጠርጣሪዎቹ አደገኝነት፣ የተሳተፉበት ወንጀል ስፋትና ውስብስብነት እና የሀገርን አንድነት የሚያፈርስ ወንጀል እንዲፈጸም የሚቀሰቅሱ፣ የሚፈጥሩ፣ የሚያደራጁ በመሆኑ፤ የምርመራ ስራችንን በስፋት፣ በሰው እና በሰነድ ማስረጃ ማጣራት እንድንችል የ14 ቀን የምርመራ ማጣሪያ የጊዜ  ቀጠሮ እንዲፈቀድልን እንጠይቃለን” ሲል ፖሊስ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል። ሁለቱን የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ወክለው ፍርድ ቤት የቀረቡት አራት ጠበቆች በበኩላቸው፤ ተፈጸመ የተባለው ወንጀል “በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት የተፈጸመ መሆኑን” በመጥቀስ፤ የደንበኞቻቸው የዋስትና መብት እንዲጠበቅላቸው አመልክተዋል።

ቴዎድሮስን ወክለው ችሎት ከቀረቡት ጠበቆች አንዱ የሆኑት አቶ አበበ መስፍን፤ “በሚዲያ ለተላለፈ ነገር የጊዜ ቀጠሮ ሊጠየቅበት አይገባም” ሲሉ ደንበኛቸው በዋስትና ከእስር እንዲለቀቅ ጠይቀዋል። ሌላኛው ጠበቃ አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ በበኩላቸው “ደንበኛዬ ‘የአማራ ህዝብ በመንግስት ላይ ተነስ’ አላሉም” ሲሉ በፖሊስ የቀረበውን “የአማራን ህዝብ ለአመጽ እና ለትግል ማነሳሳት” የሚለውን ውንጀላ ተቃውመዋል።

ጠበቃ ሰለሞን ከሁለት ዓመታት በፊት የወጣውን የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ በመጥቀስም፤ ችሎቱ ለፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዳይፈቀድ  ጥያቄ አቅርበዋል። ከመገናኛ ብዙሃን ጋር የተያያዙ ክሶች ስለሚቀርቡበት ሁኔታ የሚያትተው የዚህ አዋጅ ክፍል፤ በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ወንጀል በመፈጸም የተጠረጠረ ግለሰብ በእስር ሳይቆይ ክስ እንደሚመሰረትበት ይደነግጋል። 

ይህ የአዋጁ ድንጋጌ፤ የጋዜጠኛ ዳዊት ጠበቃ በሆኑት አቶ ቤተማርያም አለማየሁም ተነስቷል። ጠበቃ ቤተማርያም “ጉዳዩ ሊታይ የሚገባው በመገናኛ ብዙሃን አዋጁ ነው” የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል። ጠበቃው አክለውም “መቼ የተፈጸመ ወንጀል መሆኑ [በማመልከቻቸው] አልተቀመጠም። ደንበኛዬ ፍርድ ቤት የቀረቡት የተፈጸመው ወንጀል መቼ መሆኑ ባልተገለጸበት ነው። [ስለዚህ] ቀጠሮ ሊፈቀድ አይገባም” ሲሉ ተከራክረዋል። 

ሁለቱ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በአንድ መዝገብ ችሎት ፊት መቅረባቸውን የጠቀሱት ጠበቃ ቤተማርያም፤ በሁለተኛ ተጠርጣሪነት በመዝገቡ የተካተተው ዳዊት በጋሻው የወንጀል ተሳትፎ አለመገለጹን ጠቁመዋል። ጋዜጠኛ ዳዊት ባለፈው ረቡዕ በባህርዳር ከተማ በመከላከያ ሰራዊት አባላት መያዙን ያነሱት ቤተማርያም፤ በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት አለመቅረቡንም ለችሎቱ ገልጸዋል። ይህ ያልሆነበት ምክንያትም “በገለልተኛ አጣሪ ተጣርቶ እርምጃ እንዲወሰድ” ሲሉም አመልክተዋል። 

ሌላኛው የጋዜጠኛው ጠበቃ አቶ ሄኖክ አክሊሉ፤ ዳዊት በዋስትና እንዲወጣ ጠይቀዋል። ጋዜጠኛ ዳዊትን ዋስትና ሊያስከለክል የሚችል “ልዩ ሁኔታ” ለችሎት አለመቅረቡን ያነሱት ጠበቃ ሄኖክ፤ ደንበኛቸው “ቢወጡ በምርመራ ስራው ላይ ሊፈጥሩ የሚችሉት መሰናክል አልተገለጸም” ሲሉ ለዋስትና ጥያቄያቸው የማጠናከሪያ ሃሳብ አሰምተዋል። 

የዋስትና ጥያቄውን የተቃወሙት መርማሪ ፖሊሶች በበኩላቸው፤ “ወንጀሉ ቀላል አይደለም። በሚዲያ በተላለፈ መልዕክት ምክንያት የሰው ህይወት አልፏል” ሲሉ ዋስትናው ውድቅ እንዲደረግ ጠይቀዋል። “የእያንዳንዳቸውን ተሳትፎ የሚያሳይ ከብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት የመጣ ማስረጃ አለን” ያሉት መርማሪዎቹ፤ ማስረጃውን በቀጣይ ቀጠሮ እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል። 

ተጠርጣሪዎቹ “ጋዜጠኛ ቢሆኑም የወጣውን አዋጅ ጥሰው የሚንቀሳቀሱ ከሆነ የማይጠየቁበት ምክንያት የለም” ሲሉም መርማሪዎቹ በጠበቆች ለተነሳው መከራከሪያ ምላሽ ሰጥተዋል። ጋዜጠኛ ዳዊት በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት ያልቀረበበትን ምክንያት አስመልክቶ በጠበቃው ለቀረበው አቤቱታ መርማሪዎቹ በሰጡት መልስ፤ ተጠርጣሪው እነርሱ ጋር የደረሰው ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ጠዋት መሆኑን አስረድተዋል። ዳዊት ወደ እነርሱ የመጣው፤ በመከላከያ ሰራዊት አባላት ከባህር ዳር ከተያዘ በኋላ መሆኑም ለችሎቱ አስታውቀዋል።

መርማሪ ፖሊሶቹ የተጠርጣሪዎቹ ቅስቀሳ “ለሰው ህይወት ማለፍ ምክንያት ሆኗል” ሲሉ በምላሻቸው የጠቀሱትን በተመለከተ፤ ጠበቃ ሄኖክ ተጨማሪ የመናገሪያ ዕድል እንዲሰጣቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀው ተፈቅዶላቸዋል። ጠበቃ ሄኖክ፤ “የሰው ህይወት አልፏል የሚለው አዲስ ፍሬ ነገር ነው። በማመልከቻው ላይ የለም። እንዳይመዘገብ፤ ከተመዘገበም እንዲሰረዝ እንጠይቃለን” ሲሉ ለችሎቱ አቤት ብለዋል። 

የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት፤ የሁለቱ ተጠርጣሪዎች የወንጀል ተሳትፎ ተለይቶ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ጋዜጠኛ ዳዊት ለፌደራል ፖሊስ የተላለፈበትንም ቀን፤ የእስረኞች አስተዳደር በቀጣይ ቀጠሮ እንዲያሳውቅ ችሎቱ በተጨማሪነት አዝዟል። ፍርድ ቤቱ በመጨረሻም ለፖሊስ 10 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት በመፍቀድ የዕለቱን የችሎቱ ውሎ አጠናቅቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)