በአማኑኤል ይልቃል
ከአዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ገደማ ላይ በምትገኘው የቢሾፍቱ ከተማ “ማንነታቸው ያልታወቁ” ታጣቂዎች ትላንት እሁድ ግንቦት 6፤ 2015 ለሊት በፖሊስ ጣቢያ ላይ በከፈቱት ጥቃት፤ አራት የኦሮሚያ ፖሊስ አባላት ተገደሉ። በጥቃቱ ጉዳት የደረሰበት አንድ የፖሊስ አባል፤ አዲስ አበባ ወደሚገኘው የፖሊስ ሆስፒታል ተወስዶ በህክምና ላይ መሆኑን የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች ገልጸዋል።
በቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ስር በሚገኘው የክፍለ ከተማ ሶስት ፖሊስ ጽህፈት ቤት ላይ ታጣቂዎች ተኩስ የከፈቱት፤ ሌሊት ስድስት ሰዓት ገደማ ላይ መሆኑን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ሶስት የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል። በከተማዋ መግቢያ ላይ “ሰንሻይን” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው በዚሁ ፖሊስ ጣቢያ ላይ ጥቃቱን የፈጸሙት ታጣቂዎች፤ “ማንነታቸው የማይታወቅ” መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በዚሁ አካባቢ የሚኖሩ አንድ የዓይን እማኝ፤ በትላትናው ዕለት እኩለ ለሊት ገደማ በታጣቂዎቹ እና በፖሊስ አባላቱ መካከል “ከፍተኛ ድምጽ” ያለው የተኩስ ልውውጥ ሲደረግ እንደነበር ገልጸዋል። የተኩስ ልውውጡ ለአንድ ሰዓት ገደማ ያህል የቆየ እንደነበርም ተናግረዋል። ሌላው የአካባቢው ነዋሪ በበኩላቸው፤ በፖሊስ ጣቢያው ፊት ለፊት በሚገኘው “ያቱ ሆቴል” ተረኛ የነበሩ የጥበቃ ሰራተኞች ላይ ጭምር ተኩስ ተከፍቶባቸው ነበር ብለዋል። የሆቴሉ የጠዋት ተረኞች ወደ ስራ ሲገቡ፤ በሩ ላይ ቀለሃዎች ወድቀው ማግኘታቸውን እንደሰሙም አክለዋል።
በ“ያቱ ሆቴል” ሆቴል ቅጽር ግቢ ቆመው የነበሩ ተሽከርካሪዎች በጥይት መመታታቸውን እኚሁ ነዋሪ ጨምረው ገልጸዋል። በስፍራው የተገኘው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ፤ በሆቴሉ የመኪና ማቆሚያ ስፍራ ያለ እና በጥይት የተመታ የ“ቪትዝ” ተሽከርካሪ ተመልክቷል። ተኩስ የተከፈተበትን ፖሊስ ጣቢያ የቃኘው ዘጋቢው፤ በተመሳሳይ ሁኔታ በጥይት መመታቱን ታዝቧል። የፖሊስ ጣቢያው መግቢያ እና አጥሩን ተያይዞ ባለው መደብር ላይ በጥይት የተበሳሱ 25 ቀዳዳዎችን ቆጥሯል።
በፖሊስ ጣቢያው ላይ በተከፈተው ተኩስ፤ በዕለቱ ተረኛ የነበሩ አራት የኦሮሚያ ፖሊስ አባላት ሲገደሉ አንድ የፖሊስ አባል መቁሰሉን ሶስት የፖሊስ አባላት፣ ሁለት የሟቾች ቤተሰቦች እና ሶስት የአካባቢው ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። ጉዳት የደረሰበት የፖሊስ አባል፤ ለተሻለ ለህክምና አዲስ አበባ ከተማ ወደሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ሪፈራል ሆስፒታል መወሰዱንም ምንጮች ጠቁመዋል።
የሟቾቹ ቤተሰቦች እና ዘመዶች፤ ዛሬ ሰኞ በፖሊስ ጣቢያው ግቢ ውስጥ እና ደጅ ላይ ተሰብስበው እያለቀሱ የሟቾች አስከሬን ከምርመራ እስከሚመለስ ድረስ ሲጠባበቁ ተስተውለዋል። የአራቱን የፖሊስ አባላት አስከሬን የያዙ ሶስት አምቡላንሶች በፖሊስ ጣቢያው የደረሱት ከቀኑ 7፡30 ገደማ ሲሆን፤ በዚህ ጊዜ የተሰበሰቡት የሟች ቤተሰቦች እንዲሁም የኦሮሚያ ፖሊስ አባላት በከፍተኛ ድምጽ ሲያለቅሱ በስፍራው የነበረው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ተመልክቷል።
በአምቡላንስ መኪናዎች ተጭኖ የመጣው የሟቾች አስከሬን፤ ለጥቂት ደቂቃዎች በፖሊስ ጣቢያው ግቢ ውስጥ ከቆየ በኋላ ቤተሰቦች እና የፖሊስ አባላትን በጫኑ ሌሎች መኪናዎች ተሸኝቷል። በጥቃቱ ከተገደሉት የፖሊስ አባላት ውስጥ ሶስቱ ከቢሾፍቱ ከተማ ውጪ ወዳሉ “ገጠር” አካባቢዎች መሸኘታቸውን ባልደረባዎቻቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። በትላንት ለሊቱ ጥቃት ህይወታቸውን ካጡት መካከል የአንዱ ፖሊስ አስክሬን፤ ከተማዋ ውስጥ ወደሚገኘው የቤተሰቦቹ መኖሪያ ቤት መወሰዱንም ገልጸዋል።
የፖሊስ አባላቱ የአስከሬን ሽኝት ስነ ስርዓት ከተደረገ ከግማሽ ሰዓት ገደማ በኋላ፤ ጥቃት የደረሰበት የፖሊስ ጣቢያ ወደ መደበኛ ስራው ተመልሷል። በዚህ ጊዜም ተረኛ ፖሊሶች፤ በጣቢያው በእስር ላይ የሚገኙ ተጠርጣሪዎችን ለመጠየቅ የመጡ ሰዎችን ሲያስተናግዱ ታይተዋል። በግቢው ውስጥ ገብተው እስረኞችን እንዲመለከቱ የሚፈቀድላቸው፤ ለታሳሪዎች የሚሰጥ ምግብ የያዙ ሰዎች ብቻ መሆናቸውን የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ተመልክቷል።
የቢሾፍቱ ከተማ በምትገኝበት የምስራቅ ሸዋ ዞን ውስጥ የሚገኙ አካባቢዎች፤ የትላንቱን አይነት ጥቃት ከዚህ ቀደም ሲያስተናግዱ ቆይተዋል። በዞኑ ውስጥ በምትገኘው መተሐራ ከተማ እና አካባቢው፤ “ማንነታቸው ባልታወቀ ታጣቂዎች” በተፈጸሙ ጥቃቶች የአካባቢው ነዋሪዎች መገደላቸው ይታወሳል። በዚሁ ዞን ስር ባለው የወለንጪቲ ከተማ አቅራቢያ፤ ባለፈው መጋቢት ወር መጨረሻ 15 አሽከርካሪዎች መታገታቸውን መዘገቡ አይዘነጋም። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በትላንትናው ዕለት በቢሾፍቱ ከተማ ስለተፈጸመው ጥቃት፤ ከክፍለ ከተማ ሶስት ፖሊስ ጽህፈት ቤት ይፋዊ መረጃ ለማግኘት ያደረገችው ጥረት አልተሳካም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)