ከውጭ የልማት አጋሮች ዘንድሮ ለማግኘት ታቅዶ የነበረው 7.7 ቢሊዮን ብር፤ እስካሁን “ፈሰስ አለመደረጉን” የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ  

በአማኑኤል ይልቃል

የፌደራል መንግስት በተያዘው በጀት ዓመት ከውጭ ቀጥታ የበጀት ድጋፍ 7.7 ቢሊዮን ብር ለማግኘት ቢያቅድም፤ እስካሁን “ፈሰስ አለመደረጉን”  የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ። ሶስት ሚሊዮን ዜጎች በጦርነት እና ግጭት ሳቢያ “ወደ ከፋ ድህነት” መግባታቸውን በጥናት ማረጋገጡንም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገልጿል። 

የገንዘብ ሚኒስቴር ይህን ያስታወቀው የዘጠኝ ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርቱን፤ ለተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዛሬ ረቡዕ ግንቦት 9፤ 2015 ባቀረበበት ወቅት ነው። በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በቀረበው የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ከተነሱ ጉዳዮች ውስጥ የመንግስትን ገቢ የሚመለከተው ይገኝበታል።  

የፌደራል መንግስት በተያዘው በጀት ዓመት፤ ከታክስ፣ ታክስ ካልሆኑ እና ከውጭ ቀጥተኛ የበጀት ድጋፍ 446.5 ቢሊዮን ብር ለማግኘት አቅዶ እንደነበር በሚኒስቴሩ ሪፖርት ላይ ተጠቅሷል። ከዚህ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው የታክስ ገቢ ሲሆን፤ ከዚህም 400.2 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ነበር። በዘንድሮው በጀት ዓመት መጀመሪያ ላይ በተያዘው በዚህ እቅድ፤ “ከውጭ የልማት አጋሮች የሚመጣ ቀጥተኛ የበጀት ድጋፍ” በሚል ታሳቢ ተደርጎ የነበረው 7.7 ቢሊዮን ብር ነበር።

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

የገንዘብ ሚኒስትሩ በዛሬው ሪፖርታቸው፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከዓመታዊው የመንግስት የገቢ እቅድ ማሳካት የተቻለው 63.3  በመቶ መሆኑን አስታውቀዋል። በዚህ ወቅት 282 ቢሊዮን ብር ታክስ እንደተሰበሰበ ያነሱት አቶ አህመድ፤ ይህም የእቅዱን 70.5 በመቶ የሸፈነ መሆኑን አስረድተዋል። በዘንድሮው ዓመት “ለወጪ በጀት መሸፈኛ” ከልማት አጋሮች ይገኛል የተባለው ገንዘብ ግን በዘጠኝ ወራቱ ውስጥ ፈሰስ አለመደረጉን ሚኒስትሩ ለቋሚ ኮሚቴው ገልጸዋል። 

ከቀጥተኛ የበጀት ድጋፍ በተጨማሪ በዚህ ዓመት ከውጭ የልማት አጋሮች በእርዳታ እና ብድር መልክ እንዲገኝ የታቀደው ሀብት እና ከተገኘ በኋላ ይለቀቃል ተብሎ የተጠበቀው ገንዘብም በእቅድ ከተቀመጠው በታች መሆኑን አቶ አህመድ አብራርተዋል። በዘጠኝ ወራት ውስጥ በእርዳታ እና በብድር ለማግኘት ታቅዶ የነበረው 2.9 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ ማሳካት የተቻለው 62.2 በመቶ መሆኑን አመልክተዋል። ስምምነት ከተደረገባቸው ብድር እና እርዳታዎች ፈሰስ ይደረጋል ተብሎ ተጠብቆ የነበረው 2.5 ቢሊዮን ብር መሆኑን ያነሱት አቶ አህመድ፤ ከዚህ ውስጥ 1.8 ቢሊዮን ዶላር መለቀቁን ተናግረዋል።

ከውጭ የሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ ላይ እንቅፋት የሆነው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እንደሆነ በዛሬው የፓርላማ የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ተነስቷል። የፌደራል መንግስት እና ህወሓት ከሰባት ወራት ገደማ በፊት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነት ቢፈራረሙም፤ በጦርነቱ ምክንያት የተፈጠረው ተፅዕኖ ግን አሁንም መኖሩም ተጠቁሟል። አቶ አህመድ ከውጭ የሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ አፈጻጸም ዝቅተኛ የሆነበትን ምክንያት ሲያስረዱ፤ “አንዳንድ የልማት አጋሮች ከሰሜኑ የሀገራችን ጦርነት ጋር በተያያዘ በተለይ በበጀት ድጋፍ መልክ ለመስጠት የታሰበውን ፍሰት በማቆማቸው ነው” ብለዋል። 

ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ “አንዳንድ የልማት አጋሮች ያልተገባ ጫና ማድረጋቸውን” የገለጹት አቶ አህመድ፤ ከእነዚህ አካላት ውስጥ አንዳንዶቹ “የሚሰጡት የልማት ትብብር አይነት ላይ ለውጥ” ሲያደርጉ “አንዳንዶቹ” ደግሞ “ከዚህ በፊት የነበራቸው commitment በተወሰነ ደረጃ መቀዝቀዙን” አንስተዋል። ድጋፉን ከሚያደርጉት የልማት አጋሮች መካከል “ከአንዳንዶቹ ጋር ስምምነት” ተፈጽሞ የነበረ ቢሆንም፤ “ያቀዱትን ፋይናንስ ባለመስጠት ኃላፊነታቸውን አልተወጡም” ሲሉ ወቅሰዋል። 

ጦርነት በነበረባቸው አካባቢዎች የፕሮጀክቶች ትግበራ መቋረጡ፤ መለቀቅ የነበረበት እርዳታ እና ብድር ላለመምጣቱ ተጨማሪ ምክንያት መሆኑንም አስረድተዋል። ባለፉት ወራት ጦርነት በመቆሙ፤ “በአጭር ጊዜ” ውስጥ የገንዘብ ፍሰቱ ተሻሽሎ “ወደነበረበት” ይመለሳል ብለው እንደሚያስቡ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። “በቅርቡ ከተፈጠረው ሰላም አንጻር፣ የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊ ከማድረግ ጎን ለጎን፣ ከልማት አጋሮች ጋር ያለንን ትብብር ለማስፋት የተለያዩ ውይይቶች እየተደረጉ ይገኛሉ። የተሻለ መቀራረብ እና መረዳዳት አለ” ሲሉም አክለዋል። 

መንግስት ያነጋገራቸው “አብዛኛዎቹ የልማት አጋሮች” እና “የኢትዮጵያ ወዳጅ የሆኑ መንግስታት”፤ በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች የሚደረገውን የመልሶ ግንባታ ስራን ለማገዝ “ጠንካራ ፍላጎት” እያሳዩ መሆናቸውን ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል። የገንዘብ ሚኒስቴር በበኩሉ በጦርነት እና በግጭት ምክንያት የደረሰውን ጉዳት እና ለመልሶ ግንባታ የሚያስፈልገውን ገንዘብ የሚያሳዩ ሁለት የጥናት ሰነዶችን ሰርቶ ማጠናቀቁን አቶ አህመድ ገልጸዋል። 

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

“በቅርቡ ይፋ ይሆናል” በተባሉት በእነዚህ ጥናቶች መሰረት፤ ጦርነቱ 22 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚገመት ጉዳት መድረሱ እንደታወቀ ለፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ አባላት ተገልጿል። በጦርነቱ ምክንያት የደረሰው የኢኮኖሚ ኪሳራ ደግሞ ስድስት ቢሊዮን ዶላር እንደሚገመት በጥናት መረጋገጡ ተጠቅሷል። በዚሁ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጥናት ላይ፤ ግጭት እና ጦርነት በነበረባቸው አካባቢዎች በሚኖሩ ሰዎች ላይ የደረሰው ተጽእኖ ምን ያህል እንደሆነ መዳሰሱም ተመልክቷል። 

ይኸው ጥናት ጦርነት በነበረባቸው አካባቢዎች ከሚገኙ ጠቅላላ ነዋሪዎች ውስጥ፤ አንድ ሶስተኛው በጦርነቱ በቀጥታ እንደተጎዱ አረጋግጧል ተብሏል። በግጭት እና ጦርነት ሳቢያ ሶስት ሚሊዮን ዜጎች “ወደ ከፋ ድህነት” መግባታቸው በጥናቱ መረጋገጡንም፤ ለፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ አባላት የቀረበው ሪፖርት ይፋ አድርጓል። በግጭት እና በጦርነት የደረሰውን ይህንን ጉዳት “ለመቀልበስ” እና “ከጦርነት በፊት ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ” የሚያስችል “የመልሶ ማቋቋም እና ግንባታ አገራዊ የእቅድ ማዕቀፍ” መዘጋጀቱን የገንዘብ ሚኒስትሩ ለቋሚ ኮሚቴ አባላት ተናግረዋል። 

ከአውሮፓውያኑ 2023 እስከ 2028 በሚቆየው በዚህ ማዕቀፍ የተያዘውን እቅድ ለማስፈጸም፤ “በአጠቃላይ እስከ 20 ቢሊዮን ዶላር” እንደሚያስፈልግ አቶ አህመድ ገልጸዋል። መንግስት ለዚህ የአምስት ዓመት እቅድ ማስፈጻሚያ “ከልማት አጋሮች ጠንከር ያለ እገዛ” እንደሚጠብቅ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ለእቅዱ የሚውለውን ተጨማሪ ሀብት፤ “ከሀገር ውስጥ በጀት፣ ከልማት ድርጅቶች፣ ከተለያዩ ባለሀብቶች እንዲሁም ከህዝቡ ጉልበት እና የተደራጀ ተሳትፎ” ለማግኘት መታቀዱን አቶ አህመድ ለፓርላማ አባላቱ አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)