ብርቱካን ሚደቅሳ የስራ መልቀቂያ ማስገባታቸውን አስታወቁ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአፈ ጉባኤ ጽህፈት ቤት የስራ መልቀቂያ ማስገባታቸውን አስታወቁ። ለአራት ዓመታት ከስድስት ወራት ምርጫ ቦርድን የመሩት ብርቱካን ከመጪው ነሐሴ 1፤ 2015 ጀምሮ ሥራ ለመልቀቅ መወሰናቸውን የገለጹት በተረጋገጠ የፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ነው።

ብርቱካን ከዋና ሰብሳቢነታቸው የሚለቅቁት ጤናቸውን “በሚገባ ለመጠበቅ የረጅም ጊዜ እረፍት” ስለሚያስፈልጋቸው እንደሆነ በዚሁ የፌስ ቡክ መልዕክታቸው ገልጸዋል። በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አቅራቢነት ብሔራዊ የምርጫ ቦርድን እንዲመሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህዳር 13፤ 2011 የተሾሙት ብርቱካን፤ መልቀቂያቸውን ለፓርላማ አፈ ጉባኤ ጽህፈት ቤት ያስገቡት ሰኔ 5፤ 2015 መሆኑን በመልዕክታቸው ጠቅሰዋል።

ዋና ሰብሳቢዋ ስራ ሲጀምሩ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን “ተዓማኒ እና ራሱን ችሎ ምርጫን ማከናወን የሚችል ተቋም” የማድረግ ህልም እንደነበራቸው ስንብታቸውን ይፋ ባደረጉበት አጭር ጽሁፍ ገልጸዋል። ብርቱካን የምርጫ ቦርድን ዋና ሰብሳቢነት ከተረከቡ በኋላ፤ ተቋሙ ስድስተኛውን አጠቃላይ አገራዊ ምርጫ እና በደቡብ ክልል ሶስት ህዝበ ውሳኔዎችን አካሂዷል። 

ብርቱካን በስንብት ጹሁፋቸው ምርጫ ቦርድን “ተዓማኒነት በማሻሻል ረገድ፣ በተቻለ አቅምም የፓለቲካ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴዎች ለማገዝ ባደረግነው ጥረት ስኬታማ ነን ብዬ አምናለሁ” ሲሉ ጽፈዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)