በ21 የኤፈርት ድርጅቶች ላይ ተጥሎ የነበረው እግድ እንዲነሳ በፍርድ ቤት ተወሰነ   

በሃሚድ አወል

በትግራይ የመልሶ ማቋቋም ኢንዶውመንት ፈንድ (ኤፈርት) ስር የሚገኙ 21 ድርጅቶች ላይ ተጥሎ የነበረው እግድ እንዲነሳ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወሰነ። ድርጅቶቹን በጊዜያዊነት ሲያስተዳድር የቆየው የኮሜርሻል ኖሚኒስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ኃላፊነትም እንዲሻር ፍርድ ቤቱ አዝዟል። 

እነዚህን ተደራራቢ ትዕዛዞች ባለፈው ሳምንት አርብ ሐምሌ 21፤ 2015 የሰጠው፤ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ወንጀል ጉዳዮች ችሎት ነው። የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ትዕዛዞቹን ያስተላለፈው፤ ፍትሕ ሚኒስቴር በኤፈርት ስር ያሉ ድርጅቶች ላይ የተሰጠው ዕግድ እና በጊዜያዊነት የማስተዳደር ኃላፊነት እንዲነሳ ጥያቄ ማቅረቡን ተከትሎ ነው። 

በጦርነት እና በድርቅ የተጎዳውን የትግራይ ክልል ኢኮኖሚ መልሶ የማሻሻል ዓላማን ይዞ በ1987 ዓ.ም የተመሰረተው ኤፈርት፤ በኮንስትራክሽን፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ ግብርና፣ ማዕድን እና ትራንስፖርት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችን በስሩ ሲያስተዳድር ቆይቷል። ሱር ኮንስትራክሽን፣ መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ፣ ጉና ትሬዲንግ፣ መሰቦ ሲሚንቶ እና አልመዳ ጨርቃ ጨርቅ በኤፈርት ስር ከሚተዳደሩ ግዙፍ ድርጅቶች መካከል ይጠቀሳሉ። 

በኤፈርት ስር ያሉ 34 ድርጅቶች የባንክ ሂሳብ እንዲታገድ የተደረገው፤ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በይፋ ከተቀሰቀሰ ሁለት ሳምንት በኋላ ህዳር 7፤ 2013 ነበር። የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ እግዱን ያስተላለፈው፤ ድርጅቶቹ ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ጋር በተያያዘ “ሽብርተኝነትን በገንዘብ በመደገፍ” ወንጀል  በመጠርጠራቸው ምክንያት መሆኑ በወቅቱ ተገልጿል። 

ከዚህ ውሳኔ አንድ ወር ገደማ በኋላ ደግሞ በኤፈርት ስር ያሉ ድርጅቶች ወደ ስራ እንዲገቡ የሚያደርጉ ሰባት አባላት ያሉት ጊዜያዊ ባለአደራ አስተዳደር ቦርድ በፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ መሾሙ ይታወሳል። በዚህ ባለአደራ ቦርድ ውስጥ ከተካተቱት ግለሰቦች አብዛኞቹ፤ በተለያየ ወቅት በኤፈርት ስር ያሉ ድርጀቶችን በኃላፊነት የመሩ እና ለድርጅቶቹ ቅርበት ያላቸው ናቸው። ሆኖም የጊዜያዊ ባለአደራ አስተዳደር ቦርዱ ስልጣን ከወራት የዘለለ አልሆነም። 

የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ፤ የቦርዱ አባላት “የድርጅቶቹን ንብረቶች በአግባቡ እያስተዳደሩ አለመሆኑ የታመነበት” መሆኑን በመጥቀስ ከአስተዳዳሪነታቸው እንዲነሱ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀረበው ጥያቄ በመስከረም 2014 ዓ.ም ተቀባይነት አግኝቷል። ፍርድ ቤቱ ከዚህም በተጨማሪ የድርጅቶቹ የሚንቀሳቀሱ እና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ላይም በወቅቱ የእግድ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

ከዚህ ውሳኔ አምስት ወራት በኋላ በተካሄደ ችሎት፤ ኮሜርሻል ኖሚኒስ የተሰኘው ኩባንያ በኤፈርት ስር የሚገኙ 18 ድርጅቶችን እንዲያስተዳድር በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተሹሟል። በየካቲት 2014 ዓ.ም. ድርጅቶቹን ማስተዳደር የጀመረው ኮሜርሻል ኖሚኒስ፤ ውሳኔው በፍርድ ቤት እንዲሻር እስከተደረገበት እስካለፈው አርብ ድረስ ይህንኑ የኃላፊነት ድርሻውን ሲወጣ ቆይቷል። 

ሆኖም ኮሜርሻል ኖሚኒስ ድርጅቶቹን እያስተዳደር ባለበት ባለፈው መጋቢት ወር፤ የሱር ኮንስትራክሽን የህግ አገልግሎት ዋና ኦፊሰር (ቺፍ ሌጋል ኦፊሰር) አቶ ወርቀልዑል ግደይ ኩባንያው ከኃላፊነቱ እንዲነሳ ለፍትሕ ሚኒስቴር በደብዳቤ ጥያቄ አቅርበው ነበር። የኤፈርት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ በየነ መክሩም ባለፈው ሰኔ ወር አጋማሽ ተመሳሳይ ይዘት ያለው ደብዳቤ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጽፈዋል።  

የፍትሕ ሚኒስቴር ለእነዚህ ደብዳቤዎች ይፋዊ ምላሽ ባይሰጥም፤ በሐምሌ 11፤ 2015 ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ወንጀል ጉዳዮች ችሎት ባስገባው ማመልከቻ በኤፈርት ስር ባሉ 21 ድርጅቶች ላይ ተጥሎ የነበረው እግድ እንዲነሳ ጠይቋል። ማመልከቻው የቀረበለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባለፈው አርብ በነበረው የችሎት ውሎ ድርጅቶቹ ላይ ተጥሎ የነበረው እግድ ሊነሳ የማይችልበት “በቂ፣ አሳማኝ እና ህጋዊ ምክንያት የለም” በሚል ውሳኔ አስተላልፏል።  

ፍርድ ቤቱ በዚሁ የችሎት ውሎ ከዚህ ቀደም ለኮሜርሻል ኖሚኒስ የተሰጠው የአስተዳዳሪነት ሹመት እንዲሻርም በይኗል። ችሎቱ ሁለተኛውን ብይን የሰጠው “የእግድ ትዕዛዙ እንዲነሳ ከተደረገ በኋላ የንብረት አስተዳዳሪው ንብረት የማስተዳደር ስልጣኑን ይዞ እንዲቀጥል ማድረግ፤ የንብረት አስተዳዳሪነት ሹመቱ ከተሰጠበት ዓላማ ጋር አብሮ ስለማይሄድ [ነው]” በሚል ምክንያት ነው። በዚህም መሰረት ኮሜርሻል ኖሚኒስ ሲያስተዳድራቸው የቆያቸውን ድርጅቶች ንብረቶች፤ ከፍትሕ ሚኒስቴር የተወከለ ሰው እንዲሁም ታዛቢዎች በተገኙበት “ለህጋዊ ተወካያቸው” እንዲያስረክብ ፍርድ ቤቱ አዝዟል። 

ኮሜርሻል ኖሚኒስ በማስተዳደር ሲሰጥ ለነበረው አገልግሎት “ይገባኛል” የሚለውን አበል እና የድርጅቶቹን የገቢ እና ወጪ ማጠቃለያ ሪፖርት፤ በቀጣይ ቀጠሮ እንዲያቀርብም ችሎቱ ተጨማሪ ትዕዛዝ አስተላልፏል። ኩባንያው የኤፈርት ድርጅቶችን በተመለከተ እንዲያቀርብ የታዘዘውን ማጠቃለያ ሪፖርት ከአንድ ወር ገደማ በፊት ለችሎቱ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም፤ ዐቃቤ ህግ በሰጣቸው አስተያየቶች በድጋሚ ተስተካክሎ እንዲቀርብ ከዚህ ቀደም በነበረ ችሎት ትዕዛዝ ተሰጥቷል። 

ዐቃቤ ህግ፤ በ203 ገጾች ተዘጋጅቶ ለፍርድ ቤት በቀረበው የኮሜርሻል ኖሚኒስ ማጠቃለያ ሪፖርት ላይ ያልተካተቱ ድርጅቶች መኖራቸው እና ሪፖርቱ በግልጽ አለመቅረቡን በማንሳት ነበር አስተያየቱን ለችሎት ያቀረበው። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዐቃቤ ህግ አስተያየትን በመቀበል ሪፖርቱ ለዛሬ ሰኞ ሐምሌ 24፤ 2015 ተሻሽሎ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። ዛሬ ጠዋት በነበረው የችሎት ውሎ የኮሜርሻል ኖሚኒስ ነገረ ፈጅ ባለመገኘታቸው፤ ኩባንያው ሪፖርቱን ለነሐሴ 1፤ 2015 እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)