በአማኑኤል ይልቃል
የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ በአማራ ክልል ከተፈጠረው የጸጥታ መደፍረስ ጋር “ግንኙነት ያላቸው፣ ጉዳዮችን የሚያባብሱ፣ ስምሪት የሚሰጡ” ያላቸውን ግለሰቦችን ከትላንት ምሽት አንስቶ በቁጥጥር ስር ማዋል መጀመሩን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ። ከትላንትና ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ ባለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚወሰዱ እርምጃዎች ጋር በተያያዘ የሚነሱ የሰብአዊ መብት አያያዝ ሁኔታዎችን የሚከታተል አካል እንደሚደራጅም የኮሙኒኬሽን አገልግሎቱ ገልጿል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ይህንን ያስታወቀው፤ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ዛሬ ቅዳሜ ሐምሌ 29፤ 2015 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ፤ በአማራ ክልል ስላለው የጸጥታ ችግር ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደው ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ዶ/ር ለገሰ በዚህ መግለጫቸው በአማራ ክልል የተፈጠረው የጸጥታ መደፍረስ፤ የሰሜኑ ጦርነት የሰላም ስምምነትን “ባልተቀበሉ፣ ጦርነቱን የገቢ ማግኛ እና መክበሪያ አድርገው በወሰዱ፣ ‘የሰላም አማራጮች ጥቅሞቻችን እና ፍላጎታችንን አያሳኩም’ ብለው በገመቱ ወገኖች” ምክንያት የተከሰተ ነው ብለዋል። እነዚህ ግለሰቦች በአማራ ክልል ከተሞች ውስጥ “በትጥቅ የተደገፈ የሰላማዊ ሰልፎች፣ የስርዓት ለውጥ እና ህገ መንግስት የመናድ ተግባራት” ላይ ተሰማርተው ቆይተዋል ሲሉም ወንጅለዋል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ “የዝርፊያ ቡድኖች” ሲሉ የጠሯቸው እነዚህ አካላት፤ “የክልሉን ቁልፍ አመራሮች ማዕከል ያደረገ ግድያ” መፈጸማቸውንም በዛሬው መግለጫቸው ላይ አንስተዋል። “ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ በተለይም በአስተዳደር እርከን ላይ ያሉ፣ እንደዚሁም በጸጥታ ዘርፍ ላይ ያሉ የፖሊስ ኮሚሽነሮች፣ የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊዎች፣ የፓርቲ ኃላፊዎች፣ በርካታ ሰዎች ተገድለዋል” ሲሉም ዶ/ር ለገሰ አክለዋል።
በአማራ ክልል የባለስልጣናት እና ኃላፊዎች ግድያ ጎላ ብሎ መታየት የጀመረው ካለፈው ሚያዝያ ወር አንስቶ ነው። በዚሁ ወር በክልሉ በሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ በሚንቀሳቀሱ “ኢ-መደበኛ ኃይሎች ተፈጽሟል” በተባለ ጥቃት፤ የአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ እና አብረዋቸው ሲጓዙ የነበሩ አራት ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።
በተመሳሳይ ሁኔታ በተፈጸሙ ጥቃቶች ባለፈው ሰኔ ወር ውስጥ ህይወታቸውን ካጡ በአማራ ክልል የጸጥታ ዘርፍ ውስጥ ከሚሰሩ ኃላፊዎች መካከል፤ የደጀን ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ዘውዱ ታደለ እና ምክትላቸው ኢንስፔክተር ወርቁ ሽመልስ ይገኙበታል። እየተጠናቀቀ ባለው ሐምሌ ወር መጀመሪያ ደግሞ የደብረ ብርሃን ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ምንውየለት ጭንቅሎ መገደላቸው አይዘነጋም።
በክልሉ ውስጥ በተለያየ የኃላፊነት ደረጃ ሲያገለግሉ የቆዩ ግለሰቦች የተገደሉት፤ “ባልታወቁ ሰዎች” በደረሰባቸው ጥቃት እንደሆነ ሲገለጽ ቆይቷል። በክልሉ ውስጥ ይህንን አይነት ድርጊት የሚፈጽሙ “ኃይሎችን”፤ በሰላማዊ መንገድ ወደ መደበኛ ስራቸው እንዲመለሱ “በሀገር ሽማግሌዎች የታገዘ የማግባባት ስራ ለረጅም ጊዜ” ሲሰራ መቆየቱን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትሩ በዛሬው መግለጫቸው ላይ ጠቅሰዋል። ሆኖም ይህ የመንግስት ጥረት “አልተሳካም” ብለዋል።
“[የመንግስት] ከመጠን ያለፈ ታጋሽነት እና ለሰላም አማራጮች ብቻ ቅድሚያ መስጠትን፤ መንግስት የተዳከመ ነገር ግን ደግሞ የእነዚህ የዝርፊያ ቡድኖች ጉልበት የፈረጠመ አድርገው በመውሰዳቸው የሚፈጽሙትን ዝርፊያ እና ግድያ እንዲጨምሩ አድርጓቸዋል” ሲሉ ዶ/ር ለገሰ በአማራ ክልል የጸጥታ ችግሩ ተባብሶ የቀጠለበት ነው ያሉትን ምክንያት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። እነዚህ ቡድኖች በሚፈጽሟቸው ጥቃቶች፤ በአማራ ክልል ለሚገኙ አርሶ አደሮች የሚጓጓዙ የግብርና ግብአቶች “መስተጓጎል” አንዳጋጠመ አስረድተዋል።
ቡድኖቹ “የጸጥታ መዋቅሩ በነጻነት ተንቀሳቀሶ ህግ እንዳያስከብር ህጻናትን ከፊት በማሰለፍ መንገድ መዝጋት” እና “የመከላከያ ሰራዊቱን መልካም ዝናዎች እና እሴቶች የማንቋሸሽ” ተግባራትን ሲፈጽሙ ቆይተዋል ሲሉም የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ከስሰዋል። “እነዚህ የጽንፈኛ ቡድኖች እየፈጸሙ ባሉት ጥቃት ምክንያት የክልሉ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰበት መጥቷል” ሲሉም ዶ/ር ለገሰ ተናግረዋል።
ይህ ድርጊት የማይገታ ከሆነ፤ ሀገሪቱን “ለሽብር ቡድኖች፣ ለሰርጎ ገቦች እና በቀጣናው ያሉ የተለያዩ ፍላጎት ላላቸው ኃይሎች ወረራ እና ተጋላጭነት የሚዳርግ” ነው የሚል ድምዳሜ ላይ የፌደራል መንግስት መድረሱን ሚኒስትሩ በዛሬው መግለጫቸው አንስተዋል። ይህ ስጋት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በትላንትናው ዕለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያውጅ ምክንያት መሆኑንም አመልክተዋል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ትላንት አርብ ሐምሌ 28፤ 2015 ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው፤ በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው “በትጥቅ ትግል የተደገፈ ህገ ወጥ እንቅስቃሴ” “በመደበኛ የህግ ማስከበር ስርዓት ለመቆጣጠር ወደ ማይቻልበት ደረጃ እንደተሸጋገረ” በመግለጽ ነበር። ለስድስት ወራት የሚቆየው ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአማራ ክልል እና “እንደአስፈላጊነቱ በየትኛውም ክልል” ተፈጻሚ የሚሆን ነው።
የተለያዩ ክልከላዎችን የጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፤ “በአስቸኳይ ጊዜ መምሪያ ጠቅላይ ዕዝ” የሚመራ እንደሆነ በድንጋጌው ላይ ሰፍሯል። በአዋጁ መሰረት ይህንን ዕዝ የመምራት ኃላፊነት የተጣለባቸው፤ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ ናቸው። አቶ ተመስገን የደህንነት መስሪያ ቤቱን ኃላፊነት ከመረከባቸው በፊት፤ የአማራ ክልልን ለአንድ ዓመት ከሶስት ወር በርዕሰ መስተዳድርነት መምራታቸው ይታወሳል።
ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሆነው የአስቸኳይ ጊዜ መምሪያ ጠቅላይ ዕዝ፤ በትላንትናው ዕለት አስቸኳይ ስብሰባ ማድረጉን ዶ/ር ለገሰ በዛሬው መግለጫቸው ላይ አስታውቀዋል። ከዚህ ስብሰባ በኋላ ራሱን በተለያዩ ክፍሎች አደራጅቶ በይፋ ስራ የጀመረው ዕዙ፤ በአዋጁ መሰረት “የመጀመሪያ የሚባሉ እርምጃዎችን” መውሰድ መጀመሩን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ገልጸዋል። በአማራ ክልል ካጋጠመው የጸጥታ መደፍረስ ጋር “ግንኙነት አላቸው” የተባሉ ግለሰቦችን ከትላንት ምሽት ጀምሮ በቁጥጥር ስር እያዋለ መሆኑንም ዶ/ር ለገሰ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች “ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው፣ ጉዳዮች የሚያባብሱ፣ ስምሪት የሚሰጡ፣ በተለያየ መንገድ ይህንን የሚያባብሱ ኃይሎች” እንደሆኑ ዶ/ር ለገሰ በመግለጫቸው ላይ ዘርዝረዋል። ዕዙ “በቀጣዮቹ ጊዜያት የሚወስዳቸውን እርምጃዎች ለህዝቡ የሚያሳውቅ ይሆናል” ሲሉም ተጨማሪ እርምጃዎች እንደሚኖሩ ጠቁመዋል።
የአስቸኳይ ጊዜውን የደነገገው አዋጅ፤ ጠቅላይ ዕዙ “አስፈላጊ ነው ብሎ ሲያምን” ሊወስዳቸው የሚችላቸውን እርምጃዎች በዝርዝር አስቀምጧል። ከእነዚህ እርምጃዎች ውስጥ የሰዓት እላፊ ማወጅ፣ ሰዎችን በእንቅስቃሴ ገደብ ውስጥ ማቆየት፣ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በማንኛውም ጊዜ እና ስፍራ ብርበራ ማድረግ እንዲሁም የተለያዩ የአስተዳደር እርከኖች እና መዋቅሮችን መልሶ ማቋቋም የሚሉት ይገኙበታል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማዕቀፍ ውስጥ እነዚህ እርምጃዎች በሚወሰዱበት ወቅት የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳይኖር ምን አይነት ጥንቃቄዎች ሊደረጉ እንደታሰቡ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ከጋዜጠኞች ጥያቄ ቀርቦ ነበር። ህግ በማስከበር ስራ ውስጥ የሚከናወን “የተለያዩ አካላትን በቁጥጥር ስር” የማዋል ስራ ለመንግስት አዲስ አለመሆኑን ያነሱት ዶ/ር ለገሰ፤ “በሀገሪቱ ህግ መሰረት፣ የአስቸኳይ ጊዜ በሚደነግጋቸው ህግጋት መሰረት የማንኛውም ሰው ሰብአዊ መብት አይጣስም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዋነኛ አላማ “ህግና ስርዓትን ማስከበር” መሆኑን ጠቅሰው፤ “ከዚያ አልፎ የሰዎችን ስብዕና የማጥፋት፣ መጉዳት እና እነዚህን ሰዎች ባልተፈለገ መንገድ የመቅጣት አላማ የለውም” ሲሉ ድንጋጌውን ተከላክለዋል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚሰበሰብበት ጊዜ የሰብአዊ መብት አያያዝ ሁኔታን በተመለከተ የአዋጁን አፈጻጸም “የሚያጠራ፣ የሚከታተል ኃይል” እንደሚያደራጅ የጠቆሙት ዶ/ር ለገሰ፤ በአዋጁ አፈጻጸም ላይ የሰብአዊ መብት ጉዳይ “ብዙ ችግር ያመጣል ተብሎ የሚወሰድ አይደለም” ሲል ስጋቱን አጣጥለውታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)