በአማራ ክልል ከተከሰተው የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ከተማ “በትምህርት ቤቶች” እና “በተለያዩ ቦታዎች” የታሰሩ ሰዎች መኖራቸውን የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም አመኑ። በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸው በይፋ ከተገለጹ ግለሰቦች ውጭ ያሉ እስሮች የተፈጸሙት፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንጂ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ (ኮማንድ ፖስት) አለመሆኑንም ገልጸዋል።
የሰላም ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ የታሰሩ ሰዎችን በተመለከተ ማረጋገጫ የሰጡት፤ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ጋር ከትላንት በስቲያ ሰኞ ነሐሴ 8፤ 2015 ባደረጉት ውይይት ላይ ይህንኑ አስመልክቶ ለተነሱላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስ ነው። አቶ ብናልፍ እና የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል የመሩት ይህ ስብሰባ የተካሄደው፤ በአማራ ክልል የተከሰተውን የጸጥታ ችግር አስመልክቶ ለፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮቹ ገለጻ ለማድረግ ነበር።
ሶስት ሰዓት ከ40 ደቂቃ ገደማ በፈጀው በዚህ ስብሰባ ላይ፤ ሁለቱ ሚኒስትሮች ያቀረቡትን ገለጻ ተከትሎ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ሀሳብ እና ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል። በሰኞው ስብሰባ ላይ ከታደሙ 16 የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ውስጥ ጥያቄም ሆነ አስተያየት ያላቀረቡት ሁለት ተሳታፊዎች ብቻ ናቸው። አብዛኛዎቹ ተሳታፊዎች በአማራ ክልል ለተከሰተው ግጭት መንግስት ጥፋተኛ ሲያደርጉ ተደምጠዋል። መንግስት በክልሉ ላለው ችግር አስቀድሞ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ “ጉዳዩን በኃይል ለመፍታት ሞክሯል” ሲሉም ወቅሰዋል።
ይህንን ወቀሳ ካሰሙት አንዱ የሆኑት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ዋና ጸሀፊ አቶ አበበ አካሉ፤ ፓርቲያቸው በሚያወጣቸው መግለጫዎች ሲነሱ የነበሩ ችግሮች እና ስጋቶችን መንግስት “ችላ” እንዳለ በማንሳት ተችተዋል። ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የወጡ የአቸኳይ ጊዜ አዋጆች “ለውጥ እንዳላመጡ” የገለጹት አቶ አበበ፤ በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ለተከሰተው ችግር መፍትሔው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገግ ሳይሆን “ሰላማዊ ድርድር” ማካሄድ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት “የጅምላ እስር ከፍቷል” ያሉት የኢዜማ ዋና ጸሀፊ፤ በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ ላይ የሚገኙ የፓርቲው አመራሮች “በጅምላ” መታሰራቸውን ለዚህ በማሳያነት ጠቅሰዋል። የአዋጁ መውጣት በተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ አመራሮች “ትላንት የጠሉትን ሰው ለማሰር” ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረም አክለዋል። ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ እስሮች ጉዳይ፤ በኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ህብረት (ኢዲህ) ሊቀመንበር አቶ ገብሩ በርሄም ተነስቷል።
“በአዲስ አበባ ከፍተኛ አፈሳ ነው ያለው። ብዙ ህዝብ እየታሰረ ነው። ተጭነው የሄዱ የእኛ አባሎች አሉ” ሲሉ አቶ ገብሩ በመዲናዋ “እየተፈጸመ ነው” ስላሉት “የጅምላ እስር” በምሳሌ በማስደገፍ አስረድተዋል። “ትምህርት ቤቶች የታፈሱ [ሰዎች] ማጎሪያ ሆነው ነው የሰነበቱት” ያሉት የኢዲህ ሊቀመንበር፤ የፓርቲያቸው አባላት በደጃዝማች ወንድይራድ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ታስረው መቆየታቸውን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ በርካታ ሰዎች በዚህ መልክ እየታሰሩ ቢሆንም፤ በመንግስት በኩል ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተሰጠ መግለጫ የታሰሩት 23 ግለሰቦች መሆናቸው መገለጹ ጥያቄ እንደፈጠረባቸውም አቶ ገብሩ ተናግረዋል። በመግለጫው ከተጠቀሱት ሰዎች ውጭ “የያዝነው የለም ከተባለ፤ ማነው ታዲያ እነዚህን ሰዎች እየያዛቸው ያለው?” ሲሉ የሰኞውን ውይይት የመሩትን ሚኒስትሮች ጠይቀዋል።
የኢዲህ ሊቀመንበር በጥያቄያቸው ላይ የጠቀሱት መግለጫ የተሰጠው ባለፈው አርብ ነሐሴ 5፤ 2015 ነበር። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዲያስፈጽም የተቋቋመው ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ በሰጠው በዚህ መግለጫ፤ በአማራ ክልል የተፈጠረውን ግጭት “ለማባባስ ግዳጅ በመውሰድ በከተማ ውስጥ ሆነው የተለያዩ ህገወጥ ተግባራትን ሲፈጽሙ ነበር” የተባሉ 23 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር መዋላቸውን ገልጾ ነበር። ዕዙ በዕለቱ ይፋ ካደረገው የግለሰቦቹ ዝርዝር ውስጥ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባሉ ዶ/ር ካሳ ተሻገር እና ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው ተካትተዋል።
ከ23ቱ ተጠርጣሪዎች ውጪ በአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስቱ የተያዘ ሰው አለመኖሩን የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ መናገራቸው ይታወሳል። እርሳቸው ይህን ቢሉም፤ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ግን በአዲስ አበባ ከተማ “የአማራ ክልል ተወላጆች” እና ኤርትራውያን ስደተኞች “በስፋት” በቁጥጥር ስር እየዋሉ እና እየታሰሩ መሆኑን ከትላንት በስቲያ ሰኞ ባሰራጨው መግለጫ አስታውቋል።
በቁጥጥር ስር ስለዋሉ ታሳሪዎች ከቤተሰቦቻቸው እና ከጓደኞቻቸው በርካታ ሪፖርቶች እንደደረሰው የገለጸው ኢሰመኮ፤ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጅ በኋላ ታሳሪዎች ያሉበትን ሁኔታ ለመመልከት የሚያስችል ፈቃድ አለማግኘቱን በመግለጫው አመልክቷል። ብሔራዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም በመግለጫው የጠቀሰው እና በሰኞው ውይይት የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ያነሱት የበርካታ ሰዎች መታሰር ጉዳይ ትክክል መሆኑን ማረጋገጣቸውን የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ እና የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ በስብሰባው ላይ ተናግረዋል።
ይህን ጉዳይ አስመልክቶ በመንግስት ደረጃ ንግግሮች መደረጋቸውን ያነሱት ሁለቱ ሚኒስትሮች፤ እስሮቹ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ሳይሆን “በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር” የተፈጸሙ መሆኑን ለፓለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች አስረድተዋል። “ሚዲያ ላይ መግለጫ የተሰጠው ኮማንድ ፖስቱ የያዛቸውን ነው። ግን ከዚያ በላይ ብዙ የታሰሩ አሉ፤ በተለይ አዲስ አበባ ያሉ። ቅድም ባላችኋቸው በኮከበ ጽብሃ [ትምህርት ቤት]፣ በተለያዩ ቦታዎች ላይ የታሰሩ አሉ” ሲሉ የሰላም ሚኒስትሩ በርካታ ሰዎች ለመታሰራቸው ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
“ዞሮ ዞሮ ህዝቡ ማን አሰራቸው የሚለውን አይደለም የሚያየው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስቱ አሰራቸው፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አሰራቸው፤ ለህዝቡ ልዩነት የለውም። ምክንያቱም የህዝቡ ጥያቄ ሰው አይታሰር ነው። ሰው አይታሰር ስለሆነ፤ ሁሉም ነው ማቆም ያለበት” ሲሉ አቶ ብናልፍ ለውይይቱ ተሳታፊዎች ተናግረዋል። የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩም ይህኑ የሚያጠናክር ሃሳብ ሰንዝረዋል።
“የአስቸኳይ ጊዜ የታወጀው የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ነው። ከዚያ ባሻገር ግን ሰው በማንነቱ፣ በፖለቲካ አመለካከቱ፣ የሚታሰርባትን ኢትዮጵያ መልሰን የምናይ ከሆነ የተረጋጋ ሀገር ሊኖረን አይችልም”
አቶ መላኩ አለበል፤ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር
“ዋናው ግብረ ኃይል ላይ የተፈጸመ ሳይሆን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኩል የተፈጸመ እንደሆነ ሰምተናል። ነገር ግን አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ያው የብልጽግና አካል ስለሆነ እዚያ አካባቢ ላይ ያሉ ችግሮች እንዲታረሙ እናደርጋለን” ሲሉ አቶ መላኩ ቃል ገብተዋል። “የአስቸኳይ ጊዜ የታወጀው የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ነው። ከዚያ ባሻገር ግን ሰው በማንነቱ፣ በፖለቲካ አመለካከቱ፣ የሚታሰርባትን ኢትዮጵያ መልሰን የምናይ ከሆነ የተረጋጋ ሀገር ሊኖረን አይችልም” ሲሉም የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የሰዎችን እስር በተመለከተ ያለውን ችግር ለመፍታት “የኮማንድ ፖስት አመራሮች ባሉበት” ንግግር በመደረጉ፤ ጉዳዩ እልባት ያገኛል የሚል እምነት እንዳላቸው አቶ መላኩ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ተናግረዋል። የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍም “በተለያየ ምክንያት የታሰረ ብዙ ሰው ስላለ ይሄ መቆም አለበት” በሚል ግምገማ መደረጉን አረጋግጠዋል። “ወንጀለኛ ካለ አስረው ፍርድ ቤት ነው ማቅረብ ያለባቸው እንጂ ትምህርት ቤት ላይ አይደለም አጉረው እስረኛ ማስቀመጥ ያለባቸው። ይሄ መታረም ያለበት እንደሆነ በጋራ ውይይት የተደረገበት እና ውሳኔ የተደረገበት ነው” ሲሉ የመንግስትን አቋም አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)