በሃሚድ አወል
የ“ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች” የሚለውን ስያሜውን ወደ “ማዕከላዊ ኢትዮጵያ” የቀየረው ነባሩ ክልል፤ አቶ እንደሻው ጣሰውን በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የክልሉ ፕሬዝዳንት አድርጎ ሾመ። የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል የነበሩት አቶ እንደሻው፤ ከዚህ ሹመት አስቀድሞ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ሆነው በመስራት ላይ ነበሩ።
የ“ማዕከላዊ ኢትዮጵያ” ክልል ምክር ቤት ሹመቱን የሰጠው ዛሬ ቅዳሜ ነሐሴ 13፤ 2015 እያካሄደ ባለው አስቸኳይ ጉባኤው ነው። በትላንትናው ዕለት በተጀመረው በዚሁ የክልሉ ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤ ላይ፤ ነባሩን ክልል ወደ “ማዕከላዊ ኢትዮጵያ” የሚቀይረው የህገ መንግስት ማሻሻያ ጸድቋል።
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ስር የነበሩ መዋቅሮች ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት በተካሄዱ ህዝበ ውሳኔዎች ራሳቸውን የቻሉ ሶስት ክልሎች መመስረታቸውን ተከትሎ፤ ነባሩ ክልል የስያሜ፣ የአደረጃጃት መዋቅር እና ህገ መንግስት ማሻሻያ አድርጎ እንደሚቀጥል መገለጹ ይታወሳል። ነባሩ ክልል ከህገ መንግስቱ ማሻሻያ በተጨማሪ የአስተዳዳሪ ለውጥም አድርጓል።

ክልሉን ላለፉት አራት ዓመታት በምክትል ርዕሰ መስተዳድርነት እና በርዕሰ መስተዳደርነት ሲመሩት የቆዩት አቶ ርስቱ ይርዳው፤ ከስልጣናቸው ተነስተው የቀድሞው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል አቶ እንዳሻው ኃላፊነቱን ተረክበዋል። አቶ ርስቱ በ2011 ዓ.ም የደቡብን ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድርነት እንዲመሩ የተሾሙት አቶ ሚሊዮን ማቲዎስን በመተካት ነበር።
ለዚህ የስልጣን መተካካት ምክንያት የሆነው፤ በወቅቱ ክልሉን ሲያስተዳድር የነበረው የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ “የርዕሰ መስተዳድር ለውጥ እንዲደረግ” ውሳኔ በማስተላለፉ ነው። አቶ ርስቱ ክልሉን የማስተዳደር ኃላፊነት ከመረከባቸው በፊት፤ በተለያዩ የክልሉ የመንግስት ስልጣን እርከኖች ላይ አገልግለዋል።
ከጉራጌ ዞን አስተዳዳሪነት የጀመረው የአቶ ርስቱ የአመራርነት ድርሻ እስከ ሚኒስትርነት የዘለቀ ነው። አቶ ርስቱ በጥቅምት 2009 ዓ.ም የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስትር በመሆን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ካቢኔ ተቀላቅለዋል። በዚህ የኃላፊነት ቦታ ለሁለት ዓመታት ያህል የቆዩት አቶ ርስቱ፤ ሲመሩት በነበረው የሚኒስቴር መስሪያ ቤት ላይ የአደረጃጀት ለውጥ ሲደረግ የፌደራል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው ተሹመዋል።

በስፖርት ኮሚሽነርነት ስምንት ወራት ብቻ ያገለገሉት አቶ ርስቱ፤ በነሐሴ 2011 ዓ.ም የደቡብ ክልልን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ እንዲመሩ ተሹመዋል። በስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ የደቡብ ክልል ምክር ቤት አባል ሆነው የተመረጡት አቶ ርስቱ፤ በመስከረም 2014 ዓ.ም. የክልሉ መንግስት ምስረታ ሲከናወን የርዕሰ መስተዳደር ሹመትን አግኝተዋል።
አቶ ርስቱ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል በስልጣን ላይ የቆዩባቸው አራት ዓመታት ለእርሳቸው ፈታኝ ነበሩ። እርሳቸው የተወከሉበት የጉራጌ ዞንን ጨምሮ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች፤ በክልል የመደራጀት ጥያቄዎች ጎልተው የተሰሙበት እና በአንዳንድ አካባቢዎችም በዚሁ ምክንያት የሰዎች ህይወት እስከ መጥፋት ያደረሱ ተቃውሞዎች የተስተናገዱበት ነበር።
በደቡብ ክልል ያለው ራስን ችሎ በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ በጉራጌ እና በወላይታ ዞኖች አሁንም ጎልቶ የሚደመጥ ቢሆንም፤ በአቶ ርስቱ የስልጣን ዘመን ከነባሩ ክልል የተነጠሉ መዋቅሮች ሶስት ክልሎች ተመስርተዋል። በህዝበ ውሳኔ ክልል በመመስረት ቀዳሚው የቀድሞው የሲዳማ ዞን ነው። በደቡብ ክልል የነበሩ አምስት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ “የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች” የተሰኘ አዲስ ክልል በተመሳሳይ ሂደት በመመስረት ተከታይ ሆነዋል።
ከነባሩ ክልል በመነጠል ሶስተኛውን ክልል በህዝበ ውሳኔ የመሰረቱት ደግሞ በደቡብ ክልል ስር የነበሩ፤ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች ናቸው። አቶ ርስቱ ሲመሩት የነበረው የደቡብ ክልል፤ ፌዴሬሽኑን በመቀላቀል 12ኛ ለሆነው አዲሱ ክልል ስልጣን ያስረከበው ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር። በወልቂጤ ከተማ በዛሬው ዕለት በተካሄደ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስቸኳይ ጉባኤ ላይ ደግሞ ራሳቸው አቶ ርስቱ ስልጣናቸውን ለአዲስ ተሿሚ አስረክበዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስተዳዳሪነትን የተረከቡት አቶ እንደሻው፤ በብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት እና በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በአመራርነት ለአምስታት ዓመታት ሰርተዋል። አቶ እንደሻው ወደ ፌደራል የኃላፊነት ቦታ ከመዘዋወራቸው በፊት በአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ለስድስት ወራት ያህል በኃላፊነት አገልግለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሏል]