ሶማሊያ፤ ከኢትዮጵያ እና ከሌሎች ጎረቤቶቿ ጋር በመሆን በአልሻባብ ላይ ዘመቻ ልታካሄድ ነው   

የሶማሊያ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ጅቡቲ መሪዎች፤ በቁልፍ የአልሻባብ ይዞታዎች ላይ ያነጣጠረ ጠንካራ ዘመቻ “በጋራ ለማቀድ እና ለማከናወን” ከስምምነት ላይ ደረሱ። የአራቱ ሀገራት መሪዎች፤ “በሽብርተኞች” ቁጥጥር ስር የሚገኙ አካባቢዎች “ነጻ የሚያወጣ” እና “የመጨረሻ” የተባለለትን ዘመቻ ለማካሄድ መስማማታቸውን አስታውቀዋል። 

አልሻባብ ከ16 ዓመታት በላይ ያመሳት ሶማሊያ እና ጎረቤቶቿ በጋራ ሊያከናውኑት ያቀዱት ዘመቻ ይፋ የተደረገው፤ በዛሬው ዕለት በሞቃዲሾ ከተደረገ የአራት ሀገራት መሪዎች ጉባኤ በኋላ ነው። የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ መሐሙድ በመሩት በዚህ ጉባኤ ላይ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፣ የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ እና የጅቡቲ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጉሌህ ተሳትፈዋል።

የመሪዎቹ ጉባኤ ሲጠናቀቅ የወጣው መግለጫ፤ አራቱ ሀገራት በአልሻባብ ላይ “ጠንካራ ዘመቻ” ለመጀመር መስማማታቸውን ይፋ አድርጓል። አራቱ ሀገራት ከዚህ ስምምነት ላይ የደረሱት፤ የሶማሊያ ጦር በአልሻባብ ላይ በጀመረው ዘመቻ ጎረቤት አገራት “ጉልህ ተሳትፎ እንዲያደርጉ” የፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ መሐሙድ መንግስት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ነው።  

በዛሬው ጉባኤ፤ የሀገራቱ መሪዎች በአልሻባብ ላይ ያነጣጠረ “ቁርጠኛ የዘመቻ ስልት በጋራ ማቀድ” እና “ቀጠናዊ ድጋፍ ማሰባሰብ” አስፈላጊ እንደሆነ አጽንኦት መስጠታቸው በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል። አራቱ መሪዎች “ጠላት” ያሉት አልሸባብን “ለመግታት እና ለማሸነፍ” የሚደረጉ ዘመቻዎችን እና ሁለንተናዊ አቅሞችን የሚያስተባብር፤ የጋራ ስርዓት እንዲቋቋም መወሰናቸው ከሞቃዲሾው ጉባኤ በኋላ ይፋ የሆነው መግለጫ ይጠቁማል። 

አዲስ ቅጥር ወታደሮችን ለማስታጠቅ እና የሶማሊያ ብሔራዊ ጦርን የመሳሪያ አቅም ለማሳደግ፤ የሶማሊያ መንግስት ያቀረበውን ጥሪ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ጅቡቲ በበጎ መቀበላቸውን መግለጫው አትቷል። የአራቱ አገሮች ዕቅድ፤ በአፍሪካ ህብረት ስር ወደ ሶማሊያ የዘመቱ ሰላም አስከባሪ ወታደሮችን ቁጥር ቀስ በቀስ በመቀነስ፤ በሂደት የጸጥታ ጥበቃ ኃላፊነቶችን ለሀገሪቱ የጸጥታ ጥበቃ ተቋማት ማሸጋገርን ጭምር ያካተተ ነው።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት፤ የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ወታደሮች ወደ ሶማሊያ እንዲልክ ውሳኔ ያሳለፈው በ1999 ዓ.ም ነበር። “አሚሶም” በሚል ምህጻረ ቃል ይበልጥ በሚታወቀው በአፍሪካ ህብረቱ ተልዕኮ ስር የሚሰማሩ ወታደሮች፤ በሶማሊያ እንዲቆዩ የታሰበው ለስድስት ወራት ያህል ጊዜ ነበር። ሆኖም ተልዕኮው ላለፉት 15 ዓመታት በሀገሪቱ የሰላም ማስከበር ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል። 

በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ (ATMIS) የተባለ የሰላም አስከባሪ ኃይል፤ አሚሶምን በመጋቢት 2014 እንዲተካው ተደርጓል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት እና በአፍሪካ ህብረት የሰላም እና ጸጥታ ምክር ቤት የጋራ ውሳኔ የተቋቋመው ይህ ተልዕኮ፤ ወታደሮች፣ ፖሊሶች እና ሲቪሎችን ጭምር ያካተተ ነው።

በዚህ ተልዕኮ ስር የተካተቱ፤ ከኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ጅቡቲ፣ ኡጋንዳ እና ቡሩንዲ የተውጣጡ ወታደሮች፤ በማዕከላዊ እና ደቡብ እና  ሶማሊያ ተሰማርተው ይገኛሉ። ይህ የሶማሊያ ክፍል፤ በዛሬው የሞቃዲሾ ጉባኤ የተሳተፉ የአራት ሀገራት መሪዎች በበርካታ ግንባሮች ያቀዱት አልሸባብን “አስሶ የማጥፋት ዘመቻ” የሚከናወንበት ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)