የኢትዮጵያ የግማሽ ዓመት የወጪ ንግድ ገቢ፤ 6.9 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱ ተገለጸ 

በሃሚድ አወል

የመንፈቅ ዓመቱ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ (export) ገቢ፤ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ6.9 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ። መስሪያ ቤቱ በስድስት ወራት ውስጥ ለተጠቃሚዎች ለማቅረብ በዕቅድ ከያዘው 1.67 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ማቅረብ የቻለው፤ 26.7 በመቶ ብቻ መሆኑንም ሚኒስትሩ አቶ ገብረመስቀል ጫላ ተናግረዋል። 

አቶ ገብረመስቀል ይህን ያሉት የመስሪያ ቤታቸውን የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት ነው። ሚኒስትሩ ለፓርላማው ያቀረቡት ሪፖርት ዋነኛ ትኩረቱን ያደረገው፤ በፍጆታ ዕቃዎች አቅርቦት፣ በነዳጅ ድጎማ እና በወጪ ንግድ ላይ ነበር። 

የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ በዚሁ ሪፖርታቸው፤ ባለፉት ስድስት ወራት ከወጪ ንግድ 2.296 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 1.7 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት ያገኘችው ገቢ በዕቅድ ከተያዘው 76.7 በመቶው ያሳካ እንደሆነ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል። ገቢው ከ2014 ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር፤ በ131.9 ሚሊዮን ዶላር ያነሰ መሆኑንም አክለዋል። 

ከወጪ ንግድ ከተገኘው ገቢ የ77.2 በመቶ ድርሻውን በመያዝ ቀዳሚ የሆነው፤ የግብርና ዘርፉ ነው። የኢንዱስትሪ እና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ 10 በመቶ ድርሻ በማበርከት ይከተላል። የማዕድን ዘርፍ ደግሞ 6.6 በመቶ ድርሻ አለው። 

የሀገሪቱ የወጪ ንግድ አፈጻጸም ካለፈው ዓመት ከነበረው ቅናሽ ማሳየቱ፤ በተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጥያቄ አስነስቷል። አጸደ ማሞ የተባሉ የፓርላማ አባል፤ ያለፉት ስድስት ወራት “አንጻራዊ ሰላም ያለበት እና ከጦርነትም በመጠኑ ቢሆን የተሻለ ጊዜ” እንደነበር ጠቅሰው፤ የወጪ ንግዱ የቀነሰበትን ምክንያት ጠይቀዋል።

የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዲኤታው አቶ ካሳሁን ጎፌ ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ “የኮንትሮባንድ ንግድ መበራከት እና የህግ ወጥ ንግድ መጧጧፍ” የወጪ ንግድ ስራውን “ፈታኝ አድርጎታል” ብለዋል። “ኮንትሮባንዲስቶችን ለመቆጣጠር ጥረቶች ቢኖሩም፤ ቀጠናው ለኮንትሮባንድ ንግድ የተመቸ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ጉዳዩን አስቸጋሪ እና አሳሳቢ አድርጎታል” ሲሉም ሚኒስትር ዲኤታው ለገቢው መቀነስ ዋነኛ አስተዋጽኦ አለው ያሉትን ችግር አስረድተዋል። 

ፎቶ፦ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር

በወጪ ንግድ “ዘንድሮ ብዙ ተግዳሮት ገጥሞናል” ሲሉ ለፓርላማ አባላቱ የተናገሩት የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል፤ የወጪ ንግድ የቀነሰባቸውን ተጨማሪ ምክንያቶችን አብራርተዋል። “ሰሊጥ የሚያመርቱ አካባቢዎች ላይ በተለይ ጦርነት ስለነበር፤ በቅባት እህሎች ላይ የምርት እጥረት አጋጥሞናል” ያሉት ሚኒስትሩ፤ “የዓለም የገበያ መዋዠቅ” ለገቢው መቀነስ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቅሰዋል። 

አቶ ገብረመስቀል በዛሬው ሪፖርታቸው ያነሱት ሌላኛው ጉዳይ፤ የፍጆታ ዕቃዎች አቅርቦት የስራ አፈጻጸምን ነው። ለሀገር ውስጥ ገበያ ባለፉት ስድስት ወራት 1.67 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ለማቅረብ ቢታቀድም፤ ማቅረብ የተቻለው 445,537 ኩንታል ብቻ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ይህ የስኳር አቅርቦት በዕቅድ ከተያዘው 26.7 በመቶውም ብቻ የሚሸፍን ነው። 

ለስኳር አቅርቦት አፈጻጸም ማነስ በሚኒስትሩ በምክንያትነት የተጠቀሱት ሁለት ጉዳዮች ናቸው። የመጀመሪያው ምክንያት “ከውጭ በግዢ እንዲገባ የተፈቀደው ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ስኳር በዓለም ገበያ መናር እና በግዢ መጓተት ምክንያት በወቅቱ አለመግባቱ” መሆኑን አቶ ገብረመስቀል ተናግረዋል። “የሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች፤ በጸጥታ ችግር ምክንያት ባላቸው አቅም ልክ ስኳር ማምረት አለመቻላቸው” በሚኒስትሩ በሁለተኛ ምክንያትነት የቀረበ ነው። 

ሚኒስትሩ ይህን ቢሉም የፓርላማ አባላቱ ግን፤ ስኳርን ጨምሮ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚከፋፈሉ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች “የፍትሃዊነት እና ተደራሽነት ችግር ይስተዋልባቸዋል” የሚል ትችት አቅርበዋል። አስቻለ አላምሬ የተባሉ የፓርላማ አባል፤ የፍጆታ እቃዎች ስርጭት ተደራሽ እና ፍትሃዊ አለመሆኑን፤ የተወካዮች ምክር ቤት የንግድ እና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በመስክ ምልከታ ማረጋገጡን ለሚኒስትሩ ገልጸዋል። 

የፓርላማው አባል “በተለይ የስኳርና እና ዘይት ስርጭት የፍትሃዊነት እና የተደራሽነት ችግር ብቻ ሳይሆን፤ አፈጻጸሙም ዝቅተኛ ነው። ይህን ችግር ለመቅረፍ ምን እየተሰራ ነው?” ሲሉ በዛሬው ስብሰባ ላይ ለተገኙ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስራ ኃላፊዎች ጥያቄ አቅርበዋል። የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዲኤታው አቶ ተሻለ በልሁ ለጥያቄው በሰጡት ምላሽ፤ ስኳር ከውጭ በግዢ እና ከሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች ከሚያመርቱት ለተጠቃሚዎች እንደሚሰራጭ አስታውሰው፤ “በሁለቱም በኩል ክፍተት መፈጠሩን” ተናግረዋል። 

የሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች ወደ ማምረት የተመለሱት “ባለፈው ወር ነው” መሆኑን የገለጹት አቶ ተሻለ፤ በኢትዮጵያ ያሉ ፋብሪካዎች ስኳር “በበቂ ሁኔታ እያመረቱ” አለመሆኑን አብራርተዋል። ሚኒስትሩ አቶ ገብረመስቀል በበኩላቸው፤ “ፍትሃዊነትን በተመለከተ የሚከፋፋለው ዘይት እና ስኳር መጠን በጣም ትንሽ ነው። የሚፈልገው ህዝብ [ደግሞ] በጣም ብዙ ነው። ምንም ፍትሃዊ እንሁን ብንል እንቸገራለን” ሲሉ የአቅርቦት እና ፍላጎት ልዩነት መኖሩን ለአባላቱ አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)