የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ውይይትን የተቃወሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ስብሰባ ረግጠው ወጡ 

በሃሚድ አወል

የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አማራጮችን በተመለከተ በትላንትናው ዕለት በአዲስ አበባ ሲካሄድ በዋለው ውይይት ላይ ከታደሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ውስጥ የተወሰኑት፤ ስብሰባውን በተቃውሞ ረግጠው ወጡ። ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ተቃውሟቸውን የገለጹት፤ ከሽግግር ፍትሕ በፊት “የሀገራዊ ምክክር ሊቀድም” እና “ግጭቶች ሊቆሙ ይገባል” በሚሉ ሁለት ምክንያቶች ነው።  

የፖለቲካ ፓርቲዎቹን ትላንት አርብ መጋቢት 1፤ 2015 ለስብሰባ የጠራው፤ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አዘጋጅ የባለሙያዎች ቡድን ነው። የባለሙያዎቹ ቡድኑ የውይይት መድረክ ያዘጋጀው፤ ለሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ዝግጅት ግብዓቶችን ለማሰባሰብ መሆኑን ገልጿል። ቡድኑ ባለፈው ረቡዕ የመጀመሪያውን የግብዓት ማሰባሰቢያ ውይይት፤ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጋር አካሄዷል።

በአዲስ አበባው ኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተካሄደው በትላንቱ ውይይት ላይ፤ የባለሙያዎች ቡድኑ አባላት የሽግግር ፍትሕን በተመለከተ ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የባለሙያዎች ቡድን አባል የሆኑት አቶ ምስጋናው ሙሉጌታ “የሽግግር ፍትሕ ጽንሰ ሃሳብ እና የኢትዮጵያን ተሞክሮ” ለተሳታፊዎች ያብራሩ ሲሆን፤ ሌላኛዋ የቡድኑ አባል ቃልኪዳን ደረጀ ደግሞ “የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ ማዕቀፍ አማራጮች” ስለቀረቡበት ሰነድ ገለጻ አድርገዋል።

ከባለሙያዎቹ ገለጻ በኋላ የመናገር ዕድል ያገኙ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተወካዮች፤ ጠንከር ያሉ አስተያየቶችን ሰጥተዋል። በፓርቲዎቹ የተሰጡ አስተያየቶች፤ የሽግግር ፍትሕ ወቅታዊነት፣ የብሔራዊ ምክክሩ በጉዳዩ ላይ ሊኖረው ስለሚገባው ሚና እና በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ያሉ ግጭቶችን የተመለከቱ ነበሩ።  

የሲዳማ ፊደራሊስት ፓርቲ (ሲፌፓ) ሊቀመንበር አቶ ተሰማ ኤሊያስ፤ “መጀመሪያ መቅደም ያለበት ብሔራዊ መግባባት” ነው ሲሉ በሂደት ላይ ያለው ሀገራዊ ምክክር ከሽግግር ፍትሕ ሊቀድም እንደሚገባ ተናግረዋል። አቶ ተሰማ አክለውም “ችግሮቻችን ፖለቲካ ወለድ ናቸው እንጂ ከፍትሕ ጋር ብቻ የሚገናኙ አይደለም። ስለዚህ የፖለቲካ ንግግሮች ሳይቀድሙ፤ የፍትሕ ጉዳይ መምጣቱ ችግር አይሆንም ወይ?” የሚል ጥያቄ አቅርበዋል። በትላንቱ ስብሰባ የተሳተፉ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችም ከአቶ ተሰማ ጋር የተመሳሰለ አስተያየት ሰጥተዋል። 

ፎቶ:- ከEBS ቴሌቪዥን

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዝዳንት አቶ ማሙሸት አማረ፤ የሽግግር ፍትሕ “የምክክር ኮሚሽኑ አጀንዳ ነው” የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል። “የሽግግር ፍትሕ ከምክክር ኮሚሽኑ አንድ ዘርፍ ሆኖ መምጣት የሚገባው ነው። ብቻውን ራሱን ችሎ ሊቆም አይችልም” ሲሉ በአጽንኦት ተናግረዋል። አቶ ማሙሸት የሽግግር ፍትሕ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ስር እንዲሆን ላቀረቡት ምክረ ሃሳብ፤ “የፍትሕ ስርዓቱ ተዓማኒነት እና የህዝብ ቅቡልነት የሌለው” መሆኑን በምክንያትነት ጠቅሰዋል። 

የፍትሕ ሚኒስቴር ባለፈው ታህሳስ ወር መጨረሻ ላይ ይፋ ያደረገው “በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ ማዕቀፍ አማራጮችን” የያዘው ሰነድ፤ ሶስት አበይት ጉዳዮች በሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ እንዲከናወኑ አማራጭ አቅርቧል። የምክክር ኮሚሽኑ እንዲያከናውናቸው በአማራጭነት የቀረቡት ሶስት ጉዳዮች፤ “እውነትን ማጣራት፣ እርቅ እና የማካካሻ ስርዓት” ናቸው። በሰነዱ ላይ የቀረበው ሌላኛው አማራጭ፤ እነዚህ ሶስት ጉዳዮች ለማከናወን “አዲስ ኮሚሽን ይቋቋም” የሚል ነው። 

ከፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የባለሙያዎች ቡድን አባሉ አቶ ምስጋናው፤ በሀገራዊ ምክክር እና የሽግግር ፍትሕ መካከል ያለውን ልዩነት አስረድተዋል። “ሁለቱ የሚዛመዱ ሂደቶች መሆናቸው ግልጽ ነው። ነገር ግን አንድ አይነት አይደሉም” ያሉት አቶ ምስጋናው፤ “የሽግግር ፍትሕ ሂደት፤ በሀገራዊ ምክክር ሊታይ እና ሊታቀፍ የማይችል የprosecution ባህሪ ያለው ነው” ሲሉ ልዩነቱን አብራርተዋል። 

“የሽግግር ፍትሕ ጊዜ የማይሰጥ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። የምክክር ሂደቱ እስኪያልቅ ድረስ ጠብቆ የሚካሄድ ከሆነ፤ ሀገሪቷ ብዙ ነገር ልታጣ ትችላለች የሚል ፍራቻ አለን” ሲሉም የባለሙያዎች ቡድን አባሉ “ምክክር መቅደም አለበት” በሚል ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል። በትላንቱ ውይይት የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፤ ከሽግግር ፍትሕ በፊት “በሀገሪቱ እየተከሰቱ ያሉ ጥቃቶች ሊቆሙ ይገባል” ሲሉም ቅድመ ሁኔታ አቅርበዋል።

ይህን ሃሳብ ያስተጋቡት የመኢአዱ ፕሬዝዳንት፤ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አማራጮችን የያዘው ሰነድ የቀረበው “ከአውዱ ውጭ” መሆኑን ገልጸዋል። በሀገሪቷ ውስጥ “ሞት፣ መፈናቀል እና ጥቃት” መኖሩን ያስታወሱት አቶ ማሙሸት፤ “በቅድሚያ እነዚህ ድርጊቶች ሊቆሙ ይገባል” ብለዋል፡፡ የሽግግር ፍትሕ ውይይት መደረግ ያለበት “ችግሮች ጋብ ካሉ በኋላ” መሆን እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል። 

አቶ አዲሱ ሀረገወይን የተባሉ አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልም፤ ከሽግግር ፍትሕ በፊት “ጥቃት መቆም የለበትም ወይ?” ሲሉ ተመሳሳይ ሃሳብ አንጸባርቀዋል። የአብን ተወካዩ “ዓለም አቀፍ ወንጀሎች የምንላቸው እየተፈጸሙ ባለበት ሀገር ውስጥ [ድርጊቶቹ] ፋታ እንዳገኙ ተቆጥሮ ወደ ሽግግር ፍትሕ መግባት የምንችልበት ጊዜ ነው ወይ?” የሚል ተጨማሪ ጥያቄም ሰንዝረዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የሽግግር ፍትሕ ሂደት ለመጀመር ዝግጅት እያደረገ  ያለው “ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡን ለማባበል ነው” የሚል እምነት እንዳላቸው በውይይቱ ላይ የገለጹት አቶ አዲሱ፤ “መንግስት ካጋጠመው ዓለም አቀፍ ቅቡልነት ችግር አንጻር ካልሆነ በስተቀር ይህን ያህል ፋይዳ አለው ብዬ አላስብም” ሲሉ ሂደቱን አጣጥለዋል። የአገው ብሔራዊ ሸንጎ ሊቀመንበር አቶ አላምረው ይርዳውም ከዚሁ ጋር የተመሳሰለ አስተያየት አስደምጠዋል። 

ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የባለሙያዎች ቡድን አባሉ አቶ ምስጋናው ሙሉጌታ ናቸው። የሽግግር ፍትሕን “በግጭት አውድ ውስጥ፣ ውስብስብ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሁኔታ ውስጥ ሆነው የሞከሩ ሀገራት አሉ” ያሉት የቡድኑ አባል፤ የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ በምሳሌነት አንስተዋል። የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ በዝግጅት ላይ መሆ “የመንግስትን የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ግዴታዎች አያስቀርም” ሲሉም ሞግተዋል። የሽግግር ፍትሕ፤ ግጭቶችን ለማቆም አስተዋጽኦ እንዳለውም አክለዋል።  

ይህን መሰሉ የባለሙያዎች ማብራሪያ፤ የውይይቱን ተሳታፊዎች መድረኩን ረግጦ ከመውጣት አላገዳቸውም። በትላትናው ስብሰባ መርሃ ግብር መሰረት ተሳታፊዎች የቡድን ውይይት ማድረግ ቢጠበቅባቸውም፤ ከውይይቱ በፊት ለአንድ ሰዓት ገደማ የቆየ ሌላ ውይይት ከባለሙያዎች ቡድን ጋር አድርገዋል። በዚሁ ውይይት ላይ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮቹ “ውይይቱ አያስፈልግም አዳራሹን ለቅቀን እንውጣ” እንዲሁም “እንወያይ” በሚል ለሁለት ተከፍለው ተከራክረዋል።

ፎቶ:- ከEBS ቴሌቪዥን

ውይይቱን የተቃወሙት ወገኖች በዋናነት ያነሷቸው መከራከሪያዎች “የሽግግር ፍትሕ ጊዜው አይደለም” እንዲሁም “የምንሰጠው ግብዓት ጥቅም ላይ አይውልም” የሚሉ ናቸው። ለዚህም በማሳያነት ያነሱት፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ የተደረገውን የግብዓት ማሰባሰቢያ ነው። ከአንድ ዓመት በፊት የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ በመሩት መድረክ፤ ፓርቲዎች በረቂቅ አዋጁ ላይ ቅሬታዎች ቢያነሱም ማስተካከያ ሳይደረግ አዋጁ መጽደቁን አንስተዋል። 

ለአንድ ሰዓት ያህል በባለሙያዎች ቡድን እና በፖለቲካ ፓርቲዎቹ ውይይት ከተደረገ በኋላ፤ የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች መድረኩን በተቃውሞ ረግጠው ወጥተዋል። ስብሰባውን አቋርጠው ከወጡት መካከል እናት፣ መኢአድ፣ አብን እና የአገው ብሔራዊ ሸንጎ ተወካዮች ይገኙበታል። በትላንትናው ስብሰባ ላይ እንዲሳተፉ ከተጠሩ መካከል፤ የ21 የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ቀርተው የቡድን ውይይቱን አካሄደዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)