ባልደራስ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤውን እንዳያደርግ ተከለከለ  

በአማኑኤል ይልቃል

ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ዛሬ እሁድ መጋቢት 3፤ 2015  ሊያካሄድ የነበረውን ጠቅላላ ጉባኤ እንዳያደርግ ተከለከለ። ጠቅላላ ጉባኤው ሊካሄድ የነበረበት ጋምቤላ ሆቴል፤ ስብሰባውን ማስተናገድ እንደማይችል እንደነገራቸው የፓርቲው አመራሮች አስታውቀዋል። 

የተቃዋሚ ፓርቲው አባላት በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ለመገኘት በአዲስ አበባ ራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ በሚገኘው ጋምቤላ ሆቴል የተገኙት ከጠዋቱ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ጀምሮ ነበር። የፌዴራል እና የአዲስ አበባ ፖሊስ አርማ በለጠፉ ተሽከርካሪዎች ላይ የተጫኑ የፖሊስ አባላት፤ በሆቴሉ መግቢያ አካባቢ ቆመው ሁኔታውን ሲከታተሉ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ተመልክቷል።

ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ከ30 ገደማ ላይ አንድ የጋምቤላ ሆቴል አስተዳደር ሰራተኛ፤ ለጠቅላላ ጉባኤው አስተባባሪዎች እና ተሳታፊዎች “የተፈቀደ ስብሰባ” እንደሌለ አስታውቃለች። በሆቴሉ ስብሰባ እንደማይኖር መገለጹን ተከትሎ፤ የባልደራስ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አምሃ ዳኘው እና ሌሎች የፓርቲው ተወካዮች ከሆቴሉ አስተዳደር ጋር ለ20 ደቂቃ ገደማ ውይይት አድርገዋል።

ከውይይቱ በኋላ የባልደራስ አመራሮች በሆቴሉ መግቢያ በር ላይ ሆነው ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል። የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት፤ ባልደራስ ጋምቤላ ሆቴል ጉባኤውን ለማድረግ “ፈቃድ ማግኘቱን” ተናግረዋል። ሆኖም ለጉባኤው የሚያስፈልጉ ዝግጅቶችን ለማስፈጸም የፓርቲ አመራሮች ባደረጓቸው ሂደቶች፤ ተደጋጋሚ ተግዳሮቶች እንዳጋጠማቸው አስረድተዋል።

የባልደራስ ፓርቲ አመራሮች ከትላንት በስቲያ አርብ ለሆቴሉ ክፍያ ለመፈጸም ቢገኙም “ከከንቲባ ጽህፈት ቤት የሰላም እና የጸጥታ ቢሮ የፈቃድ ወረቀት” እንዲያመጡ እንደተነገራቸው አቶ አምሃ ገልጸዋል። ፓርቲው “የፈቃድ ወረቀቱን” ይዞ በሆቴሉ በመገኘት ክፍያ ለመፈጸም ሲሞክርም፤ የሆቴሉ ምክትል ስራ አስኪያጅ እንደሆኑ የገለጹ ግለሰብ “ከእናንተ በፊት ከኦሮሚያ ፖሊስ መጥተው ስብሰባው እዚህ እንዳይካሄድ ብለው አስፈራርተውኛል” የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው አስረድተዋል።

የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አክለውም “እሺ ብለን ወደ ሌላ አማራጭ ሄድን። አሁን ደግሞ ክፍያ ስላልፈጸሙ ነው የሚል ነገር መጣ። ቼኩን ይዘን ክፍያ ለመፈጸም መጣን። አሁንም `አንቀበልም፤ አናስተናግድም` ተብሎ እንደምታዩት `ሆቴሉ አናስተናግድም` ስላለ በዚህ ሁኔታ ስብሰባችንን ለማካሄድ አልቻልንም” ሲሉ የባልደራስ አመራሮች ያጋጠማቸውን ችግር ለጋዜጠኞች አብራርተዋል። የጋምቤላ ሆቴል አስተዳደር “ቼኩን አንቀበልም ማለታቸውን” ለማረጋገጥ፤ ጠቅላላ ጉባኤውን ለመታዘብ በቦታው ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ወኪሎች ከሆቴሉ ስራ አስኪያጆች ጋር መነጋገራቸውንም ገልጸዋል። 

የባልደራስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ እና የስራ አስፈጻሚ አባል ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ፤ የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ትላንት ቅዳሜ መጋቢት 2 ለሰዓታት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው “በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች እንዲዘዋወሩ” መደረጉን ጠቅሰው፤ ይህም በፓርቲው ላይ ጫና ለመፍጠር የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው ብለዋል። “ሀገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ እናውቃለን። ከፍተኛ አፈና በየትኛውም አቅጣጫ እየተካሄደ ነው። ስለዚህ ፓርቲው የመጀመሪያውን ጠቅላላ ጉባኤ አድርጎ ሰርተፊኬቱን እንዳያገኝ የኦሮሚያ ፖሊስ፣ የፍትህ እና የደህንነት ኃይላት ከፍተኛ ጫና አድርገውብን ማካሄድ አልቻልንም” ሲሉ ተደምጠዋል።

የፓርቲው አባላት ወደ ጋምቤላ ሆቴል በሚገቡበት ሰዓት በ“ፒክ አፕ” መኪና ላይ በመሆን ሁኔታውን ሲከታተሉ የነበሩ የፌደራል ፖሊስ አባላት ከቆይታ በኋላ አካባቢውን ለቅቀው ቢሄዱም፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላትን የያዘ ሌላ “ፒክ አፕ” መኪና በተደጋጋሚ በሆቴሉ መግቢያ ላይ በመቆም ከሆቴሉ ጥበቃዎች ጋር እየተነጋገረ ሲሄድ በስፍራው የነበረው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ታዝቧል። የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች የጠቅላላ ጉባኤውን ክልከላ አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መግለጫ በሚሰጡበት ወቅት፤ የፌደራል ፖሊስ አባላት በቅርብ ርቀት ላይ ሁኔታውን ሲከታተሉ ነበር።

ባልደራስ ዛሬ ሊያካሄደው በነበረው ጠቅላላ ጉባኤ፤ የፓርቲውን አመራሮች ለመምረጥ እና “የተለያዩ ውሳኔዎችን” ለማሳለፍ አጀንዳዎችን ይዞ እንደነበር የፓርቲው አመራሮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። የቀድሞ የፓርቲው ፕሬዝዳንት አቶ እስክንድር ነጋ ራሳቸውን ከፖለቲካው አውድ ማግለላቸውን ተከትሎ በምክትል ፕሬዝዳንት ሲመራ የቆየው ባልደራስ፤ በጠቅላላ ጉባኤው አዲስ ፕሬዝዳንት ለመምረጥ እቅድ ይዞ ነበር። የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት፣ ኦዲት እና ቁጥጥር ኮሚቴ እንዲሁም የዲሲፕሊን ኮሚቴ አባላት፤ በዚሁ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ይመረጣሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር። 

ፓርቲው በዛሬው ጉባኤው ለውሳኔ ሊያቀርባቸው ከነበሩ አጀንዳዎች ውስጥ፤ ባልደራስን ሀገር አቀፍ ፓርቲ ማድረግ የሚለው ይገኝበታል። በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በክልላዊ ፓርቲነት የተመዘገበው ፓርቲው፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት ሲንቀሳቀስ የቆየው በአዲስ አበባ ከተማ ነበር። ባልደራስ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የሚደረግ “ጥምረትን” በተመለከተ፤ በዛሬው ጉባኤ ውሳኔ ለማሳለፍም አቅዶ ነበር። የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ ማጽደቅም፤ በፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤው ከተያዙ አጀንዳዎች አንዱ ነው።

የፓርቲው አመራሮች ዛሬ የተሰረዘውን ጠቅላላ ጉባኤ፤ “በሌላ ጊዜ” እንደሚያካሄዱ በቦታው ለተገኙት የባልደራስ አባላት ገልጸዋል። የስራ አስፈጻሚ አባሉ ዶ/ር በቃሉ “ዛሬ ቢያግዱን ነገ ሊያግዱን አይችሉም። ጠቅላላ ጉባኤውን መክረን፣ ዘክረን፣ ቀስ ብለን እናካሄዳለን” ብለዋል። የባልደራስ ምክትል ፕሬዝዳንት በበኩላቸው፤ ፓርቲው ከምርጫ ቦርድ ጋር ንግግር ካደረገ በኋላ ጠቅላላ ጉባኤው የሚካሄድበትን “ተለዋጭ ቀን” ለአባላቱ እንደሚያሳውቅ ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃዎች ታክለዋል]