በጸጥታ ችግሮች ሳቢያ “የገቢ ጉድለት” እንደገጠመው ኢትዮ ቴሌኮም አስታወቀ

በተስፋለም ወልደየስ

ከጸጥታ ጋር በተገናኘ የሚፈጠሩ ችግሮች፤ በኢትዮ ቴሌኮም ገቢ ማመንጨት ላይ ችግሮች እየፈጠሩበት መሆኑን የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ተናገሩ። ኩባንያው በኢንተርኔት መዘጋት ምክንያት ያጣው ገቢ፤ በቅርቡ በዓለም አቀፍ ሪፖርት የተጠቀሰውን ያህል እንዳልሆነም ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል። 

ዋና ስራ አስፈጻሚዋ የኢትዮ ቴሌኮምን የ2016 በጀት ዓመት የመንፈቅ የስራ አፈጻጸም በዛሬው ዕለት ይፋ ባደረጉበት ወቅት፤ ኩባንያው በግማሽ ዓመቱ ካጋጠሙት ተግዳሮቶች መካከል አንዱ “በተለያዩ አካባቢዎች ይሰጥ የነበረው አገልግሎት መቋረጥ” መሆኑን ጠቅሰዋል። መንግስታዊው የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ አገልግሎቱን ለማቋረጥ የተገደደው   በአካባቢዎቹ ባጋጠመው “የጸጥታ ችግር ምክንያት” መሆኑ የገለጹት ፍሬሕይወት፤ በዚህም ሳቢያ ኩባንያው “የገቢ ጉድለት” እንዳጋጠመው አስታውቀዋል። 

“ተዘዋውረን ካልሰራን እና ጥገና ማድረግ ካልተቻለ፤ የተዘረጉ መሰረተ ልማቶችን አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ካላደረግን ጉድለት ያመጣል። ወይም ያቀድነውን ዕቅድ ሙሉ ለሙሉ እንዳናሳካ የራሱ የሆነ ተጽዕኖ አለው” ሲሉ ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ችግሩን ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም በ2016 በጀት ዓመት ገቢውን በ15 ቢሊዮን ብር ገደማ ለማሳደግ ማቀዱን ባለፈው ሐምሌ ወር አስታውቆ ነበር። ኩባንያው አጠቃላይ ገቢውን 90.5 ቢሊዮን ብር ለማድረስ፤ የደንበኞቹን ቁጥርም በስድስት ሚሊዮን ለመጨመር ዕቅድ መያዙን ካስታወቀ ከመንፈቅ በኋላ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በግማሽ ዓመቱ ያስመዘገበው አፈጻጸም “ከፍተኛ እና  አበረታች” መሆኑን ገልጿል። 

በገቢ ረገድ ኩባንያው ከያዘው ዕቅድ 98 በመቶውን በማሳካት፤ በግማሽ ዓመቱ 42.9 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን በዛሬው መግለጫው ይፋ አድርጓል። በዚሁ ጊዜ ውስጥ የደንበኞቹን ቁጥር ወደ 74.6 ሚሊዮን ማሳደግ መቻሉንም ኢትዮ ቴሌኮም ገልጿል። ይህ አፈጻጸም በእቅድ ከተያዘው 98.3 በመቶውን ያሳካ እንደሆነም ኩባንያው አስታውቋል።

ኢትዮ ቴሌኮም የዘንድሮው በጀት ዓመት እቅዱ “ ‘በጣም የተለጠጠ ነው’ የሚለው እውነት ነው” ያሉት ፍሬሕይወት፤ በግማሽ ዓመቱ ካጋጠሙት ተግዳሮቶች በመነሳት ዕቅዱን እንደገና ከመከለስ ይልቅ “የማካካሻ” ስራዎችን ወደ መስራት መግባቱን አስረድተዋል። የጸጥታ ችግር በሌለባቸው አካባቢዎች የሚደረገው የኩባንያው “የማስፋፊያ ስራ” ከማካካሻ ስራዎች አንዱ መሆኑንም አስረድተዋል። 

“ያቀድነውን ዕቅድ መከለስ ያልፈለግነው አንዱ፤ ኩባንያችን በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ፣ ግዙፍ እየሆነ ነው። ስለዚህ የፋይናንስ አቅምን ማሳደግ ማጠናከር በጣም ያስፈልጋል ማለት ነው። ስለዚህ ያቀድነውን ገቢ መጠን ዝቅ ከምናደርግ፤ ያንን ለማሳካት የተለያዩ የገቢ ምንጮችን መፈለግ ይሻላል ብለን ነው እየሰራን ያለነው” ሲሉ የኩባንያው ስራ አስፈጻሚ አብራርተዋል። 

ኢትዮ ቴሌኮም ኢንተርኔት በተዘጋባቸው አካባቢዎች ላሉ ለደንበኞቹ አገልግሎቱን ባለመስጠቱ በዚያ አካባቢ ያገኝ የነበረው ገቢ ቢቀንስበትም፤ በቅርቡ በአንድ ዓለም አቀፍ ሪፖርት የተጠቀሰውን ያህል “ገንዘብ አላጣም” ሲሉ ፍሬሕይወት አስተባብለዋል። ዋና ስራ አስፈጻሚዋ የጠቀሱት ሪፖርት፤ ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2023 በኢንተርኔት ላይ በጣለችው ገደብ ምክንያት፤ 1.59 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የኢኮኖሚ ጥቅም ማጣቷን ይፋ ያደረገ ነበር። 

ሪፖርቱ “ቀጥታ ኢትዮ ቴሌኮምን የሚመለከት አይደለም” ያሉት ፍሬሕይወት፤ ልኬቱን የሰራው አካል የኢንተርኔት መቋረጥ በኢኮኖሚው ላይ የሚኖረውን “ሳይድ ኢፌክት” በማጥናት ያዘጋጀው ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል። ዋና ስራ አስፈጻሚዋ “እነሱ የሚያሰሉባቸው የራሳቸው የሆነ አሰራር ሊኖራቸው ይችላል … ኢትዮ ቴሌኮም ላይ [ግን] የዚያን ያህል የገቢ ተጽዕኖ አልተፈጠረም” ቢሉም፤ ኩባንያቸው በኢንተርኔት መዘጋት ምክንያት ያጣውን ገቢ ትክክለኛ መጠን በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት ሳይገልጹ ቀርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃዎች ታክለውበታል]