በአማራ ክልል፣ ሰሜን ጎጃም ዞን፣ መራዊ ከተማ፤ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች “ለፋኖ ድጋፍ አድርጋችኋል” በሚል ምክንያት፤ ቢያንስ 45 ሲቪል ሰዎችን “ከህግ ውጭ መግደላቸውን” ማረጋገጡን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ። ኮሚሽኑ ለጊዜው ብዛታቸውን ለማረጋገጥ ያልቻላቸው ሰዎችም፤ “የፋኖ አባላት ናቸው” በሚል ተጠርጥረው ከተያዙ በኋላ በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች በተመሳሳይ ሁኔታ መደገላቸውንም ገልጿል።
ኮሚሽኑ ይህን የገለጸው በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው “የትጥቅ ግጭት”፤ በሲቪል ሰዎች ላይ “ከህግ ውጭ የተፈጸሙ ግድያዎች” (extrajudicial killings) በተመለከተ ዛሬ ማክሰኞ የካቲት 5፤ 2016 ባወጣው መግለጫ ነው። ኮሚሽኑ “የትጥቅ ግጭቱ” በሰብአዊ መብቶች እና በማህበራዊ እንቅስቃሴ ላይ እያስከተለ ያለውን ጉዳት እና አሉታዊ ተጽዕኖ፤ የመንግስት አካላትን እና የተለያዩ ወገኖችን በማነጋገር እየተከታተለ እንደሚገኝ በመግለጫው ጠቅሷል።
በዚህም መሰረት በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እና በተለምዶ “ፋኖ” ተብለው በሚጠሩት “የታጠቁ ኃይሎች” መካከል፤ በመራዊ ከተማ ጥር 20፤ 2016 ውጊያ መካሄዱን ተከትሎ በሲቪል ሰዎች ላይ ስለደረሰው ጉዳት ኮሚሽኑ ምርመራ እያከናወነ መሆኑን አመልክቷል። ኢሰመኮ የምርመራ ስራውን በተለያዩ ምክንያቶች ማጠናቀቅ ባይችልም፤ እስካሁን ድረስ ባደረገው ክትትል የደረሰበትን ግኝት በዛሬው መግለጫው ይፋ አድርጓል።
በመራዊ ከተማ፤ በመንግስት የጸጥታ የጸጥታ ኃይሎች እና በ”ፋኖ ታጣቂዎች” መካከል ውጊያ የተካሄደው፤ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እንደነበር ኮሚሽኑ ገልጿል። ኮሚሽኑ ከምስክሮች ባሰባሰበው መረጃ፤ በውጊያው ዕለት ለቀን ስራ በጠዋት ከቤታቸው ወጥተው ድንገት ተኩስ ሲከፈት፤ “በአንድ ቦታ ተጠልለው የነበሩ 18 ሲቪል ሰዎች መገደላቸውን” መረዳቱን ገልጿል። በከተማይቱ ቀበሌ 02 አካባቢ፣ በተለምዶ ሚሊኒየም ተብሎ በሚጠራ ሰፈር፤ ስምንት ሲቪል ሰዎች በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች መገደላቸውንም ኮሚሽኑ አስታውቋል።
የመንግስት የጸጥታ ኃይሎቹ ግድያውን የፈጸሙት፤ የጠፋባቸውን አባላቸውን በሚያፈላልጉበት ወቅት “በፍለጋው አልተባበሩም” ባሏቸው ሰዎች ላይ መሆኑን ኢሰመኮ ምስክሮችን እማኝ አድርጎ በመግለጫው አስፍሯል። በወቅቱ 12 የሶስት እግር ተሽከርካሪዎች (ባጃጆች) በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች መቃጠላቸውንም ኮሚሽኑ አክሏል።
ኢሰመኮ “ከደረሱት በርካታ ጥቆማዎች እና ከልዩ ልዩ መረጃ ምንጮች ከሰበሰባቸው” የተገደሉ የሲቪል ሰዎች ስም ዝርዝር ውስጥ፤ “ማንነታቸውን በመለየት ለማረጋገጥ የቻለው” የአርባ አምስቱን ብቻ መሆኑን በዛሬው መግለጫው አጽንኦት ሰጥቷል። ሆኖም “የጉዳቱ መጠን ከዚህ ሊበልጥ እንደሚችል ምክንያታዊ ግምት ለመውሰድ ተችሏል” ሲል ብሔራዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም በመግለጫው አስገንዝቧል።
“በዚህ ግጭት በሁሉም ወገኖች በተለይም በየአካባቢው ነዋሪዎችና በሲቪል ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለው ስቃይ እጅግ እየጨመረ በመምጣቱ ሁሉም ወገኖች ብቸኛው ዘላቂ መፍትሔ ሰላማዊ ውይይት መሆኑን ተቀብለው በቁርጠኝነት ይተገብሩት ዘንድ አሁንም በድጋሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን
– ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር
በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች በመራዊ ከተማ “ከህግ ውጭ” የተገደሉት የተገደሉት 45 ሲቪል ሰዎች፤ “ለፋኖ ድጋፍ አድርጋችኋል” በሚል ምክንያት መሆኑን ኢሰመኮ ገልጿል። ኮሚሽኑ ለጊዜው ብዛታቸውን ማረጋገጥ ያልቻላቸው ሰዎች፤ “የፋኖ አባላት ናቸው” በሚል ተጠርጥረው ከተያዙ በኋላ “በተመሳሳይ ሁኔታ በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ተገድለዋል” ብሏል።
ኢሰመኮ በመራዊ ከተማ ተፈጽሟል ስላለው የሲቪል ሰዎች ግድያ፤ “የተሟላ ምርመራ የማድረግ አስፈላጊነት” በመግለጫው አስንስቷል። ይህንኑ ያስተጋቡት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “በዚህ ግጭት በሁሉም ወገኖች በተለይም በየአካባቢው ነዋሪዎችና በሲቪል ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለው ስቃይ እጅግ እየጨመረ በመምጣቱ ሁሉም ወገኖች ብቸኛው ዘላቂ መፍትሔ ሰላማዊ ውይይት መሆኑን ተቀብለው በቁርጠኝነት ይተገብሩት ዘንድ፣ እንዲሁም የተሟላ ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥና የተበደሉም እንዲካሱ አሁንም በድጋሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን” ማለታቸው በመግለጫው ተጠቅሷል።
በመራዊ ከተማ ሲቪል ሰዎችን ኢላማ ያደረገ ግድያ መፈጸሙን በተመለከተ የወጡ ሪፖርቶች “እጅጉን እንዳሳሰቡት” ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የገለጸው የአሜሪካ መንግስትም፤ ተመሳሳይ አቋም አንጸባርቆ ነበር። በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኢርቪን ማሲንጋ ባለፈው አርብ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ግድያውን የፈጸሙ አካላት “ለፍርድ እንዲቀርቡ” የሚያስችል “ገለልተኛ ምርመራ” እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
ገለልተኛ የሰብዓዊ መብት ተቆጣጣሪዎች “ያለምንም ገደብ” ወደ ስፍራው በመጓዝ ምርመራ እንዲያካሄዱ ሊፈቀድላቸው እንደሚገባም አምባሳደሩ በአሜሪካ ኤምባሲ ይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጾች በወጣው በዚሁ መልዕክታቸው አሳስበው ነበር። በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚታዩ ችግሮች መፍትሔው ግጭት ሳይሆን ውይይት መሆኑንም ማሲንጋ አስገንዝበዋል።
የመራዊ ከተማ ግድያ ሪፖርት ከመውጣቱ አስቀድሞ፤ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በሌሎችም የኢትዮጵያ አካባቢዎች፤ “የመንግስት እና መንግስታዊ ያልሆኑ ኃይሎች ተሳትፈውባቸውዋል” የተባሉ፤ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን የሚያመለክቱ በርካታ ሪፖርቶች እንደደረሷቸው የአሜሪካ አምባሳደር በዚሁ መልዕክታቸው ጠቅሰው ነበር። ኢሰመኮ በዛሬው መግለጫው፤ ከመራዊ ግድያ በተጨማሪ በአማራ ክልል በጥር ወር ብቻ 21 ሰዎች “ከህግ ውጭ” በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች መገደላቸውን ይፋ አድርጓል።
የመጀመሪያው ግድያ የተፈጸመው በምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ቋሪት ወረዳ፣ ወይ በይኝ ቀበሌ፣ አብሥራ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ጥር 6፤ 2016 እንደሆነ ኮሚሽኑ በመግለጫው ጠቁሟል። በዚሁ አካባቢ “ለወታደራዊ ቅኝት” የተሰማሩ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች፤ “ቤት ለቤት ባደረጉት አሰሳ” ስድስት ሲቪል ሰዎችን ከየቤታቸው አውጥተው “ከህግ ውጭ እንደገደሏቸው” ምስክሮችን ዋቢ አድርጎ ኢሰመኮ ገልጿል።
ጥር 10፤ 2016፤ በምስራቅ ጎጃም ዞን፣ ሸበል በረንታ ወረዳ፣ የዕድ ውኃ ከተማ በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች የተፈጸመው የ15 የሲቪል ሰዎች ግድያ፤ ኢሰመኮ በዛሬው መግለጫ ያካተተው ሌላው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው። በዕለቱ በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተኩስ ልውውጥ ሲካሄድ መቆየቱን የጠቀሰው ኮሚሽኑ፤ ታጣቂዎች ከተማዋን ለቅቀው ከወጡ በኋላ 15 ሰዎች በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች “ከህግ ውጭ” መገደላቸውን አስታውቋል።
እነዚህ ሰዎች የተገደሉት የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች “ቤት ለቤት” ባደረጉት “ፍተሻ” ወቅት እንዲሁም “መንገድ ላይ በመገኘታቸው” ምክንያት እንደሆነ ኢሰመኮ አብራርቷል። ከሟቾቹ ውስጥ ሴቶች እንደሚገኙበትም መግለጫው ጠቁሟል። በዚሁ ጊዜ ሌሎች ሁለት ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱንም ኮሚሽኑ አክሏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]