በአራት ክልሎች ቀሪ እና ድጋሚ ምርጫ በመጪው ሰኔ ወር ሊካሄድ ነው 

በሚራክል ልደቱ

ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ በተካሄደበት ወቅት ምርጫ ሳይደረግ በቀረባቸው ቦታዎች፤ በመጪው ሰኔ ወር መጀመሪያ ምርጫ ሊካሄድ ነው። ምርጫ የሚደረገው፤ በአራት ክልሎች ውስጥ ለሚገኙ ዘጠኝ የፓርላማ መቀመጫዎች እና 26 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ነው።  

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይህንኑ የተመለከተ የጊዜ ሰሌዳ፤ ዛሬ አርብ የካቲት 22፤ 2016 የፖለቲካ ፓርቲ እና የሲቪክ ማህበራት ተወካዮች በተገኙበት ይፋ አድርጓል። በጊዜ ሰሌዳው መሰረት ምርጫው በሚካሄድባቸው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አፋር፣ ሶማሌ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ባሉ የምርጫ ክልሎች፤ መራጮች ድምጽ የሚሰጡት ሰኔ 6፤ 2016 ዓ.ም. ይሆናል።

ቀሪ እና ድጋሚ ምርጫውን ለማካሄድ፤ 1,146 የምርጫ ጣቢያዎች እንደሚቋቋሙ በዛሬው መርሃ ግብር ላይ ተጠቅሷል። ከእነዚህ የምርጫ ጣቢያዎች መካከል ሰላሳ አራቱ ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው ቦታዎች የሚቋቋሙ መሆኑን ምርጫ ቦርድ አስታውቋል። በአሁኑ ወቅት የጸጥታ ችግር በሌለባቸው ቦታዎች ይካሄዳል በተባለው በዚሁ ምርጫ፤ የመራጮች ምዝገባ የሚከናወነው ከሚያዝያ 7 እስከ 21፤ 2016 ባሉት ጊዜያት እንደሚሆንም ቦርዱ ገልጿል።

በጊዜ ሰሌዳው ላይ የዕጩዎች ምዝገባ ከሚያዝያ 7 ጀምሮ ለ10 ቀናት እንደሚካሄድ ሰፍሯል። በሁሉም ቀሪ እና ድጋሚ ምርጫ በሚካሄድባቸው የምርጫ ክልሎች ላይ፤ የዕጩዎች ምዝገባ “በወቅቱ ተጠናቅቆ” እንደነበር በዛሬው የውይይት መርሃ ግብር ላይ ተነስቷል። ነገር ግን  የዕጩዎች ምዝገባ ከተካሄደ ሁለት ዓመት ያለፈው በመሆኑ እና “ዕጩዎች በተለያዩ ምከንያቶች የሚቀየሩ ከሆነ” በሚል ቦርዱ ከፓርቲዎች መረጃ የማሰባሰብ ስራ ሰርቷል ተብሏል። 

በስድሰተኛው ጠቅላላ ምርጫ ወቅት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተለያዩ ምክንያቶች የዕጩ ምዝገባ ማስመዝገብ ያልቻሉ ፓርቲዎች መኖራቸውን ከግምት ማስገባቱን የገለጸው ምርጫ ቦርድ፤ በዚህ ምክንያት በክልሉ በሚገኙ ምርጫ ክልሎች የዕጩዎች ምዝገባ “በአዲስ መልክ እንዲከናወን” ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቋል። 

በቀሩት ከልሎች ለሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ዕጩዎቻቸውን “በተለያየ ምከንያት የሚቀይሩ ከሆነ” ይህንኑ እንዲያሳውቁ ቦርዱ በደብዳቤ መጠየቁን በዛሬው መርሃ ግብር ተነስቷል። በዚህ መሰረት የፖለቲካ ፓርቲዎች “የዕጩዎች ይቀየርልኝ ምክንያቶቻቸውን” አደራጅተው ለቦርዱ ማቅረባቸው ተገልጿል። ብሔራዊው ምርጫ ቦርድ በአራት ክልሎች የሚካሄደውን የቀሪ እና ድጋሚ ምርጫ፤ የተረጋገጠ ውጤት ይፋ ለማድረግ ዕቅድ የያዘው ለሰኔ 16፤ 2016 ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)