ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ኤርትራ በምትገኝበት ቀጠና “ጦርነት ለመቀስቀስ የሚያሴሩ ኃይሎች አሉ” ሲሉ ወነጀሉ 

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ “ጠቅላይ እና ሁሉን ልቆጣጠር ባይ ኃይሎች” ሲሉ የጠሯቸው አካላት፤ ሀገራቸው በምትገኝበት ቀጠና “ሌላ የጦርነት ዑደት ለመቀስቀስ እያሴሩ ነው” ሲሉ ወነጀሉ። ኤርትራ ሊያጋጥማት ለሚችሉ ሁሉም አይነት ጦርነቶች “ዝግጁ” መሆኗንም ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ይህን ያሉት፤ ኤርትራ ነጿነቷን ያወጀችበት 33ኛ ዓመት ክብረ በዓል ትላንት አርብ ግንቦት 16 በአስመራ ስቴዲየም በተከናወነበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ነው። ሶስት ሰዓት ገደማ በፈጀው በዚሁ ክብረ በዓል፤ ባለፉት ዓመታት እንደነበሩት ተመሳሳይ መርሃ ግብሮች ሁሉ ወታደራዊ ሰልፎች፣ የወጣቶች ስፖርታዊ ትርኢቶች እና የሙዚቃ ዝግጅቶች ቀርበዋል። 

ፎቶዎች፦ የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር

አስራ ሶስት ደቂቃ ከፈጀው የኤርትራው ፕሬዝዳንት ንግግር አብዛኛውን ሽፋን ያገኘው፤ ኢሳያስ በከዚህ ቀደም ንግግሮቻቸውም ሆነ ቃለ መጠየቆቻቸው ላይ በስፋት ሲተነትኑ የሚደመጡት የዓለም አቀፍ ፖለቲካ አሰላለፍ እና የልዕለ ኃያላን ውድቀት ጉዳይ ነው። ፕሬዝዳንቱ በትላንቱ ንግግራቸውም ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቂያ በኋላ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት በ“አዲሱ ዓለም አቀፍ ስርዓት” ቅርጽ የያዙትን ርዕዮተ ዓለሞች እና ፖሊሲዎች አንስተዋል። 

ከሩሲያ እስከ ቻይና፣ ከታይዋን እስከ ሆንግ ኮንግ፣ ከአሜሪካ እስከ ፍልስጤም፣ ከኔቶ እስከ አውሮፓ ህብረት፣ ከቀይ ባህር እስከ ኤደን ባህረ ሰላጤ የተዳሰሱበት የፕሬዝዳንት ኢሳያስ ንግግር፤ መቋጫውን ያደረገው የኤርትራ ጎረቤቶችን ጉዳይ በማንሳት ነው። “በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በውስጣዊ ጉዳዮቻችን ላይ የቀረበ ተጽዕኖ እና ጫና የሚያሳድሩ፤ በጎረቤቶቻችን እየታዩ ያሉ ወቅታዊ ሁኔታዎች እና አዝማሚያዎች፤ በእርግጥም በርካታ ናቸው” ብለዋል ኢሳያስ። 

በኤርትራ ባለፉት 33 የነጻነት ዓመታት ለደረሱ “የተወሳሰቡ ችግሮች እና ውድመቶች”፤ ፕሬዝዳንቱ “ጠቅላይ እና ሁሉን ልቆጣጠር ባይ” ሲሉ በንግግራቸው በተደጋጋሚ የጠቀሷቸውን ኃይሎች ተጠያቂ አድርገዋል። እነዚህ ኃይሎች “ክፍፍል እንዲኖር የማነሳሳት”፣ “ቀውሶችን የመፍጠር እና የማባባስ” ከዚያም አልፎ ወረራ እና ጦርነት እንዲቀሰቅስ አጀንዳዎችን የማስረጽ ሚና ሲጫወቱ መቆየታቸውን ኢሳያስ በንግግራቸው አትተዋል። 

እነዚህ ኃይሎች ያቀዷቸው በርካታ ግጭቶች አለመሳካት “ከፍተኛ ተስፋ መቁረጥ” ውስጥ እንደከተታቸው የጠቀሱት የኤርትራው ፕሬዝዳንት፤ በዚህም ምክንያት በአሁኑ ወቅት “ሌላ የጦርነት ዑደት ለመቀስቀስ እያሴሩ ነው” ሲሉ ወንጅለዋል። ፕሬዝዳንቱ የሌላ ዙር ጦርነት ጉዳይን “የአደባባይ ሚስጥር ነው” ሲሉ በንግግራቸው ቢገልጹም ዝርዝሩን ከመግለጽ ተቆጠበዋል። የዚህ ጉዳይ ዝርዝር “በትክክለኛው ጊዜ” የሚገለጽ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በትላንቱ ንግግራቸው ማገባደጃ ላይ ኤርትራ ሊያጋጥማት ለሚችሉ ሁሉም አይነት ጦርነቶች የሀገሪቱ የጸጥታ ኃይሎች ዝግጁነት አሁንም ብቁ መሆኑን አስታውቀዋል። የኤርትራ ህዝብም በዚህ ጉዳይ ሊጨነቅ እንደማይገባውም ማስተማመኛ ሰጥተዋል። ፕሬዝዳንቱ በስተመጨረሻም ኤርትራ ነጻነቷን እና ሉዓላዊነቷን ከመጠበቅ ባሻገር፤ ከቅርብ ጎረቤቶቿ ጋር ያላትን “ወዳጅነት፣ ትብብር እና ተመጋጋቢነት” ለማጠናከር የሚያስችሉ ስራዎችን አሁንም በብርቱ ማከናወኗን እንደምትቀጥል ጨምረው ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

[የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደሩ” ሰለሞን በርሀ ለዚህ ዘገባ አስተዋጽኦ አድርጓል]