የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ባካሄደው የመልካም አስተዳደር ምዘና፤ የማዕድን ሚኒስቴር “ዝቅተኛ አፈጻጸም” ማስመዝገቡ ተገለጸ

በናሆም አየለ

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በፌደራል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ያለውን “መልካም አስተዳደር አፈጻጸም” በተመለከተ ላለፉት 10 ወራት ባደረገው ምዝና፤ የማዕድን ሚኒስቴር “ዝቅተኛ አፈጻጸም” ማስመዝገቡን አስታወቀ። የማዕድን ሚኒስቴር አፈጻጸሙ ዝቅ ያለው፤ የተቋቋመበት አዋጅ “የተሟላ ስልጣን እና ኃላፊነት ለሚኒስቴሩ የማይሰጥ በመሆኑ” ምክንያት እንደሆነ ተነግሯል። 

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፤ የመንግስት አስፈጻሚ አካላት በአዋጅ የተሰጣቸንው ተግባራት “ጥራት፣ ቅልጥፍ እና ግልጽነት ባለው መንገድ” እየሰሩ መሆናቸውን የመከታተል እና የመቆጣጠር ስልጣን አለው። በዚህም መሰረት ተቋሙ የማዕድን ሚኒስቴርን ጨምሮ በ15 የፌደራል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ላይ ከየካቲት 3፤ 2015 ጀምሮ ለ10 ወራት የቆየ “የመልካም አስተዳደር አፈጻጸም” ምዝና ሲያከናውን መቆየቱን ገልጿል። 

ተቋሙ ምዝነናውን ለማከናወን የተጠቀማቸው፤ “ተጠያቂነት፣ ግልጽነት፣ ፍትሃዊነት፣ ለህግ ተገዢነት እና ውጤታማነት” የሚሉትን የመልካም አስተዳደር መለኪያዎች መሆናቸውን በመስሪያ ቤቱ የመልካም አስተዳደር አፈጻጸም ቁጥጥር እና የመንግስት ፕሮጀክቶች ግምገማ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ አዳነ በላይ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በእነዚህ መለኪያዎች የተሻሻለ አፈጻጸም በማምጣት ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ የያዙት የገንዘብ፣ የትምህርት እና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች መሆናቸውን አስረድተዋል።

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶቹ የመልካም አስተዳደር አፈጻጸም ምዘና፤ “የተሻለ”፣ “መካከለኛ” እና “መሻሻል የሚገባው” በሚል ተከፋፍሎ የተከናወነ መሆኑ ትላንት ሐሙስ ግንቦት 29፣ 2016 በአዲስ አበባው ካፒታል ሆቴል በተካሄደ የዕውቅና መድረክ ላይ ተገልጿል። “የተሻለ የመልካም አስተዳደር አፈጻጸም አስመዝግበዋል” በሚል በትላንቱ መርሃ ግብር ዕውቅና የተሰጣቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ስድስት ናቸው። የመጀመሪያዎቹን ሶስት ደረጃዎች የያዙትን በመከተል በዚህ ምድብ የተካተቱት የግብርና፣ የጤና እና የፍትህ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ናቸው።  

“መካከለኛ አፈጻጸም” ማስመዝገባቸው ከተነገረላቸው ስምንት የፌደራል ተቋማት ውስጥ፤ የገቢዎች፣ ንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር፣ የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ እንዲሁም የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ይገኙበታል። የቱሪዝም፣ የሴቶች እና ማሕበራዊ፣ የስራ እና ክህሎት፣ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችም በዚሁ ምድብ ውስጥ ተካትተዋል። 

“መሻሻል የሚገባው” በሚለው ምድብ በብቸኝነት የተቀመጠው የማዕድን ሚኒስቴር መሆኑም በትላንትናው የዕውቅና መድረክ ይፋ ተደርጓል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አፈጻጸሙ ዝቅ ያለው፤ የተቋቋመበት አዋጅ “የተሟላ ስልጣን እና ኃላፊነት ስላልሰጠው” መሆኑን በኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ ዶ/ር እንዳለ ኃይሌ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

“አሁን ማዕድንን በሚመለከት የተሻለ አቅም ያላቸው ክልሎች ናቸው። በክልሉ ያለውን ሀብት የበለጠ የሚቆጣጠሩት እነርሱ ናቸው። ለምሳሌ ጋምቤላ ላይ ወርቅ ካለ፤ በክልሉ ያለውን ሃብት የሚቆጣጠሩት እዚያው ያሉ አካላት እንጂ ማዕድን ሚኒስቴር አይደለም። እንደውም ‘አየር ላይ የተንጠለጠለ ነው፤ የተንሳፈፈ ተቋም ነው’ የሚል ነገር ነው ያለው” ሲሉ ዋና ዕንባ ጠባቂው አብራርተዋል። 

“ማዕድኑ ያለበት ቦታ ላይ የማዕድን ሚኒስቴር ስልጣንና ተግባሩ ምንድን ነው? ምንድን ነው ማድረግ የሚችለው የሚለው ላይ ግልፅ የተደረገ ስልጣን [በአዋጅ] አልተሰጠውም” ሲሉም ዶ/ር እንዳለ አክለዋል።  በ2014 ዓ.ም የተሻሻለው የፌደራል አስፈጻሚ አካላትን ስልጣን እና ተግባር መወሰኛ አዋጅ፤ የማዕድን ሚኒስቴር “የማዕድንና ነዳጅ ስራዎች በሚከናወንበት አካባቢ፤ የአካባቢ ማህበረሰብን ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል” ሲል ይደነግጋል። 

ለዚህ የሚረዳ “የሕግ ማዕቀፍ የማመንጨት” እና “በሚመለከተው አካል ሲጸድቁም በአግባቡ መፈጸማቸውን የማረጋገጥ” ስልጣን አዋጁ የሰጠው ለማዕድን ሚኒስቴር ነው። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፤ የማዕድንና ነዳጅ ስራዎች በሚከናወንበት አካባቢ “የአካባቢ ጥበቃ መስፈርቶችን የመከታተል” ኃላፊነትም በአዋጁ ተጥሎበታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)