በቤት ኪራይ ውድነት የተቸገሩ የመቐለ ዩኒቨርሲቲ መምህራን፤ በተማሪዎች ዶርም “በጊዜያዊነት” እየኖሩ ነው

በሙሉጌታ በላይ

በትግራይ ክልል በሚገኘው መቐለ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩ የተወሰኑ መምህራን “ቤት ተከራይቶ መኖር እንደከበዳቸው” ለተቋሙ ማመልከታቸውን ተከትሎ፤ በተማሪዎች ማደሪያ ዶርም “በጊዜያዊነት” እንዲቆዩ ተፈቅዶላቸው እየኖሩ መሆኑን ገለጹ። የዩኒቨርስቲው መምህራን በክልሉ በነበረው ጦርነት ሳቢያ የ17 ወር ደመወዝ ያልተከፈላቸው መሆኑ፤ በአስር ሺህዎች የሚቆጠር ውዝፍ የቤት ኪራይ እንዲከማችባችው አድርጓል።  

በ1992 ዓ.ም በወጣ ደንብ የተቋቋመው መቐለ ዩኒቨርሲቲ፤ በአሁኑ ወቅት ከስምንት ሺህ በላይ ሰራተኞች ያሉት ሲሆን ከእነርሱ ውስጥ ሁለት ሺህ ገደማ የሚሆኑት መምህራን መሆናቸውን ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በዩኒቨርሲቲው ስር ባሉት ሰባት ካምፓሶች ከሚያስተምሩት ከእነዚህ መምህራን ውስጥ አብዛኞቹ በግል ቤት ተከራይተው የሚኖሩ ናቸው። 

የዩኒቨርሲቲው መምህራን “የቤት ኪራይ መክፈል አቅቶናል” የሚሉ ማመልከቻዎችን ለተቋሙ ማስገባት የጀመሩት ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ ቢሆንም፤ ካለፈው ሶስት ወር ወዲህ ግን በርካታ መምህራን ተመሳሳይ ጥያቄዎች ለተቋሙ ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንት ቢሮ ማቅረባቸው ተነግሯል። መምህራኑ ለዩኒቨርሲቲው ጥያቄ እንዲያቀርቡ የተገደዱት፤ በጦርነት ወቅት ሳይከፍሉ የቀሩትን “ውዝፍ የቤት ኪራይ” አሁን እንዲያመጡ እየተጠየቁ በመሆኑ እና በክልሉ ባለው የኑሮ ውድነት ምክንያት መሆኑን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው መምህራን ያስረዳሉ። 

በመቐለ ዩኒቨርሲቲ 10 ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ያስተማሩ አንድ መምህር፤ በተማሪዎች ማደሪያ ክፍል እንዲሰጣቸው ያመለከቱት ከሁለት ወር በፊት መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። እርሳቸውን ጨምሮ ሌሎች መምህራን ጥያቄውን ያቀረቡት፤ “የ17 ወራት ውዝፍ ደመወዝ ስላልተሰጣቸው” እና ያልተያዙ የተማሪ መኖሪያ ክፍሎች መኖራቸውን ታሳቢ በማድረግ መሆኑን መምህሩ ገልጸዋል። 

“የአስራ ሁለተኛ ክፍል ውጤት የፈጠረው ጫና ስላለ፤ ሶስት ፐርሰንት፣ሁለት ፐርሰንት ነው እያለፉ ያሉት። [በዚህ ምክንያት] ግቢ ውስጥ የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር ቀንሷል። ክፍት የሆኑ የተማሪዎች ማደሪያ ክፍሎች ስላሉ ‘ደመወዛችንን ባይሰጡን እንኳን ለምን ይህን ዕድል አንጠቀምም’ በሚል ነው ጥያቄውን ያቀረብነው” ሲሉ የኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ መምህሩ አብራርተዋል። 

በ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን ከወሰዱ 845 ሺህ ገደማ ተማሪዎች መካከል፤ ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ የማለፊያ ነጥብ ያመጡት ተፈታኞች ብዛት 3.2 በመቶዎቹ ብቻ መሆናቸውን ትምህርት ሚኒስቴር ባለፈው መስከረም ወር ላይ አስታውቆ ነበር። መቐለ ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮ ዓመት በቅድመ ምረቃ፣ በድህረ ምረቃ፣ በማታ እና በርቀት የሚያስተምራቸው ተማሪዎች ብዛት 11 ሺህ የሚጠጋ ነው።

“አዲሃቂ” ወይም “ቢዝነስ” በሚባለው ካምፓስ የሚያስተምሩ አንድ መምህር፤ ተማሪዎች ባልገቡባቸው የመኖሪያ ክፍሎች ለመኖር አመልክተው ጥያቄያቸው ተቀባይነት ያገኙ መምህራን 55 ገደማ እንደሆኑ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። መቐለ ዩኒቨርሲቲ ከአዲሃቂ ካምፓስ በተጨማሪ አሪድ (ዋናው ግቢ)፣ አይደር፣ ቃላሚኖ፣ መለስ፣ ዓይናለም (ኤም. አይ.ፒ) እና ባሎኒ ተብለው የሚታወቁ ካምፓሶች አሉት። 

በዩኒቨርሲቲው “ግራጅዌት አሲስታንት” እንደሆኑ የተናገሩት መምህር፤ ማመልከቻቸው ተቀባይነት አግኝቶ በሚያስተምሩበት አዲ ሃቂ ካምፓስ “ዶርም” እንደተሰጣቸው አመልክተዋል። ለመምህራን የተማሪዎች ማደሪያ ዶርም እንደተሰጠ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያረጋገጡት የመቐለ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር አብዱልቃድር ከድር፤ ይህ የተደረገው “ቤት ለተወደደባቸው፣ ተከራይተው መኖር ላልቻሉ፣ የፋይናንስ ችግር” ላለባቸው መምህራን መሆኑን አስረድተዋል። 

በአዲሃቂ ካምፓስ የሚያስተምሩት መምህር ለዩኒቨርሲቲው ያስገቡት ማመልከቻ፤ የሚከፈላቸው ደመወዝ “ቤት ተከራይቶ ህይወት ለመምራት የማያስችላቸው” መሆኑን የሚያስረዳ ነበር። “በአሁኑ ሰዓት ያለው የዩኒቨርሲቲ አስተማሪ ክፍያ ‘ሰርቫይቭ’ እንድታደርግ የሚያስችል አይደለም። ለምሳሌ እኔ ስምንት ሺህ ብር ደመወዝ ነው የሚከፈለኝ። በዚህ ብር መቐለ ከተማ ውስጥ [ቤት] ኪራይ ከፍለህ፤ በእያንዳንዷ ቀን ዳቦ ገዝተህ ‘ሰርቫይቭ’ ማድረግ እንኳን አትችልም። ሶስት በሁለት ወይም ሶስት በሶስት የሆነች ትንሽዬ ክላስ እስከ ሶስት ሺህ ብር ይከራያል” ይላሉ መምህሩ። 

ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በኋላ በመቐለ ከተማ “ከፍተኛ የሆነ የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪ” እንዳለ የከተማይቱ ነዋሪዎችም ይስማማሉ። አቶ መለስ ኪዳነ የተባሉ በቤት ድለላ የተሰማሩ ነዋሪ ከጦርነቱ በፊት “ከ300 ብር ጀምሮ” ቤት ያከራዩ እንደነበር ያስታውሳሉ። “በዚያን ወቅት በ1,000 ብር የሚከራይ ሰው፤ መኝታ እና ሳሎን ሁሉ ነበረው” ሲሉም በአድናቆት ያወሳሉ።   

የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተፈረመበት ከጥቅምት 2015 ወዲህ ባለው ጊዜ ግን፤ በመቐለ የቤት ኪራይ “በእጥፍ እንደጨመረ”  አቶ መለስ ይገልጻሉ። በአሁኑ ወቅት “ጥሩ የሚባል” ባለ አንድ ክፍል ቤት፤ ከ3,500 እስከ 4,000 ብር እንደሚከራይ የሚያስረዱት የቤት ደላላው፤ ከዚህ ዋጋ በታች ከ2,000 እስከ 2,500 ብር የሚከራዩት “ደቃቃ ቤቶች” መሆናቸውን ይናገራሉ። በከተማይቱ ሁለት መኝታ ቤት ያለው ኮንዶሚኒየም ከ4,000 እስከ 5,000 ብር ባለ የኪራይ ዋጋ እንደሚገኝም ያክላሉ።

በመቐለ ዩኒቨርሲቲ “በሲቪል ኢንጂነሪንግ” ትምህርት ክፍል የሚያስተምሩ መምህር፤ በትግራይ ክልል ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት ለተከራዩት አንድ ክፍል ቤት ይከፍሉ የነበረው 1,800 ብር እንደነበር ይጠቅሳሉ። የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት እንደተፈረመ የተከራዩት ቤት ዋጋ በሁለት እጥፍ ጨምሮ 3,500 ብር መግባቱን ይናገራሉ። 

እኚህ መምህር ከጭማሪው ሌላ በጦርነቱ ወቅት ለዩኒቨርሲቲው መምህራን የሚከፈለው ደመወዝ ቆሞ ስለነበር፤ “ያልከፈሉት ከ30 ሺህ ብር በላይ ውዝፍ የቤት ኪራይ” አለባቸው። አከራያቸው “ሁሌ የሚጠይቋቸውን ዕዳ” ለመክፈል”፤ በዩኒቨርሲቲው “የተማሪዎች ዶርም እንዲሰጣቸው” ካመለከቱ አንድ ወር ገደማ ሆኗቸዋል።

እንደ እርሳቸው ጥያቄ ካቀረቡ መምህራን ውስጥ የተወሰኑት፤ ቀድሞውኑም ለመምህራን ታስቦ የተሰራ፤ መኝታ ቤት እና ማብሰያ ክፍል ያለው መኖሪያ እንደተሰጣቸው አስተውለዋል። ሌሎች መምህራን ደግሞ “የተማሪዎች ዶርም” የነበሩ ክፍሎች ውስጥ መኖር እንደጀመሩም ተመልክተዋል። እነዚህ መምህራን ከሚኖሩበት አቅራቢያ መጸዳጃ ቤት ባለመኖሩ፤ በእኩለ ለሊትም ቢሆን የተወሰነ ርቀት በጭለማ  ለመጓዝ ይገደዳሉ።

“ወደህ አይደለም፤ ‘ሰርቫይቭ ለማድረግ’ አማራጭ ስለሌለ ምን ይደረጋል?” ይላሉ ማመልከቻቸው ተቀባይነት እንዲያገኝ እየጠበቁ ያሉት መምህር። በአዲ ሃቂ ካምፓስ የተማሪዎች ዶርም የተሰጣቸው መምህር፤ “አሁን ለቤት ኪራይ የምናወጣው ባይኖርም፤ የተሻለ እየኖርን አይደለም” ሲሉ ሃሳቡን ይጋራሉ። 

ለዚህ በማሳያነትም፤ ለተማሪዎች በመኪና የሚመጣ ውሃ ወረፋ እየጠበቁ እንደሚቀዱ፤ በዶርም ውስጥ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል “ምድጃ ለመለኮስ ፓዎር ስለሌለው” ምግብ “እንደተማሪዎች ከውጭ ገዘተው” እንደሚመገቡ ይጠቅሳሉ። በዚህ የተማሪዎች ዶርም ውስጥ “ትዳር ያላቸው” እና “ሶስት ልጅ ይዘው የሚኖሩ” መምህራን እንዳሉ እና የኑሮ ሁኔታው “አስቸጋሪ” የሚባል መሆኑን ያስረዳሉ። 

የኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍሉ መምህሩ በበኩላቸው አዲ ሃቂ ካምፓስ በተጨማሪ አሪድ እና በአይደር ካምፓሶች “ቤተሰቦቻቸውን ይዘው በተማሪዎች ማደሪያ ውስጥ” እየኖሩ ያሉ መምህራን እንዳሉ ጠቁመዋል። “ምን አማራጭ አለህ? ባለትዳርም፣ ወንደላጤም ብትሆን፤ የሚሰጥህን ዶርም እንደምንም ብለህ አብቃቅትህ መኖር ነው” ሲሉ መምህራኑ የተሻለ አማራጭ እንደሌላቸው ይሟገታሉ።

የመቐለ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ከእነ ችግሩም ቢሆን ለገጠማቸው የደመወዝ እና የኑሮ ውድነት ተግዳሮት፤ እንደ መፍትሔ እየተጠቀሙበት ያለው የተማሪዎች ዶርምን የማግኘት ሂደት “እንዲቆም መደረጉ” ተገልጿል። በዩኒቨርሲቲው በኃላፊነት ላይ ያሉ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ ምንጭ፤ ለመምህራኑ የሚሰጠው ጊዜያዊ መኖሪያ ቤት “መቆሙን” የሚገልጽ ደብዳቤ መመልከታቸውን “ለኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ይህ ውሳኔ የተላለፈው በበጀት እጥረት እና በተለያዩ ምክንያቶች የተማሪዎች መኖሪያዎችን “መጠገን ስለማይቻል” እንደሆነ በደብዳቤው ላይ መገለጹን ምንጩ አክለዋል። በጦርነት ውስጥ በቆየው ትግራይ ክልል የሚገኘው መቐለ ዩኒቨርሲቲ፤ ለ2017  ከፌደራል መንግስት የተመደበለት መደበኛ በጀት 1.1 ቢሊዮን ብር ነው። ለዩኒቨርሲቲው ለካፒታል ወጪዎች ከመንግስት ግምጃ ቤት ከተመደበለት 1.7 ቢሊዮን ብር ውስጥ 30 ሚሊዮን ብር ያህሉ የተያዘው ለአስተማሪዎች መኖሪያ ህንጻ ግንባታ ነው። 

የዩኒቨርሲቲው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጭ፤ ለመምህራን ሳይከፈል የቀረው የ17 ወር ደመወዝ ዘንድሮ “ይከፈላል ተብሎ እየተጠበቀ” መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል። ውዝፍ ክፍያው ከተፈጸመ በኋላ ወደ ተማሪዎች መኖሪያ እንዲገቡ የተደረጉት መምህራን፤ ዶርሞቹን ሊለቁ እንደሚችሉ አመልክተዋል።

“የተማሪዎች ዶርም የተሰጠው ጊዜያዊ ነው። የተወሰነ እስከሚያገግሙ ድረስ ነው” የሚሉት የመቐለ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር አብዱልቃድር፤ የተማሪዎች መኖሪያን የመስጠት አካሄድ በአሁኑ ወቅት መቆሙን አረጋግጠዋል። የተወሰነ የተዘጋጀ ነበር። እሱን ሰጠን። በመደበኛነት የመምህራን መኖሪያ አይደለም፤ የተማሪዎች ነው። ቀድሞም ስላልተዘጋጀ የቆመ ነገር አለ። የተዘጋጀ ዶርም ከሌለ ምንም ማድረግ አንችልም” ሲሉ ከውሳኔው ጀርባ ያለውን ምክንያት አብራርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)