ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት 3.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር አገኘች

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ስራ አስፈጻሚ ቦርድ ለኢትዮጵያ 3.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር አጸደቀ። የተራዘመ የብድር አቅርቦት (ECF) በተባለው ፕሮግራም ከጸደቀው ብድር ውስጥ፤ አንድ ቢሊዮን ዶላር በአፋጣኝ ለኢትዮጵያ የሚለቀቅ እንደሆነ ተቋሙ አስታውቋል።  

መቀመጫውን በዋሽንግተን ያደረገው ድርጅት የስራ አስፈጻሚ ቦርድ ብድሩን ያጸደቀው፤ የኢትዮጵያ መንግስት በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርዓት ዛሬ ሰኞ ተግባራዊ ማድረጉን ተከትሎ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ተግባራዊ ባደረገው እርምጃ ብር ከዶላር አኳያ ያለው የምንዛሬ ተመን በ30 በመቶ ተዳክሟል። የአንድ ዶላር ምንዛሬ ከ58 ብር ከ50 ሳንቲም ወደ 76 ብር ከ73 ሳንቲም ከፍ ሲል፤ በገበያው የምግብ ዘይትን በመሳሰሉ ሸቀጦች የመሸጫ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ተከስቷል። 

በአራት ዓመታት የሚለቀቀው የIMF ብድር፤ የኢትዮጵያ መንግስትን “ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለመደገፍ፣ ማክሮ ኢኮኖሚያዊ መዛባቶችን ለማስወገድ፣ የውጭ ዕዳ ዘላቂነትን ለማረጋገጥ እና ለከፍተኛ፣ አካታች እና በግሉ ዘርፍ የሚመራ ዕድገት መሰረት ለመጣል” የታቀደ እንደሆነ ተቋሙ አስታውቋል። 

ተቋሙ ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 22፤ 2016 ያጸደቀው ብድር፤ ሌሎች የኢትዮጵያ የልማት አጋሮች እና አበዳሪዎች ተጨማሪ የፋይናንስ እገዛ እንዲሰጡ ያበረታታል ተብሎ እንደሚጠበቅ በመግለጫው ጠቁሟል።“የሽግግር ወቅት ወጪዎችን እና የውጭ ምንዛሬ ማሻሻያ የሚያስከትላቸውን ጫናዎች ለመቀነስ”፤ የኢትዮጵያ መንግስት “10.7 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ትልቅ የገንዘብ ድጋፍ ከውጭ አጋሮች” ማግኘቱን የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ ተናግረዋል። 

አቶ ማሞ  የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ስርዓት ማሻሻያን አስመልክቶ ዛሬ ሰኞ ማለዳ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “ይኸ የገንዘብ ድጋፍ ከዓለም የገንዘብ ድርጅት፣ ከዓለም ባንክ እና ከአበዳሪዎች የሚገኘውን ይህን ሪፎርም የሚመለከተውን ይጨምራል” ሲሉ ተደምጠዋል። የብሔራዊ ባንኩ ገዥ “በማዕከላዊ ባንክ ተቀማጭ ሒሳብ (Central Bank Deposit) እና የሀገራት የገንዘብ ልውውጥ (Currency Swap) መልክ ተጨማሪ 2.8 ቢሊዮን ዶላር ከወዳጅ ሀገሮች” ማግኘቱንም ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)