በአዲስ አበባ ከተማ የ50 አመት እድሜ ያላቸው ዘመናዊ ጎጆ ቤቶች በኮሪደር ልማት ምክንያት ሊፈርሱ ነው    

በናሆም አየለ

በአዲስ አበባ፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ፣ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት የሚገኙ የሃምሳ ዓመት እድሜ ያላቸው 31 ጎጆ ቤቶች በከተማይቱ አስተዳደር ትዕዛዝ ሊፈርሱ ነው። ንብረትነታቸው የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን የሆኑት ጎጆ ቤቶቹ የሚፈርሱት፤ ቦታው “ለኮሪደር ልማት” ስለሚፈለግ እንደሆነ ተገልጿል።

ጎጆ ቤቶቹ የተሰሩት፤ የኢትዮጵያ ሴቶች በጎ አድራጎት ማህበር በመስከረም 1966 ዓ.ም. ባስመረቀው ባለ ዘጠኝ ወለል ህንጻ አካል በመሆን ነበር። ህንጻው የተገነባው “ለሀገር እና ለወገናቸው በጎ ስራ ሰርተው ያለፉ ኢትዮጵያውያት እንዲታሰቡበት፣ መጪዎችም ይገነዙበት ዘንድ፣ ስራቸውም ለትውልድ ተላልፎ ዘላቂነት እንዲኖረው በማሰብ” እንደሆነ በህንጻው መግቢያ ላይ የተለጠፈው መረጃ ያሳያል። 

በስተኋላ ላይ ለኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን የተላለፈው ይህ ህንጻ “በዲዛይን ልህቀቱ፣ በቦታ አጠቃቀሙ፣ ባህላዊ እሳቤን በዘመናዊ አሰራር ያወሃደ” በመሆኑ ተጠቃሽ እንደሆነ የኪነ ህንጻ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ባለሙያዎቹ ህንጻውን እና የእርሱ አካል የሆኑትን ጎጆ ቤቶች፤ “የአዲስ አበባ ምልክት ከሆኑ” ግንባታዎች መካከል ይመድቧቸዋል። 

ጎጆ ቤቶቹ በውስጣቸው የመጻህፍት መደብር፣ የሙዚቃ መሳሪያ እና አልበም መሸጫ፣ በምሽት የጃዝ ሙዚቃ የሚቀርብበት ስፍራ፣ የስራ ላይ ደህንነት መጠበቂያ ቁሳቁሶች የሚሸጡበት ሱቅ፣ የጉዞ ወኪል ቢሮ፣ እስከ እኩለ ለሊት አገልግሎት የሚሰጡ ካፌ እና ሬስቶራንት ያሉባቸው ናቸው። እነዚህን ጎጆ ቤቶች ተከራይተው ለረጅም አመታት ለህዝብ አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ የንግድ ድርጅቶች፤ ከትላንት በስቲያ ጀምሮ ስፍራውን “በአስቸኳይ” ለቅቀው እንዲወጡ እንደተነገራቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

ይኸው ትዕዛዝ፤ የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ማክሰኞ ሐምሌ 23፤ 2016 ለተከራዮች ባሰራጨው ደብዳቤ ላይ በጉልህ ሰፍሯል። ፌዴሬሽኑ ተከራዮቹን “በአስቸኳይ ለቅቀው እንዲወጡ” ያዘዘው፤ ከአንድ ቀን በፊት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 ዋና ስራ አስፈጻሚ ጽህፈት ቤት የደረሰውን ደብዳቤ መሰረት በማድረግ ነው።

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው የጽህፈት ቤቱ ደብዳቤ፤ ከእስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን እስከ ቤተ መንግስት ያለው መንገድ ቀጣይ የኮሪደር ልማት አካል መሆኑን ይጠቅሳል። በዚህም መሰረት የኮሪደር ልማት ስራው ሲሰራ “ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ እንዲሳካ”፤ “መነሳት ያለበትን በማንሳት፣ መፍረስ ያለበትን በማፍረስ እንዲሁም በማስዋብ እና አረንዴ በማልበስ” አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ይጠይቃል። 

የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን የወረዳ ጽህፈት ቤቱን ደብዳቤ በመጥቀስ ለተከራዩቹ ባሰራጨው ደብዳቤ ላይ፤ በራሱ ህንጻ ዙሪያ ያሉ ጎጆ ቤቶች “ለኮሪደር ልማት ተነሺ መሆናቸውን” ገልጿል። ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ተከራዮቹ “አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ” ፌዴሬሽኑ በደብዳቤው አሳስቧል። 

ደብዳቤው የደረሳቸው የንግድ ድርጅት ባለቤቶች ከትላንት በስቲያ ጀምሮ እቃዎቻቸውን ማውጣት መጀመራቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በስፍራው ላይ ከአርባ አመት በላይ መስራታቸውን የሚናገሩ አንድ ተከራይ፤ ማክሰኞ ጠዋት በፌደሬሽኑ በኩል ደብዳቤ ከደረሳቸው በኋላ ከሰዓት ወደ ስምንት ሰዓት ገደማ ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ ቦታውን ለመለካት ሶስት ሰዎች መምጣታቸውን ተናግረዋል።

የክፍለ ከተማው ሰዎች ቦታውን “በአስቸኳይ ለቅቀው እንዲወጡ” እንደነገሯቸው የሚገልጹት ተከራዩ፤ ይህ ካልሆነ ግን ንብረታቸው እንደሚወረስ እንዳስጠነቀቋቸው በሀዘኔታ አስረድተዋል። ግለሰቡ ረጅም አመት ህጋዊ ሆነው ግብር እየገበሩ ከሰሩበት ቤት በአንድ ቀን ልቀቁ በመባላቸው ማዘናቸውንም ገልጸዋል። ትላንት ረቡዕ ሐምሌ 24፣ 2016 በስፍራው የተገኘው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ፤ ድርጅቶቹ እቃዎቻቸውን ሲያጓጉዙ ተመልክቷል። 

“ተከራዮች ለምን በፍጥነት እንዲወጡ እንደተደረገ” ጥያቄ ያቀረብንላቸው የህንጻው አስተዳደር ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ መንበረ አሽኔ፤  “እኛም እኮ የተነገረን ሰኞ ነው የምናወቀው ነገር አልነበረም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። የኮሪደር ልማቱ የተጀመረ ሰሞን፤ የእነርሱ ህንጻ ያለበት ስፍራ ከዋናው አስፓልት ሰባት ሜትር ወደ ውስጥ ገባ እንደሚደረግ ሲወራ እንደነበር የሚያስታውሱት ወ/ሮ መንበረ፤ ቆይቶ ግን “እዚህ አካባቢ ምንም ዓይነት ፈረሳ የለም” ተብሎ እንደነበር ገልጸዋል። 

“ተከራዮቹ ለቅቀው እንዲወጡ ሲባል ‘ቀነ ገደብ አይሰጥም ወይ?’ ብለን ከክፍለ ከተማ የመጡትን ሰዎች ስንጠይቅ፤ ‘ከተሞክሮ ውሰዱ’ የሚል ምላሽ ነው ያገኘነው። ‘ተሞክሮ ምንድነው?’ ብለን ስንጠይቅ ደግሞ ‘ጠዋት ነግረው፤ ማታ ሊመጡ ይችላሉ’ የሚል መልስ ሰጡን። ስለዚህ ተከራዮቻችንን በፍጥነት እቃዎቻቸን እንዲያወጡ ነግረናቸዋል” ሲሉ ስራ አስኪያጇ ከውሳኔያቸው ጀርባ ያለውን ምክንያት አብራርተዋል።

ጎጆ ቤቶቹ ግማሽ ምዕተ አመት የተጠጋ እድሜ ቢኖራቸውም “ዛሬም ውበታቸው አለመጥፋቱን” የሚናገሩት ወ/ሮ መንበረ፤ ለምን ማፍረስ እንደተፈለገ እንዳልገባቸው ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን በህንጻው ስር ያሉ ጎጆ ቤቶች እንደሚፈርስበት ከመነገሩ አስቀድሞ፤ በአራዳ ክፍለ ከተማ የሚገኝ እና በ3,330 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ የሙያ ማዕከል እንደፈረሰበት ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ምንጭ ለ “አትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

ፌዴሬሽኑ ወደፊት ግንባታ ሊያከናውንበት ዝግጅት አድርጎ የነበረበት እና በፒያሳ ደጎል አደባባይ አካባቢ የሚገኝ ሌላ መሬትም እንደተወሰደበትም ምንጩ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን በተለያዩ ቦታዎች በሚገነባቸው የገበያ ማዕከሎች እና መስቀል አደባባይ አካባቢ ካለው ህንጻ የሚያገኘውን ገቢ፤ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ሴቶች ድጋፍ እንደሚያውለው አክለዋል። የገበያ ማዕከሎቹ ለሴቶች የስራ ዕድል በመፍጠር ረገድም የማይናቅ ሚና እንዳላቸውም አስረድተዋል።  

በመስቀል አደባባይ አካባቢ ከሚገኙት ጎጆዎች አንዱ ተከራይተው ሲሰሩ የቆዩ ግለሰብ፤ “ከ100 በላይ ሰራተኞች ተቀጥረው የሚሰሩባቸው እና ባህላዊ የጎጆ ቤትን እሳቤ ከዘመናዊነት ጋር አዋህደው የተሰሩት” ግንባታዎች እንዲፈርሱ በመታዘዙ ማዘናቸውን ገልጸዋል። ተከራይዩ ጎጆ ቤቶቹ ባሉበት ቦታ ላይ ህዝብ የሚገለገልበት “ፕላዛ” ለመገንባት እንደታሰበ መስማታቸውን ይጠቅሳሉ። 

ጎጆ ቤቶቹን “አሁን እየሰጡ ካሉት አገልግሎት ብዙ ለማይለይ አገልግሎት ማፍረስ” ተገቢ ውሳኔ እንዳልሆነ እኚሁ ተከራይ ያስረዳሉ። “ከውበት፣ የኢኮኖሚ እና ቦታ አጠቃቀም አንጻር ውሳኔው በድጋሚ ቢታይ ጥሩ ነው” ሲሉም ያሳስባሉ። ስፍራውን የሚያውቁ አንድ የኪነ ህንጻ ባለሙያም “ቦታው መስቀል አደባባይ አካባቢ እንደመገኘቱ፤ በቅርብ ከተሰሩት ጋር ተናብቦ ለማቆየት፤ ዲዛይኑ ውስጥ ከመጀመሪያው ተጣጥሞ የተሰሩ መጠነኛ የውሃ ገንዳ እና ላንድስኬፕ ወቅቱን እንዲያማክሉ ማድረግ ይቻላል” ሲሉ የተከራዩን አስተያየት ያጠናክራሉ። 

ጎጆ ቤቶቹ ከመስታወት የተሰራ ግድግዳ ያላቸው መሆናቸው፣ ከእነርሱ ውስጥ የተወሰኑቱ አልፎ ሂያጅ መንገደኛ በጸሀይ እና በዝናብ እንዲጠለልባቸው ተደርገው መሰራታቸው እና በጀርባቸውም አረንጓዴ ስፍራ ማካተታቸው ከኮሪደር ልማቱ ጋር የተጣጣሙ መሆናቸውን በተጨማሪነት ያነሳሉ። ወደ ጎጆ ቤቶቹ የሚያስገባው ቦታ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ተደርጎ የተሰራ መሆኑንም በኪነ ህንጻ ባለሙያው የሚጠቀስ ሌላኛው የቦታው መለያ ነው። 

“የጎጆዎቹ መፍረስ ባይሆን ይመረጣል። የግድ መሆን አለበት ከተባለግን በቅርብ ቀለም የተቀብትን የጎጆዎቹን ጣራዎች እና የተሸከሟቸውን ለአይን የማይከብዱ ቋሚዎችን ሳይነኩ፤ አማራጭ መፍትሄዎችን ማየት ይበጃል” ሲሉም ይመክራሉ። የኪነ ህንጻ፣ የኢንጂነሪንግ እና የከተማ ፕላን ባለሙያዎች፤ ፍላጎቱን ባማከለ መልኩ በስፍራው ማሻሻያዎች ማድረግ እንደሚችሉም ያስገነዝባሉ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)