የውጪ ምንዛሬ ተመን በገበያ በመወሰኑ “ለሚመጣው ምስቅልቅል”፤ መንግስት ሙሉ ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ኢዜማ ገለጸ

በሙሉጌታ በላይ

መንግስት “በገበያ ላይ የተመሰረተ” የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርዓትን ተግባራዊ ማድረጉን ተከትሎ፤ በሀገር እና በህዝብ ላይ ለሚደርሰው ማንኛውም “የምጣኔ ሀብት፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ምስቅልቅል” ሙሉ ኃላፊነቱን የሚወስደው መንግስት እንደሆነ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አስታወቀ። ፓርቲው ይህንን የገለጸው ኢትዮጵያ መንግስት “በገንዘብ ፖሊሲ ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ” አስመልክቶ ዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 23፤ 2016 ባወጣው መገለጫ ነው። 

ኢዜማ በዚሁ መግለጫው የገንዘብ ፖሊሲን ጨምሮ አጠቃላይ ሀገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገትን በሚመለከቱ ጉዳዮች “መንግስት በቀጥታ እና በንቁ ሁኔታ ጣልቃ መግባት ካልቻለ፤ “ከጥልቅ ድህነት መውጣትም ሆነ ማህበራዊ ፍትሕን ማረጋገጥ እንደማይቻል” በጽኑ እንደሚያምን ገልጿል። የኢትዮጵያ መንግስት የገባበትን “ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት” እና “አጠቃላይ የምጣኔ ሀብት አጣብቂኝ” “እረዳለሁ” ያለው ፓርቲው፤ ሆኖም መንግስት ለችግሮቹ የወሰደውን መፍትሔ ተችቷል።

የአምራች ዘርፉ “እንጭጭ በሆነ” እና ከውጭ በሚገቡ ሸቀጦች ላይ “ጥገኛ ለሆነች ሀገር” መንግስት የተከተለው መፍትሔ፤ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪን በማስከተል “የዋጋ ንረትን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያባብስ” መሆኑን ፓርቲው አስታውቋል። መንግስት ሊከሰት የሚችል የዋጋ ንረትን “ለማስታመም የሚያስችሉ”፤ የደመወዝ ጭማሪ፣ ድጎማዎች፣ የሴፍቲኔት መርኃ ግብሮች እና ሌሎች እርምጃዎች እንደሚወስድ ማስታወቁን ፓርቲው በመግለጫው አስታውሷል። 

ሆኖም እነዚህ እርምጃዎች “ለጊዜው ማስታገሻ ከመሆን ባለፈ” ችግሩን በዘላቂነት ሊፈቱ የሚችሉ መፍትሔዎች አለመሆናቸውን ፓርቲው አስገንዝቧል። በኢትዮጵያ ለሚስተዋለው “ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት” መፍትሔው፤ የምርት ኃይሎች ወደ ስራ እንዲገቡ እንቅፋት የሆኑ “የፖለቲካ ስንክሳሮችን መፍታት ነው” የሚል እምነቱን ኢዜማ በዛሬው መግለጫው አንጸባርቋል። የሀገሪቱን እድገት “አንቀው የያዙ” በሚል ፓርቲው ከጠቀሳቸው ውስጥ “የሰላም እጦት” እና “የዘውጌ ፌደራሊዝም” ይገኙበታል። 

እነዚህን ችግሮች ከመፍታት በተጨማሪ ወደተለያዩ የምጣኔ ሀብት ክፍሎች “ሚዛን የጠበቀ የሀብት ፍሰት እንዲኖር ማድረግ” የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ሊፈታ እንደሚችል ኢዜማ በመግለጫው ጠቁሟል። በዚህ ረገድ በተለይ ለግብርና ዘርፉ ተገቢውን ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ፓርቲው አሳስቧል።  

“ግብርና ለአጠቃላዩ ጥቅል ሀገራዊ ምርት እና የስራ ፈጠራ ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ አንሳር የሚገባውን በጀት እስካልተመደበለት፣ ዘርፉን ብቃት ባላቸው ግለሰቦች እንዲመራ እስካልተደረገ እና መሰረታዊው የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ እልባት እስካላገኘ ድረስ፤ የውጪ ምንዛሬ ተመን በገበያ መወሰኑ የዋጋ ንረትን ከማባባስ ያለፈ ዘላቂ እና መሠረታዊ ችግሮቻችንን የመፍታት ፋይዳ አይኖረውም” ሲል ፓርቲው አጽንኦት ሰጥቷል። 

“የውጭ ምንዛሬን በገበያ መወሰንን በሚመለከት በተወሰነው ውሳኔ የሚመጣውን ማንኛውም በሀገርና በሕዝብ ላይ የሚደርስ የምጣኔ ሀብት፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ምስቅልቅል ውሳኔውን ያሳለፈው መንግሥት ሙሉ ኃላፊነቱን የሚወስድ መሆኑን እንገልጻለን”

– የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)

ኢዜማ የገንዘብ ፖሊሲን በተመለከተ ያለውን አቋም፤ “በተደጋጋሚ ጊዜ ለመንግስት እና ለህዝብ ሲያሳውቅ ቢቆይም” “ሰሚ ጆሮ” እንዳላገኘ በዛሬው መግለጫው ጠቅሷል። የውጭ ምንዛሬን ተመን በገበያ እንዲመራ በመደረጉ፤ በሀገር እና በህዝብ ላይ ለሚደርስ “የምጣኔ ሀብት፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ምስቅልቅል” ሙሉ ኃላፊነቱን የሚወስደው “ውሳኔውን ያሳለፈው መንግስት መሆኑንም” ፓርቲው ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)