ህወሓት የምርጫ ቦርድን የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ “አልቀበልም” አለ 

በተስፋለም ወልደየስ

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለፓርቲው “በልዩ ሁኔታ” የሰጠውን የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ፤ የቀድሞውን ህልውናውን “ወደነበረበት የማይመልስ” በመሆኑ እንደማይቀበለው አስታወቀ። ፓርቲው ያቀረበው ጥያቄ እስኪመለስ ድረስ፤ የህወሓት “ህገ ደንብ በሚፈቅድለት መልኩ ተያያዥ ስራዎችን እንደሚያከናውን” ገልጿል።

ብሔራዊው ምርጫ ቦርድ የህወሓትን “በልዩ ሁኔታ መመዝገብ እና የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ ማግኘትን” አስመልክቶ የደረሰበትን ውሳኔ ይፋ ያደረገው በትላንትናው ዕለት ነበር። ምርጫ ቦርድ በዚሁ ውሳኔው፤ ህወሓት  “የቀድሞው ህልውና ወደነበረበት እንዲመለስ” ያቀረበውን ጥያቄ አለመቀበሉን አስታውቆ ነበር። 

ቦርዱ ለዚህ ውሳኔው በማስረጃነት ያቀረበው፤ ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ የተሻሻለውን “የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነምግባር” አዋጅን ነው። አዋጁ “በአመጽ ተግባር ተሰማርቶ ለተሰረዘ ፓርቲ የቀድሞውን ህልውና መልሶ የሚሰጥ የህግ ድንጋጌ ያልያዘ መሆኑን” የጠቀሰው ቦርዱ፤ በዚህ ምክንያት የህወሓት ጥያቄ ተቀባይነት አለማግኘቱን አስገንዝቧል። 

ምርጫ ቦርድ ያሳለፈውን ውሳኔ የያዘ ደብዳቤ እንደደረሰው፤ ህወሓት ዛሬ ቅዳሜ ነሐሴ 4፤ 2016 ባወጣው መግለጫ አረጋግጧል። ፓርቲው በዚሁ መግለጫው፤ “በቦርዱ ውሳኔ ላይ የተካተቱት ዝርዝር ይዘቶች አዲስ በወጣው ማሻሻያ ህግ መሰረት የተቀመጡ እና ህወሓት ካቀረበው ጥያቄ ጋር የማይገናኙ ናቸው” ብሏል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህወሓትን በልዩ ሁኔታ መመዝገቡን የገለጸውም ይህን የማሻሻያ ህግ መሰረት በማድረግ መሆኑን ፓርቲው በመግለጫው ጠቅሷል። ሆኖም ምርጫ ቦርድ ያሳለፈው ውሳኔ፤ “ድርጅታችን ህጋዊ ሰውነቱ ወደነበረበት እንዲመለስ ያቀረበውን ጥያቄ የማይመልስ በመሆኑ አልተቀበለውም” ሲል ህወሓት በዛሬ መግለጫው አቋሙን አስታውቋል። 

“ውሳኔው በፕሪቶሪያው ስምምነት ያልተመሰረተ፣ ከዚህ በፊት በሌሎች የፌደራል ተቋማት የተሰጡትን ውሳኔዎች እንዲሁም የነበሩ ውይይቶችን የሚቃረኑ ዝርዝር ይዘቶች በህወሓት ላይ የሚጭን በመሆኑ፤ የቀረበው ጥያቄ እስኪመለስ ድረስ፤ ህወሓት የፓርቲው ህገ ደንብ በሚፈቅድለት መልኩ ተያያዥ ስራዎችን ያከናውናል” ሲል ፓርቲው በቀጣይ ሊተገብር ያቀደውን በመግለጫው አመልክቷል።

ህወሓት “ተያያዥ ስራዎች” ያላቸውን ጉዳዮች፤ በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ባጋራው መግለጫ ላይ በግልጽ አላስቀመጠም። ህወሓት የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ከመተላለፉ አስቀድሞ፤ ጠቅላላ ጉባኤውን በሐምሌ ወር መጨረሻ እንደሚያካሄድ አስታውቆ የነበረ ቢሆንም ጉባኤው በተባለው ጊዜ ሳይደረግ ቀርቷል። 

ሆኖም ፓርቲው ጠቅላላ ድርጅታዊ ጉባኤውን ለማከናወን የሚያስችሉ ዝግጅቶችን መቀጠሉን፤ ባለፉት ቀናት በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ በሚያወጣቸው መረጃዎች ሲገልጽ ቆይቷል። ህወሓት ጉባኤውን መቼ እንደሚያካሄድ እስካሁን በይፋ የገለጸው ነገር ባይኖርም፤ የዝግጅቱ ሂደቱ በምክትል ሊቀመንበሩ አቶ ጌታቸው ረዳ እና በፓርቲው ማዕከላዊ የቁጥጥር ኮሚሽን ተቃውሞ ቀርቦበታል። 

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ ጌታቸው፤ ሂደቱ “ዲሞክራሲያዊ እና ህጋዊ አይደለም” በሚል ራሳቸውን ከጠቅላላ ጉባኤው ማግለላቸውን በትላንትናው ዕለት አስታውቀዋል። አቶ ጌታቸው በዛሬው ዕለት ለምርጫ ቦርድ በጻፉት ደብዳቤ ደግሞ ህወሓት ለቦርዱ ያቀረበው “የምዝገባ ጥያቄ”፤ “የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ የማያውቀው ነው” ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

ህወሓት ይህን ጥያቄ ባቀረበበት ወቅት፤ የፓርቲውን ኃላፊዎች ስም እና ፊርማ የያዘ ሰነድ ማቅረቡን ከምርጫ ቦርድ መግለጫ መረዳታቸውን አቶ ጌታቸው በደብዳቤያቸው ጠቅሰዋል። “እኛ ለዚህ ምዝገባ ብለን የፈረምነው ምንም አይነት ሰነድ ሳይኖር፤ ግለሰቦች በቡድን ተደራጅተው፣ ከድርጅቱ አሰራር ውጭ የፈጸሙት ተግባር መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን” ሲሉም የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር በደብዳቤያቸው አስገንዝበዋል።

ፓርቲው ዛሬ ምሽት ባወጣው መግለጫ፤ አቶ ጌታቸው በደብዳቤያቸው ላነሱት ጉዳይ ምላሽ ሰጥቷል። ህወሓት ለምርጫ ቦርድ ያቀረባቸው ሰነዶች “የተሰረዘውን ህጋዊ ሰውነቱን ወደነበረበት እንዲመለስ የሚያግዙ” መሆናቸውን ያመለከተው ፓርቲው፤ እነርሱም “የፓርቲው ፕሮግራም፣ መተዳደሪያ ደንብ እና የጠቅላላ አመራሮቹ ዝርዝር የያዙ” እንደሆነ አብራርቷል።

ህወሓት “በማሻሻያ አዋጁ መሰረት የስራ አስፈጻሚ አባላት ስም፣ አድራሻ እና በተለየ ኃላፊነት ወስደው ቃል የሚገቡበትን የተፈረመ ሰነድ አላቀረበም” ሲል ፓርቲው በመግለጫው አክሏል። ብሔራዊው ምርጫ ቦርድ በትላንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ ህወሓት ለቦርዱ ያቀረባቸው “የፖለቲካ ፓርቲው ፕሮግራም፣ የመተዳደሪያ ደንብ፣ የፓርቲው ኃላፊዎች ስምና ፊርማ የያዙ ሰነዶች” መሆናቸውን አስታውቆ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]