የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሁለተኛ ዙር ውይይት ነገ በአንካራ ሊካሄድ ነው

በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለመፍታት በቱርክ የተጀመረው ሽምግልና ሁለተኛ ዙር ንግግር ከታቀደለት ጊዜ አስቀድሞ ሊካሄድ ነው። በቱርክ ዋና ከተማ አንካራ በሚካሄደው እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታዬ አጽቀሥላሴ እንዲሁም የሶማሊያ አቻቸው አህመድ ሙዓሊም ፊቅ የሚሳተፉበት ውይይት፤ ነገ ሰኞ እንደሚካሄድ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ አንድ የዲፕሎማቲክ የመረጃ ምንጭ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር በተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት ምክንያት ከሶማሊያ ጋር ለገባችበት ውዝግብ መፍትሔ ለማበጀት፤ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታዬ እና የሶማሊያ አቻቸው በአንካራ ያደረጉት የመጀመሪያ ዙር ውይይት ያለ ውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል። የሁለቱ ሀገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፤ በዚህ ወር መጨረሻ ዳግም ለመገናኘት ቀጠሮ መያዛቸውም በወቅቱ ተገልጾ ነበር። 

ሁለተኛው ዙር ውይይት ከታቀደለት ጊዜ አስቀድሞ እንደሚካሄድ አስቀድመው ያስታወቁት፤ ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ግብጽን ጎብኝተው የተመለሱት የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሐካን ፊዳን ናቸው። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከጉብኝታቸው በኋላ ከትላንት በስቲያ አርብ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ “በሚቀጥለው ሳምንት ሁለተኛ ዙር ውይይት ለማድረግ አቅደናል” ሲሉ ተናግረዋል። 

የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት ባወጣው መረጃ፤ በአህመድ ሙዓሊም ፊቅ የሚመራ ልዑካን ቡድን ነገ ሰኞ ነሐሴ 6፤ 2016 በሚካሄደው ውይይት ላይ  ለመሳተፍ በትላንትናው ዕለት ወደ አንካራ ማምራቱን አስታውቋል። የነገውን ሁለተኛ ዙር ውይይት የምታስተናግደው ቱርክ፤ በሶማሊያ እና ኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ ለመፍታት እስካሁን ከተደረጉ ጥረቶች ሁሉ የተሻለ መሻሻል ማሳየቷ ይነገርለታል። 

ቱርክ የጀመረችው የሽምግልና ጥረት፤ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ረጂብ ጣይብ ኤርዶኻን በትላንትናው ዕለት ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር በነበራቸው የስልክ ንግግር ውይይት ወቅት መነሳቱን ጽህፈት ቤታቸው አስታውቋል። “ሶማሊያ አንድነቷን፣ ሉዓላዊነቷን እና የግዛት አንድነቷን በተመለከተ ያሉባትን ስጋቶች ለማስወገድ ኢትዮጵያ የምትወስዳቸው እርምጃዎች”፤ ቱርክ “ውጥረቱን ለመፍታት” የጀመረችውን ሂደት እንደሚያመቻች ኤርዶኻን ተናግረዋል ተብሏል። 

የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በስልክ ውይይት ማድረጋቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ዛሬ ባወጣው መረጃ አረጋግጧል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ “በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተከሰተውን የሃሳብ ልዩነት ለመፍታት ላደረጉት ጥረት ለኤርዶኻን “ምስጋና” ማቅረባቸውን ጠቅሷል። አብይ በዚሁ ውይይት “የ120 ሚሊዮን ህዝብ ሀገር ለሆነችው ኢትዮጵያ፤ በጋራ ስምምነት መንገድ የባህር በር የማግኘት አስፈላጊነትንም አጽንኦት ሰጥተው አንስተዋል” ሲል ጽህፈት ቤታቸው አስታውቋል። 

የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሐካን ፊዳን በአርቡ መግለጫቸው፤ ሀገራቸው ለሶማሊያ እና ኢትዮጵያ መንግስታት ባቀረበችው ምክረ ሃሳብ የባህር በር ጉዳይ መካተቱን ጥቆማ ሰጥተዋል። ምክረ ሃሳቡ “ኢትዮጵያ ያለ ምንም ጥርጥር የሶማሊያን የግዛት አንድነት እና ፖለቲካዊ ሉዓላዊነት አክብራ፤ በሶማሊያ በኩል የባህር በር ማግኘት የምትችልበት” እንደሆነ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። 

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያን ለውዝግብ የዳረጋቸው የመግባቢያ ስምምነት፤ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና በሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሒ አብዲ የተፈረመው ባለፈው ታህሳስ ወር መጨረሻ ነበር። የመግባቢያ ስምምነቱ ዝርዝር እስካሁን ይፋ ባይደረግም፤ ኢትዮጵያ የባህር ኃይል የምትመሰረትበት የጦር ሰፈር እና ለንግድ አገልግሎት የሚውል ወደብ እንድታገኝ የሚፈቅድ እንደሆነ በወቅቱ ተገልጿል። 

የመግባቢያ ስምምነቱ ተግባራዊ ሲሆን ኢትዮጵያ ለሶማሌንድ እውቅና እንደምትሰጥ ውሉን የተፈራረሙት ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሒ በወቅቱ ተናግረው ነበር። የሶማሊያ መንግስት ለሶማሌላንድ የሚሰጥ እውቅና፤ በሀገሪቱ ሉዓላዊነት ላይ የሚፈጸም “ጥቃት” እንደሆነ በመግለጽ ሲቃወም ቆይቷል። 

ሶማሌላንድ ራስ ገዝ ብትሆንም፤ ሶማሊያ የግዛቴ አካል ናት የሚል ጽኑ አቋም አላት። የሶማሊያ መንግስት በኢትዮጵያ እና በሶማሌላንድ መሪዎች የተፈረመው ስምምነት “ህጋዊ ተቀባይነት የሌለው” በማለት ውድቅ ማድረጉም አይዘነጋም። ሶማሊያ በሞቃዲሾ የነበሩትን የኢትዮጵያ አምባሳደር ከማባረር አንስቶ ጉዳዩን እስከ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት ብታደርስም፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ውዝግብ እስካሁን እልባት አላገኘም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)