የህወሓት ህጋዊ ሰውነትን የመመለስ ጉዳይ፤ በህግ እና በምርጫ ቦርድ አሰራር “ብቻ” እልባት የሚያገኝ መሆኑን የፌደራል መንግስት አስታወቀ 

በተስፋለም ወልደየስ

የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የህግ ሰውነት የማግኘት ጉዳይ “አግባብነት ባለው ህግ” እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ “አሰራር መሰረት ብቻ” እልባት ማግኘት የሚገባው መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ። የፓርቲውን የህግ ሰውነት እና የምዝገባ ጉዳይ በተመለከተ፤ የፌደራል መንግስት “በፕሪቶሪያ ስምምነት ውስጥ የወሰደው የተለየ ኃላፊነት ወይም ግዴታ የለም” ሲልም አስታውቋል።

የኢፌዲሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ይህን ያስታወቀው፤ ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 6፤ 2016 ባወጣው መግለጫ ነው። የኮሙኒኬሽን መስሪያ ቤቱ መግለጫውን ያወጣው፤ ህወሓት በብሔራዊው ምርጫ ቦርድ “በልዩ ሁኔታ” የ የተሰጠውን የህጋዊ ሰውነት የማረጋገጫ የምስክር ወረቀት “አልቀበለም” ማለቱን ካስታወቀ ከሁለት ቀን በኋላ ነው።

ህወሓት የምርጫ ቦርድን ውሳኔ ያልተቀበለው፤ ፓርቲው “ህጋዊ ሰውነቱን ወደነበረበት እንዲመለስ ያቀረበውን ጥያቄ የማይመልስ በመሆኑ” ምክንያት እንደሆነ ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር። የምርጫ ቦርድ ውሳኔ “በፕሪቶሪያው ስምምነት ያልተመሰረተ”፣ ከዚህ በፊት በሌሎች የፌደራል ተቋማት የተሰጡትን ውሳኔዎች እንዲሁም የነበሩ ውይይቶችን “የሚቃረኑ ዝርዝር ይዘቶች በህወሓት ላይ የሚጭን ነው” ሲል ፓርቲው በቅዳሜው መግለጫው ተችቷል።


የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ይህንኑ በተመለከተ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ የፌደራል መንግስት በፕሪቶሪያ ስምምነት የገባው ግዴታ “የህወሓት ሽብርተኝነት እንዲነሳ ሂደቱን የማሳለጥ ኃላፊነት” መሆኑን አስታውሷል። በዚሁ ስምምነት ውስጥ የፌደራል መንግስት የህወሓትን የህግ ሰውነት እና የምዝገባ ጉዳይ በተመለከተ “የወሰደው የተለየ ኃላፊነት ወይም ግዴታ” እንደሌለም የኮሙኒኬሽን መስሪያ ቤቱ ገልጿል። 

መስሪያ ቤቱ በዚሁ መግለጫው፤ በጥቅምት 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተደረገው የግጭት ስምምነት በህወሓት ላይ የጣለውን ግዴታ ጠቅሷል። በስምምነቱ መሰረት፤ ህወሓት “የሀገሪቱን ሕገ መንግስት፣ ህጎች፣ የፌደራል ተቋማት እና ሌሎች ህገ መንግስታዊ ተቋማትን ስልጣን የማክበር ግዴታ ገብቷል” ሲል መግለጫው አትቷል።

“ህወሓት የሀገሪቱን የፖለቲካ ፓርቲዎች የምዝገባ ህግ እና የምርጫ ቦርድን ስልጣን በማክበር የመስራት ግዴታ እንዳለበት ግልጽ ነው” ያለው የኮሙኒኬሽን መስሪያ ቤቱ፤ “ከፕሪቶሪያ ስምምነት አኳያም ሲታይ የህወሓት የህግ ሰውነት ጉዳይ አግባብነት ባለው ህግ እና በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሰራር መሰረት ብቻ እልባት ሊያገኝ የሚገባ ጉዳይ ነው” ሲል የፌደራል መንግስትን አቋም አስታውቋል። 

ከፕሪቶሪያ ስምምነት አኳያም ሲታይ የህወሓት የህግ ሰውነት ጉዳይ አግባብነት ባለው ህግ እና በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሰራር መሰረት ብቻ እልባት ሊያገኝ የሚገባ ጉዳይ ነው

– የኢፌዲሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

የህወሓት ህጋዊ ሰውነት ጉዳይ መፍትሔ እንዲያገኝ “ከመንግስት በኩል ሊደረግ የሚችለው ሁሉ ተደርጓል” ያለው  ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፤ ይህንኑ የተመለከቱ ጥረቶችን እና ሂደቶችን በመግለጫው ዘርዝሯል። “የፌደራል መንግስት ከግማሽ ርቀት በላይ ሄዶ፣ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት ከሚጠበቅበት እና ካለበት ግዴታ አልፎ ከምርጫ ቦርድ እና ከህወሓት ጋር በጉዳዩ ላይ ተከታታይ ውይይቶች አድርጓል” ሲልም መግለጫው አክሏል።

በዛሬው የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ የተጠቀሰው ዝርዝር፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ  ከሁለት ሳምንት በፊት ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ የሰጡትን ማብራሪያ ያስተጋባ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ማብራሪያቸው፤ ህወሓት በምርጫ ቦርድ ተመዝግቦ ህጋዊ ፓርቲ እንዲሆን በፌደራል መንግስት በኩል መከናወን የሚገባቸው ስራዎች “መቶ በመቶ” መፈጸማቸውን ገልጸዋል። 

“ፓርቲ ለፓርቲ፤ መንግስት ለመንግስት ውይይቶች ነበሩን። ጥያቄዎች ተነስተው መልሰናል” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ተናግረው ነበር። ህወሓት ማድረግ የሚጠበቅበት “አስፈላጊውን ሰነድ አሟልቶ” ወደ ምርጫ ቦርድ በመሄድ “በህጋዊ መንገድ ተመዝግቦ ጉባኤ ማካሄድ” መሆኑንም በማብራሪያቸው ጠቁመዋል። 

ፓርቲው “[ይህንን] ባያደርግ እኔ ብፈልግም ባልፈልግም፤ ዋጋ የለውም። ምርጫ ቦርድ ካልተቀበለው፣ ህጋዊ ፓርቲ ካላለው፣ በምርጫ ሊሳተፍ አይችልም። መንግስት ሊሆን አይችልም” በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሂደቱን አንደምታ አስረድተዋል። ህወሓት ህጋዊ መንገዱን ተከትሎ ጉባኤ ካላካሄደ፤ “ተመልሰን ጦርነት እንገባለን ማለት ነው” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ አስጠንቅቀው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ህወሓት ምዝገባውን በምርጫ ቦርድ አጠናቅቆ፣ በህጋዊ መንገድ ጉባኤ ማካሄድ እንደሚችል ቢገልጹም፤ ፓርቲው ከትላንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ ግን ለምርጫ ቦርድ ያቀረበው ጥያቄ እስኪመለስ ድረስ “የፓርቲው ህገ ደንብ በሚፈቅድለት መልኩ ተያያዥ ስራዎችን” እንደሚያከናውን አስታውቋል። ህወሓት “ተያያዥ ስራዎች” ያላቸውን ጉዳዮች በመግለጫው በግልጽ ባይጠቅስም፤ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ታዛቢዎች ግን ፓርቲው ሊያደርገው ካቀደው ጠቅላላ ጉባኤ ጋር አያይዘውታል። 

ህወሓት ጠቅላላ ጉባኤውን በሐምሌ ወር መጨረሻ እንደሚያካሄድ ቀደም ሲል አስታውቆ የነበረ ቢሆንም፤ ጉባኤው በተባለው ጊዜ ሳይከናወን ቀርቷል። ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤውን ነገ ማክሰኞ ነሐሴ 7፤ 2016 እንደሚያካሄድ በዛሬው  ዕለት ይፋ ተደርጓል። የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳ ጨምሮ 14 የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፤ በጠቅላላ ጉባኤው እንደማይሳተፉ በትላትናው ዕለት ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃዎች ታክለውበታል]