በነገው ዕለት ለሚካሄደው የህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ፤ ምርጫ ቦርድ “እውቅና አልሰጥም” አለ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በነገው ዕለት ለሚያካሄደው ጠቅላላ ጉባኤም ሆነ በጉባኤው ላይ ለሚተላለፉ ውሳኔዎች በሙሉ “እውቅና እንደማይሰጥ” አስታወቀ። ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ከማድረጉ 21 ቀናት በፊት ለምርጫ ቦርድ ማሳወቅ እና ፓርቲው በሚያደርገው ጠቅላላ ጉባኤ የቦርዱ ታዛቢዎች መገኘት እንደነበረባቸውም አስታውቋል።

ብሔራዊው ምርጫ ቦርድ ይህን ያስታወቀው፤ ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 6፤ 2016 ለህወሓት በጻፈው ደብዳቤ ነው። የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ፊርማ ያረፈበት ይህ ደብዳቤ፤ ህወሓት “ጠርቶታል” የተባለውን ጠቅላላ ጉባኤ የሚመለከት እንደሆነ በመግቢያው ላይ ተቀምጧል።

ይኸው ደብዳቤ፤ ህወሓት በቦርዱ “በልዩ ሁኔታ” እንዲመዘገብ ከተደረገ በኋላ ከቦርዱ የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት እንደተሰጠው አስታውሷል። ህወሓት ይህ የምስክር ወረቀት ከደረሰው በኋላ የሚተዳደረው፤ በ2011 ዓ.ም በወጣው እና ባለፈው ግንቦት ወር በተሻሻለው፤ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ  መሰረት መሆኑንም ቦርዱ ጠቅሷል። 

ቦርዱ ይህን አዋጅ መሰረት በማድረግ ባለፈው ሳምንት አርብ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች መካከል፤ የፓርቲውን ጠቅላላ ጉባኤ የሚመለከተው እንደሚገኝበት በዛሬው ደብዳቤው አመልክቷል። ቦርዱ በዚሁ ውሳኔው፤ ህወሓት በልዩ ሁኔታ ከተመዘገበበት ዕለት ጀምሮ ባሉት ስድስት ወራቶች ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ እንዳለበት አሳስቦ ነበር። 

ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤውን ከማድረጉ ከ21 ቀናት በፊት ለምርጫ ቦርዱ ማሳወቅ እንዳለበትም በውሳኔው ላይ ሰፍሯል። ቦርዱ ይህን ቀነ ገደብ የሰጠው “የፓርቲውን የቅድመ ጉባኤ ዝግጅት የተመለከቱ ስራዎችን ለመከታተል እንዲረዳው” መሆኑን በወቅቱ ገልጿል። 

ህወሓት ጠቅላላ ጉባኤውን ማካሄድ ያለበት “የቦርዱ ታዛቢዎች በሚገኙበት” እንደሆነም የቦርዱ ውሳኔ ያትታል። ብሔራዊው ምርጫ ቦርድ እነዚህን “ግዴታዎች” ለፓርቲው ቢያሳውቅም፤ ህወሓት ጠቅላላ ጉባኤውን እንደሚያደርግ የተረዳው በመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች መሆኑን በዛሬው ደብዳቤው ላይ ገልጿል። 

“ቦርዱ ለአንድ ጠቅላላ ጉባኤ መደረግ አስፈላጊ የሆኑ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እንዲያውቅ ባልተደረገበት፣ ባልተከታተለበት እና ባላረጋገጠበት እንዲሁም የቦርዱ ታዛቢዎች ባልተገኙበት ተጠራ የተባለው ጠቅላላ ጉባኤ ሊካሄድ አይችልም” ሲልም በደብዳቤው አጽንኦት ሰጥቷል።

ምርጫ ቦርድ ይህን ቢልም፤ ህወሓት ጠቅላላ ጉባኤውን ነገ ማክሰኞ ነሐሴ 7፤ 2016 እንደሚያካሄድ ይፋ አድርጓል። በጠቅላላ ጉባኤው ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችም፤ ከትላንትና ጀምሮ ወደ መቀለ ከተማ በመግባት ላይ መሆናቸውንም ፓርቲው በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጹ ላይ በተከታታይ እያስተዋወቀ ይገኛል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጠቅላላ ጉባኤው ከራሱ ፍቃድ ውጭ ከተካሄደ “ለጉባኤውም ሆነ በጉባኤዎቹ ላይ ለሚወሰኑ ውሳኔዎች በሙሉ እውቅና እንደማይሰጥ” በዛሬ ደብዳቤው አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)