በጋምቤላ ክልል በጎርፍ አደጋ ሳቢያ ከ57 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ሊፈናቀሉ ይችላሉ ተባለ

በሙሉጌታ በላይ

በጋምቤላ ክልል በዘንድሮ የክረምት ወቅት የጎርፍ አደጋ ሊያጋጥማቸው ይችላል ተብለው ከተለዩ ዘጠኝ ወረዳዎች ከ57 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ የክልሉ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር አገልግሎት ኃላፊ አቶ ጋትቤል ሙን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ። ባለፈው ቅዳሜ በክልሉ ባሉ አራት ወረዳዎች ባጋጠመ የጎርፍ አደጋ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ቁጥር 17 ሺህ መድረሱንም ኃላፊው ተናግረዋል።

የጎርፍ አደጋው የተከሰተው፤ ከሶስት ቀናት በፊት አርብ ምሽት በጣለው ከባድ ዝናብ የአኮቦ እና ጊሎ ወንዞች ሞልተው ጎግ፣ ላሬ፣ ጆር እና ዋንቱዋ የተባሉት ወረዳዎችን በማጥለቅለቃቸው መሆኑን አቶ ጋትቤል አስረድተዋል። በአደጋው የሞተ ሰው አለመኖሩን የገለጹት ኃላፊው፤ ሆኖም “በንብረት፣ በሰብል እና ከብቶች ላይ ግን ጉዳት ደርሷል” ብለዋል።

በጎርፍ መጥለቅለቁ ሳቢያ እስከ ትላንት ድረስ 16 ሺህ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን መረጋገጡን የገለጹት ኃላፊው፤ የተፈናቃዮቹ ቁጥር በትላንትናው ዕለት መጨመሩን አስረድተዋል። ሁሉም ተፈናቃዮች በየወረዳዎቹ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንዲጠለሉ መደረጉን አቶ ጋትቤል አመልክተዋል። 

ፎቶ፦ የጋምቤላ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት 

ተፈናቃዮቹን በጤና ጣቢያዎች ውስጥ እንዲጠለሉ ለማድረግ ታስቦ የነበረ ቢሆንም፤ ተቋማቱ የሚሰጡትን አገልግሎት ላለማስተጓጎል ለጊዜው በትምህርት ቤቶች ብቻ እንዲቆዩ መደረጋቸውን አብራርተዋል። ለተፈናቃዮቹ በአሁኑ ወቅት የሚመገቡትን እያቀረቡላቸው የሚገኙት፤ በተጠለሉባቸው አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች እንደሆኑ የጋምቤላ ክልል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር አገልግሎት ኃላፊ ጠቁመዋል። 

“መጀመሪያ የተደረገው ነዋሪዎቹ ከተፈናቀሉበት ውሃማ ቦታ፤ ወደ ደረቃማ ቦታ መውሰድ ነው። ህጻናት፣ አዛውንቶች ወደ ደረቃማ ቦታ እንዲጓጓዙ [ተደርጓል]። መጀመሪያ በተሰራው ስራ፤ ያልወደመ ንብረታቸውም ተጓጉዟል። ከዚያ በኋላ በአካባቢው ያለ ህዝብ፣ በእጃቸው ያለው ነገር ሁሉ ተሰብስቦ፣ ድጋፍ ማድረግ ሁለተኛ ስራ ነው የሆነው” ሲሉ አቶ ጋትቤል የዕለት ደራሽ እርዳታ በማቅረብ ረገድ ያለውን ሂደት አብራርተዋል። 

በጎርፍ አደጋ ከተፈናቀለው የክልሉ ነዋሪ ብዛት እና እየተደረገ ካለው ድጋፍ አንጻር፤ ተፈናቃዮቹ “ከባድ ችግር ውስጥ ናቸው” ይላሉ ኃላፊው። ተፈናቃዮቹ የውሃ ሙላቱ እስኪጎድል ድረስ በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚቆዩ በመሆኑ፤ ለእነዚህ ጊዜያት የሚበቃ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸውም ያሳስባሉ። 

ፎቶ፦ የጋምቤላ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት 

የጋምቤላ ክልል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር አገልግሎት ተፈናቃዮቹ ስላሉበት ሁኔታ ለክልሉ መንግስት ማስታወቁን አቶ ጋትቤል ገልጸዋል። ተቋማቸው ለተፈናቃዮቹ ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑንም አክለዋል። 

በጋምቤላ ክልል በዘንድሮው የክረምት ወቅት “ከመደበኛው መጠን በላይ” ዝናብ ይዘንባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የሚቲዎሮሎጂ ትንበያዎች እንደሚያመለክቱ የተናገሩ አቶ ጋትቤል፤ ይህን ተከትሎም በዘጠኝ ወረዳዎች የሚገኙ ከ57 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ሊፈናቀሉ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳለ ጠቁመዋል። እነዚህን ነዋሪዎች “ቀድሞ ለማገዝ” ከክልሉ መንግስት ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

በክረምት ወቅት በጋምቤላ ክልል የተለያዩ ወረዳዎች የጎርፍ አደጋ ሲያጋጥም የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም። በ2015 ዓ.ም ከፍተኛ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ ሳቢያ፤ በክልሉ 12 ወረዳዎች የሚገኙ ቢያንስ 185 ሺህ ገደማ ነዋሪዎች ተፈናቅለው እንደነበር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (OCHA) በወቅቱ አስታውቆ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)