በተስፋለም ወልደየስ
ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በተለያዩ ወገኖች ተቃውሞ እና ትችት የተሰነዘረበትን የጠቅላላ ጉባኤ የመክፈቻ ስነ ስርዓት፤ ዛሬ ማክሰኞ ነሐሴ 7፤ 2016 በመቐለ ከተማ በሚገኘው የሰማዕታት ሐውልት አዳራሽ አካሄደ። ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤውን ያካሄደው ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ ጌታቸውን ረዳን ጨምሮ 14 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ባልተገኙበት ነው።
ህወሓት ከስድስት ዓመት በኋላ የጠራው የዛሬው ጠቅላላ ጉባኤ፤ ከዚህ ቀደም የነበሩ የአከባበር ሂደቶች ያልታዩበት ነበር። ጠቅላላ ጉባኤውን ያስተናገደችው የመቐለ ከተማ፤ በመሰል ስብሰባዎች ወቅት የሚታየው መጨናነቅ አልተስተዋለባትም። ወዳጅ ሀገራት ፓርቲዎችም ሆነ የሀገር ውስጦቹ አጋር ፓርቲዎችም፤ እንደ ድሮው የድጋፍ ንግግር ለማሰማት ወደ ከተማይቱ አልመጡም።
የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ እንደሚካሄድ ያበስሩ የነበሩ ግዙፍ “ቢልቦርዶች” በበርካታ ቦታዎች አልተሰቀሉም። በከተማይቱ ሶስት ቦታዎች የተተከሉት አነስተኛ የማስታወቂያ ሰሌዳዎችም፤ የሰውን ትኩረት ያን ያህል ሲስቡ አልታዩም። የጠቅላላ ጉባኤው ስሜት ይበልጥ ጎላ ብሎ የተስተዋለው፤ የህወሓት ጽህፈት ቤት በሚገኝበት እና በስብሰባው አዳራሽ አቅራቢያ ነው።
ወደ ሰማዕታት ሐውልት አዳራሽ ሲገባ የነበረው ስሜት ግን በውጭ ከሚታየው የተለየ ነበር። በቀይ ኮፍያ፣ በቢጫ የአንገት ልብስ እና በነጭ ቲሸርት የደመቁት የጉባኤተኛው ተሳታፊዎች፤ ከመድረክ ለሚተላለፉ ዝግጅቶች በእጃቸው የያዟቸውን ባንዲራዎች በማውለብለብ ድጋፋቸውን በጋለ ስሜት ሲሰጡ ታይተዋል።
በዛሬ የህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ የመክፈቻ ስነ ስርዓት በቀረቡ ዘፈኖችም ሆነ በሌሎች መሰናዶዎች በተደጋጋሚ ሲደመጥ የነበረው፤ ፓርቲው “ሳይከፋፈል እና ሳይፈርስ” በጽናት የሚቀጥል መሆኑን ነው። “የመዳን ጉባኤ” የሚለው የጠቅላላ ጉባኤው መሪ ቃል እና በአዳራሹ መድረክ ግድግዳ ላይ በተሰቀለው ባነር የተጻፈው “አደራችሁን እንዳትክዱ” የሚለው ኃይለ ቃል ይህንኑ ያስተጋባ ሆኗል።
በጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉት የህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል፤ ፓርቲውን ከመፍረስ የማዳንን ጉዳይ ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደው አብራርተዋል። “የ14ኛው ጉባኤ ዋና ተልዕኮ፤ ፓርቲያችንን እና ህዝባችንን ከጥፋት ማዳን ነው” ሲሉም ለጉዳዩ አጽንኦት ሰጥተውታል።
“ህወሓት ፈረሰ ማለት የፕሪቶሪያው ስምምነት ታሪክ ሆነ ቀረ ማለት ነው” ሲሉ የተደመጡት ዶ/ር ደብረጽዮን፤ ይህ አይነቱ አካሄድ “የትግራይን ህዝብ ለአደጋ ያጋልጠዋል” ሲሉ ጉዳዩ ከፓርቲም ተሻግሮ ከህዝብ ጋር የተሳሰረ መሆኑን አመልክተዋል። ህወሓትን ለማዳን ጥረት ሲደረግ “የማደናገሪያ ሃሳቦችን የሚያመጡ አሉ” ሲሉም ወንጅለዋል።
ዶ/ር ደብረጽዮን በህወሓት ውስጥ ያለ ቡድን፤ “የፓርቲው ህጋዊ እውቅና እንዳይመለስ” እና “ጠቅላላ ጉባኤውን እንዳያካሂድ ሲያደናቅፍ ነበር” ሲሉ በንግግራቸው ከስሰዋል። የፓርቲው ሊቀመንበር የቡድኑን አባላት ማንነት በግልጽ ባይጠቅሱም፤ በዚያው ንግግራቸው በፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ “የአመራር ብልሽት” መከሰቱን በማንሳት ተችተዋል።
ዛሬ የተጀመረው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ “ማስተካከያ” እንደሚያደርግም አስታውቀዋል። በመጪዎቹ ቀናት በሚቀጥለው የህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ፤ የፓርቲው የስድስት ዓመት ግምገማ እንደሚቀርብም ጠቁመዋል። የአሁኑ ጉባኤ በህወሓት ውስጥ ለሚስተዋሉ ችግሮች መፍትሔ እንደሚያመጣም የፓርቲው ሊቀመንበር እምነታቸውን ገልጸዋል።
እርሳቸው ይህን ቢሉም፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና የፌደራል መንግስት ግን ጉባኤው ህግን ያልተከለ መሆኑን በመጥቀስ እውቅና ነፍገውታል። ምርጫ ቦርድ ህወሓት ለሚያካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ እውቅና እንደማይሰጥ የገለጸው፤ ትላንት ለፓርቲው በጻፈው ደብዳቤ ነው።
ምርጫ ቦርድ በዚሁ ደብዳቤው፤ ህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ ከማድረጉ ከ21 ቀናት በፊት ሊያሳውቀው ይገባ እንደነበር አስታውቋል። ጠቅላላ ጉባኤ መካሄድ ያለበትም፤ የቦርዱ ታዛቢዎች በሚገኙበት እንደሆነም ቦርዱ ገልጿል። የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር አቶ ለገሰ ቱሉ፤ በዛሬው ዕለት በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት ህወሓት “ከምርጫ ቦርድ ፈቃድ ውጭ” ጠቅላላ ጉባኤውን ማካሄዱን ተችተዋል።
ህወሓትን “ግትር ባህሪ” ያለው ሲሉ የወቀሱት ሚኒስትሩ፤ ፓርቲው ያካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ “የትግራይ ህዝብ ያገኘውን አንጻራዊ ሰላም እንደመንጠቅ ይቆጠራል” ሲሉ ነቅፈዋል። ህወሓት የፕሪቶሪያውን ስምምነት “እንደመሸሸጊያ” ደጋግሞ እንደሚያነሳው የጠቀሱት አቶ ለገሰ፤ ስምምነቱ የፌደራል ተቋማትን አሰራሮች፣ ህጎች እና አካሄዶች በጥብቅ እንዲያከብር በፓርቲው ላይ “ግዴታ” የጣለበት እንደሆነ አስታውሰዋል።
“ቀድሞ የገባውን ግዴታ ሲሸራርፍ የመጣው ህወሓት ዛሬ በተጨባጭ ተግባር ደምስሶታል” ሲሉም የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ህወሓት ጠቅላላ ጉባኤውን እየካሄደ ባለበት ወቅት ባሰራጩት መልዕከት አስታውቀዋል። “አንዴ፣ ሁለቴ፣ መሳሳት ያለና የነበረ ነው። በተመሳሳይ መንገድ፤ ተመሳሳይ ስህተት ሶስቴ መፈጸም ግን የመጨረሻው የጥፋት መንገድ ነው” ሲሉም አቶ ለገሰ አስጠንቅቀዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ሁሉ ህወሓት ጠቅላላ ጉባኤውን በሚያደርግበት ጊዜ መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፤ የፕሪቶሪያው ስምምነት “በአግባቡ አለመከበሩ” በትግራይ ክልል “ስር የሰደደ ስጋት እንዲኖር፣ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን እንዲጠፍ አድርጓል” ብሏል።
ህወሓት እንደ ፓርቲ ህልውናውን ለማስቀጠል በሚያደረገው ሂደት፤ የፓርቲው አመራሮች “የእርስ በእርስ ሽኩቻ” እንዲሁም በህወሓት እና በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር መካከል ቁርሾዎች መፈጠራቸውን ኢዜማ በመግለጫው አትቷል። ይህ ሁኔታ በትግራይ ክልል ለሚኖሩ ዜጎች “ከፍተኛ ስጋት” መደቀኑንም ፓርቲው ገልጿል።
“በጥይትና በጠብመንጃ ማሰብ ጊዜው ያለፈበት ያረጀ ያፈጀ መንገድ ነው” ያለው ኢዜማ፤ “እኔ ያልኩት ብቻ ካልሆነ ከሚል ግትርነት እንዲወጣ እና በሰከነ መንገድ ማሰብ” እንደሚገባ በመግለጫው አሳስቧል። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርም ሆነ የፌደራል መንግስት፤ ለዜጎች ሰላም እና ደህንነት “ከምንም ጉዳይ በፊት ቅድሚያ እንዲሰጡም” ኢዜማ በዛሬው መግለጫ ጠይቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[ለዚህ ዘገባ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደሩ” ሙሉጌታ በላይ አስተዋጽኦ አድርጓል]