በ12ኛ ክፍል ፈተና ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች 5.4 በመቶ ብቻ ናቸው  

በቤርሳቤህ ገብረ

የዘንድሮውን 12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን ከወሰዱ 674,823 ተፈታኞች ውስጥ፤ ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ያስመዘገቡት ተማሪዎች 5.4 በመቶ ብቻ መሆናቸውን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። ተማሪዎችን ካስፈተኑ ትምህርቶች ቤቶች መካከል 1,363 የሚሆኑት አንድም ተማሪ አለማሳለፋቸውን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይህንን የገለጸው የዚህን አመት የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ውጤት፤ ዛሬ ሰኞ ጷጉሜ 4፤ 2016 ይፋ ባደረገበት ወቅት ነው። ለሶስተኛ ጊዜ በመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ እንዲሰጥ የተደረገውን ይህን ሀገር አቀፍ ፈተና ከወሰዱት ተማሪዎች ውስጥ፤ ስምንት በመቶ ያህል የሚሆኑት በይነ መረብን ተጠቅመው የተፈተኑ ናቸው። 

የዘንድሮውን ሀገር አቀፍ ፈተናውን ለመውሰድ ከተቀመጡት ተማሪዋች መካከል፤ ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበው በተፈጥሮ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ነው። ከተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ ፈተናውን ከወሰዱ 321,536 ተማሪዎች መካከል፤ ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ያመጡት 9 በመቶው መሆናቸው ሚኒስቴሩ አስታውቋል። 

የማህበራዊ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ፈተናውን ከወሰዱት 353, 287 ተፈታኞች የማለፊያ ውጤት ያስመዘገቡት 2 በመቶ ብቻ እንደሆነ የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። በአጠቃላይ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች 1,221 መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

በ2016 የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና፤ በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ የተመዘገበው ከፍተኛው ውጤት 575 ሲሆን በማህበራዊ ሳይንስ ደግሞ 538 መሆኑ ዛሬ ይፋ ተደርጓል። ሁለቱም ከፍተኛ ውጤት የተመዘገቡት፤ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ነው። 

በካቴድራል እና በኢትዮ ፓረንትስ ትምህርት ቤቶች ሴት ተማሪዎች ያስመዘገቡት ይህ ውጤት የተመዘገበው፤ ፈተናው ከ600 ተመዝኖ መሆኑን ፕሮፌሰር ብርሃኑ አስረድተዋል። ይህ ምዝና ከትግራይ ክልል ውጪ ባሉት ሌሎች ቦታዎች ተግባራዊ የተደረገ መሆኑ በዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተጠቅሷል።

@ethiopiainsider

ለ12ተኛ ክፍል ፈተና በሃገር ደረጃ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡት እነማን ናቸው? ethiopia news ethiopiannews berhanu_nega ministryofeducation 12thresult 12thresult2024 education exam 12exam ethiopianuniversity ethiopiainsider ኢትዮጵያ ዜና የኢትዮጵያዜና 12ኛክፍል የፈተናውጤት ፈተና ብርሀኑነጋ ዩኒቨርስቲ ትምህርትሚኒስቴር ኢትዮጵያኢንሳይደር

♬ original sound – Ethiopia Insider – Ethiopia Insider


“የትግራይ [ክልል] ፈተናዎች ትንሽ ይለያሉ። በፊትም ከ700 ነው የታረሙት። እና የእዚህን አመት 12ኛ ክፍል አይጨምሩም። ግን 675 ከ700 የተገኘበት ውጤት ነው። በነገራችን ላይ ይህንን [ውጤት አስመልክቶ] ከክልሎች ጋር ስንወያይ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው 675 [ውጤት] የተገኘው። ይህንን ያመጣው ከቃላሚኖ ወንድ [ተማሪ] ነው” ሲሉ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ተናግረዋል።  

የዘንድሮውን ፈተና ካስፈተኑ ትምህርት ቤቶች መካከል 1,363 የትምህርት ቤቶች “አንድም ተማሪ አለማሳለፋቸውን” የትምህርት ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። በኢትዮጵያ ያሉ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ብዛት 3,792 ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)