የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በታክሲዎች የሰርቪስ አገልግሎት ላይ ጥሎት የነበረውን ገደብ ሙሉ ለሙሉ አነሳ 

በቤርሳቤህ ገብረ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ ለተማሪዎች የሰርቪስ አገልግሎት በሚሰጡ ታክሲዎች ላይ ጥሎት የነበረውን ገደብ ከዚህ ወር ጀምሮ ማንሳቱን አስታወቀ። ቢሮው አገልግሎቱን ለሚሰጡ ታክሲዎች ፈቃድ የመስጠት ኃላፊነቱንም ወደ ታክሲ ማህበራት አዛውሯል። 

መስሪያ ቤቱ ይህን ይፋ ያደረገው፤ የትራንስፖርት ጉዳይ ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር ዛሬ አርብ መስከረም 3፤ 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባው ኔክሰስ ሆቴል ባደረገው ውይይት ላይ ነው። ቢሮው የዛሬውን ውይይት የጠራው፤ በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን የትራንስፖርት እጥረት ችግር ለመፍታት ባዘጋጀው የሶስት ወር እቅድ ላይ ለመወያየት ነበር። 

በተጠናቀቀው 2016 ዓ.ም. በከተማይቱ በትራንስፖርት ፍላጎት እና አቅርቦት መካከል “ከፍተኛ የሆነ አለመመጣጠን” መስተዋሉን በቢሮው የህዝብ ትራንስፖርት አደረጃጀት እና ስምሪት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ ስዩም ለተሰብሳቢዎቹ ተናግረዋል። የትራንስፖርት አቅሞችን “በአግባቡ እና በሙሉ አቅም አለመጠቀም” ሌላው በዘርፉ የሚታይ ችግር መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። 

በአዲስ አበባ ያለው የትራፊክ ጭንቅንቅ፤ የተሽከርካሪዎችን ምልልስ እንዲቀነስ በማድረግ የትራንስፖርት ችግሩን ይበልጥ እንዳባባሰውም አቶ አሸናፊ አስረድተዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ፤ ይህን ችግር ለመፍታት በቀጣይ ሶስት ወራት ሊተገብራቸው ካቀዳቸው መፍትሔዎች መካከል አንዱ ለብዙሃን ትራንስፖርት ተብለው በተለዩ መስመሮች ላይ “አስፈላጊውን የቁጥጥር ስራ ማከናወን” ነው።  

በአጥር ወይም በበር የተዘጉ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን ማስከፈት እንዲሁም በእግረኛ እና በውስጥ ለውስጥ መንገዶች በሚካሄዱ ንግዶች ወይም ሁነቶች ላይ ቁጥጥር ማድረግ በመፍትሔ ሃሳብነት ከቀረቡት ውስጥ ይጠቀሳሉ። የተማሪ ሰርቪስ አገልግሎት በሚሰጡ ታክሲዎች ምክንያት የትራንስፖርት እጥረት እንዳይፈጠር፤ ተሽከርካሪዎቹ በተመደቡበት ተርሚናል ላይ አገልግሎት እንዲሰጡ ቢሮው “ጥብቅ ቁጥጥር” ለማድረግም አቅዷል። 

ከትምህርት ቤቶች መከፈት ጋር በተያያዘ የሚኖረውን የትራንስፖርት አቅርቦት እጥረት ለመፍታት፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ያሉ አውቶብሶች “በሙሉ አቅም አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ” የሚለውም በቢሮው የሶስት ወር እቅድ ውስጥ ተካትቷል። በተማሪዎች ላይ ያለውን የትራንስፖርት እጥረት ለማቃለልም፤ ቢሮው የሰርቪስ አገልግሎት በሚሰጡ ታክሲዎች ላይ የነበረውን ገደብ እንደሚያነሳ በዛሬው ውይይት ላይ ተገልጿል።

እስካሁን በስራ ላይ በቆየው አሰራር፤ ለተማሪዎች የሰርቪስ አገልግሎት ለሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ፍቃድ ሲሰጥ የነበረው “በፐርሰንት” ተሰልቶ እንደነበር አቶ አሸናፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ስሌቱ የሚከናወነው በታክሲ መስመሮች ስምሪት ላይ ያሉትን ተሽከርካሪዎች ቁጥር መሰረት በማድረግ መሆኑንም አስረድተዋል። 

በአዲስ አበባ ከተማ ባለው “የትራንስፖርት እጥረት” ምክንያት፤ በታክሲዎች የሰርቪስ አገልግሎት ላይ ተጥሎ የነበረው ይህ “የፐርሰንት” ገደብ የዘንድሮው የትምህርት ዘመን ከሚጀመርበት ዕለት ጀምሮ እንደሚነሳ አቶ አሸናፊ ገልጸዋል። ይህን አገልግሎት ለመስጠት ለሚፈልጉ ታክሲዎች ይሰጥ የነበረውን ፈቃድም፤ ከከተማይቱ ትራንስፖርት ቢሮ ወደ ታክሲ ማህበራት መዛወሩን አክለዋል። 

በአዲስ አበባ ከተማ 13 የታክሲ ማህበራት እንደሚገኙ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በማህበራቱ ስር ካሉ አምስት ሺህ ገደማ ታክሲዎች በተጨማሪ ሰባት ሺህ ገደማ ድጋፍ ሰጪ ተሽከርካሪዎች በከተማይቱ የታክሲ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ የቢሮው መረጃ ይጠቁማል።

የታክሲ ማህበራቱ የሰርቪስ አገልግሎት ፈቃድ ከመስጠት ባለፈ፤ በስራቸው ያሉ ተሽከርካሪዎችን መከታተል እና መረጃ መስጠት ግዴታ እንዳለባቸው የህዝብ ትራንስፖርት አደረጃጀት እና ስምሪት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል። ታክሲዎቹ ለተማሪዎች የሚሰጡትን የሰርቪስ አገልግሎት ቀደም ብለው ሰርተው፤ ለህዝብ ትራንስፖርት በተመደቡበት ተርሚናል ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ መገኘት ይገባቸዋል ብለዋል።

“[ከዚህ ቀደም] የሰርቪስ አገልግሎት የሚሰጡት ሰአታቸው አልተሻሻለም ነበር። ሰርቪስ ሰርተው ሲጨርሱ፤ ‘ፒክ ሃወሩ’ ካለፈ በኋላ ነበር የሚገኙት። ይህ ከሆነ ደግሞ ህዝቡን አያገለግሉም። አሁን ቀደም ብለው የተማሪ ሰርቪስ ሰርተው ሲጨርሱ፤ ቢያንስ [ጠዋት] አንድ ሰዓት ላይ ተርሚናል ገብተው ስራውን እንዲሰሩ ነው” ሲሉ አቶ አሸናፊ አብራርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)